Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመንግሥትና ሲቪክ ማህበራት እሰጥ አገባ

0 1,122

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ባሳለፍነው ሳምንት፤ በሼራተን አዲስ፤ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት፣ ፋና ፕሮድካስቲንግና የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በጋራ ያዘጋጁት አንድ መድረክ ነበር፤ «በአገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሲቪክ ማህበረሰብ ሚና ተሞከሮች፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች» በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደ መድረክ፡፡ መድረኩ ከምክክር ባለፈ እስጥ አገባ የበዛበት፣ በሰለጠነ መንገድ የሃሳብ ፍልሚያ የተካሄደበትና ጥናታዊ ወረቀቶችም የቀረቡበት ሆኖ አልፏል።

የመነሻ ጽሑፎች በጨረፍታ

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡትና ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶክተር አሰፋ ፍስሐ ባቀረቡት ጽሑፍ እንደተብራራው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሲቪክ ማህበራት አሁን ያላቸውን ቅርጽ የያዙት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በተለይም የበርሊን ግንብ ከፈረሰ በኋላ ነው፡፡ በሊብራልም ይሁን በሶሻሊስት ርዕዩተ ዓለም የሲቪክ ማህበራት የተለያየ ሚና ያላቸው ቢሆኑም በሁለቱም ዘንድ ፋይዳቸው ቅቡል ነው።

ዶከተሩ በዚሁ ጽሑፋቸው፤ በኢትዮጵያም እንደ እድርና መሰል በሆኑ ባህላዊ መንገዶች የሲቪክ ማህበራት ከ60 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተሳታፊ እያደረጉ ናቸው ብለዋል። ዘመናዊ የሲቪክ ማህበራት እንቅስቃሴ የተጀመረው ግን በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በተለያዩ የሙያ ማህበራት አማካኝነት እንደሆነና ከሦስት ዓመት በፊት የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው ከሦስት ሺህ 77 በላይ የሲቪክ ማህበራት በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ብለዋል።

ከኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት መድረክ የመጡት ወይዘሮ ሳባ ገብረመ ድህን በበኩላቸው፤ የሲቪክ ማህበራት የፖሊቲካ ስልጣን ለመያዝና ለትርፍ ያልተቋቋሙ፣ ህብረተሰቡን የሚውክሉ፣ በአገር ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ላይ የህዝብ መገናኛ፣ መነጋገሪያና ለውጥ ማምጫ መድረኮች መሆናቸውን አስምረውበታል። ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያም ህገ መንግሥቱ ከጸደቀ በኋላ በርካታ ማህበራት ህጋዊ ሆነው ተመስርተዋል። በአሁኑ ወቅትም በፌዴራል ከ3 ሺ እና በክልል ከአንድ ሺ በላይ የሲቪክ ማህበራት የተባለውን ዓይነት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው ይላሉ።

እውነታው ይሄ ቢሆንም ይላሉ ወይዘሮ ሳባ በመንግሥት፣ በመገናኛ ብዙሃንና በህዝቡ ዘንድ የሲቪክ ማህበራት ማለት የዕርዳታ ማግኛና የሙስና ምንጭ እንደሆኑ አድርጎ የመውሰድ ችግር አለ፡፡ ተቀራርቦ መመካከር አለመኖር፣ የገቢ ችግር፣ የራሳቸው የሲቪክ ማህበራቱ በጊዜ የተወሰነ ግብ አለመኖርና ሌሎች ችግሮች የዘርፉ ሁነኛ እንቅፋት ናቸው ሲሉ በጽሑፋቸው አብራርተዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ጉዳዮች አስተባባሪ አቶ አብዱላዚዝ መሀመድ በበኩላቸው ባቀረቡት ጽሑፍ፤ የሲቪክ ማህበራት በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 31 እና በአዋጅ ቁጥር 621/2000 ተግባር፣ ኃላፊነታቸውና ነፃነታቸው ጭምር በግልጽ መደንገጉን በመግለጽ ፋይዳቸውን መንግሥት የሚረዳበትን ልክ አስቀምጠዋል። ማህበራቱ በአባላቱ ሙሉ ተሳትፎ ላይ የተመሰረቱ፤ ዴሞክራሲያዊ አሠራር የሚከተሉ፤ የገቢ ምንጫቸውና ተግባራቸው ምን መሆን እንዳለበትም ጭምር ያስቀምጣል። ማህበራቱ መንግሥት በሚሠራው ሥራ ላይ ተጨማሪ ማስተካከያ በማድረግና በህዝቡ ተጠያቂ እንዲሆን ያግዛሉ። ከሌሎች አካሎች ጋርም በመደራደር ችግሮች እንዲፈቱና ጥቅማቸው እንዲከበር ይሠራሉ።

የልማታዊ መንግሥታት መርህ ፈጣን ቀጣይነት ላለው ልማት ትኩረት ሰለሚሰጥ የሲቪክ ማህበራት ወሳኝ ናቸው። ልማታዊ መንግሥት ልማታዊ የሆኑ ሃሳቦች ብቻ ሳይሆን ልማታዊ ያልሆኑ አስተሳሰቦች ወደ መድረክ ቀርበው ክርክር ከተደረገባቸው በኋላ የብዙሃኑን ድምፅ ይዞ ይሄዳል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ሁሉንም ለልማቱ የሚያነሳሳ በመሆኑ ህዝቡ በንቃት እንዲሳተፍና የላቀ ሚና እንዲጫወት የሲቪክ ማህበራት መሳሪያ ናቸው ብለዋል፤ አቶ አብዱላዚዝ፡፡

የሲቪክ ማህበራት ሚናቸው እንዳለ ሆኖ ግን የተቀመጡ ህጎችን አክበረው መሥራት አለባቸው። አባሎቻቸውን የሚያስተናግዱበት ግልጽ መስፈርት ሊኖራቸውም ይገባል ነው ያሉት አቶ አብዱላሊዝ። የእኛ መብት ብቻ ይከበር ሌላው የፈለገውን ይሁን ማለትም የለባቸውም። ነፃነታቸውን ከመንግሥትም ይሁን ከፓርቲዎች ማስጠበቅ አለባቸው። ከጥቂቶች ክበብ ወይንም ከቤተሰብ ሸንጎነት የወጡ መሆን እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

እርሳቸው እንደሚሉትም፤ በመንግሥት በኩልም የወጡ ህጎችን ተከታትሎ ተፈፃሚ ማድረግና የሲቨክ ማህበራትን መደገፍ ይጠበቃል። የሚወጡ ፖሊሲዎችና ህጎችን ለሚመለከታቸው ማህበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማቅረብና የሚያቀር ቧቸውን አማራጮች በማዳመጥ፤ መስተካከል አለበት ብሎ የሚያምነውን ማስተካከል ይገባዋል። ሁለቱ አካላት ሰምምነት በደረሱባቸው ጉዳዮች ላይም በጋራና በቅንጅት መሥራትና አፈፃፀማቸውን በጋራ መገምገም አለባቸው። ልዩነታቸውንም በህጋዊና በሰለጠነ መንገድ ይዘው መሄድ አለባቸው።

የሃሳብ ፍጭት አንድ

የሙያ ማህበራትን በመወከል በዕለቱ በስፍራው የተገኙት ዶክተር መሻሻ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበራት የሚፈለገውን ያህል እየሠሩ ካልሆነ የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጁን በመፈተሽ ያለበትን ችግር መፍታት ያስፈልጋል፤ በተለይም ደግሞ በተዳጋጋሚ በችግርነት የሚነሳው የ70/30 እና የ10/90 ቀመሮች ያመጡት መልካም ነገርና ያመጡት አሉታዊ ውጤት መታየት አለበት ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

ምሁራንን የወከሉትም ዶክተር ካሳሁን ደግሞ፤ የሲቪክ ማህበራት በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ምን አስተዋፅኦ አድርገዋል፤ ምን ይቀራል የሚለውን ማጥናት፤ በመንግሥትና በአገር ላይ ያደረሱት ተጽዕኖ፤ የፖለቲካ ተቀጽላ በመሆን ዴሞከራሲያዊ ስርዓትን በማናገት የፈጠሩት ጫና ምን ያህል እንደሆነ መመርመርና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ፈትሾ ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል።

ከትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ የመጡት አቶ ክብረአብ አበራ ለማህበራቱ ሜዳው ቢኖርም ያለ አቅም ምንም ዓይነት ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚል መከራከሪያ ነጥብ አላቸው። የቤት ኪራይና ሠራተኛ መቅጠር በማይችሉበትና የህልውና ጥያቄ ውስጥ ሆነው ማህበራቱ ለዴሞክራሲ ስርዓት አጋዥ ሊሆኑ አይችሉም፤ በተፈጠረውን ምህዳር ላይ ለመጫወት የ10/90 ቀመር ሊነሳላቸው ይገባል ሲሉም ሞግተዋል።

ሌሎች ሃሳብ እቅራቢዎችም አዋጁ ከወጣ በኋላ በርካታ የሲቪክ ማህበራት መዘጋታቸውን በማነሳት አዋጁ ሊሻሻል እንደሚገባው ተከራክረዋል። ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ከቀዳሚ ፈራሚዎች ተርታ የምተመደብ አገር ሆና ሳለ የዓለም ሲቪክ ማህበራት የኢትዮጵያን ማህበራት አይርዱ በማለት የፈረመችውን ስምምነት መጻረር ነው፤ የአገሪቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ያህል እያንዳነዱ ዜጋ ኃላፊነት አለበት፤ ለአገር ጉዳይ አንዱ ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ መደረግ የለበትም፤ በአገሩ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሞከረን አካል በህግ ተጠያቂ ማድረግ ይገባል እንጂ ገና ለገና በዕርዳታ የሚመጣ ድጋፍ ለሌላ ዓለማ ይውላል ተብሎ እንዳይቀበሉ መከልከል የለበትም፤ አለበለዚያ ከዓለም ማህበረሰብ እየተገለሉና እየኮሰመኑ ይሄዳሉ ሲሉም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የሥራ ተቋራጮች ማህበርን ወክለው የመጡት ኢንጅነር ጸደቀ ይሁኔ፤ እባብን ያየ በልጥ በረየ እንደሚባለው ከ1997 .ም በኋላ ሲቪክ ማህበራት እራሳቸውን የማሰርና ለመብት የመቆምና የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የዝግጁነት ችግር አለባቸው ብለዋል። የ10/90 ቀመር ሁሉንም ሲቪክ ማህበራት እንደማያካትት አንስተው በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ግን የ10/90 ቀመር መጣሉ ተገቢ መሆኑን በማንሳት ተከራከረዋል፡፡ በሌሎች አገሮች ከታየው የቀለም አብዮትና የእርስ በእርስ ጦርነት የሚያድነን በመሆኑም ቀመሩ ይነሳ ያሉት ተከራካሪዎች ስህተት ናቸው በማለት ሞግተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር አሰፋ፤ ጫፍ የወጡ ሲቪክ ማህበራት የሉም ብሎ መከራከር ስህተት እንደሆነ በመግለጽ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት የተፈጠረውን ሁኔታ በማሳያነት ያነሳሉ፡፡ የመምህራን ማህበር ለሁለት ተከፍሎ ቁጥር አንድ የቅንጅት ቁጥር ሁለት የኢህአዴግ ደጋፊዎች ሆነው ታይተዋል፡፡ መንግሥትም ከዚህ ዓይነቱ ተሞክሮ በመነሳት ማህበራቱ የአገር ውስጥና የውጭ ተጽዕኖን በመቀበል አስፈፃሚ ሆነዋል ብሎ በማመኑ ብሎም የሚመጣውን ዕርዳታ ለህዝብ ጥቅም ከማዋል ይልቅ ለግለሰቦች መዝናኛ የሚወጣው እንደሚ በልጥ በማረጋገጡ አዋጁ መውጣቱን ተናግረዋል።

ሲቪክ ማህበራት ከተቀመጠላቸው የተዛነፈ አካሄድ ከተከተሉ፤ መንግሥትም ቢሆን ሲቪክ ማህበራት ከተዳከሙና ከመንግሥት ገለልተኛ የመሆን ጥያቄ ውስጥ ሲገቡ የአሰላለፍ ችግር በማምጣት የአምናውን ዓይነት ብጥብጥ ያመጣሉ። በመሆኑም ሲቪክ ማህበራት ህበረተሰቡን ወደ አንድነት የሚያመጡ፣ የህብረተሰብ መገናኛና የሚያስተሳስሩ ገመድ መሆን አለባቸው። ስለዚህ በሁሉቱም በኩል ከጽንፍ መውጣትና እርስ በእርስ መጠራጠርን ማቆም አለባቸው ሲሉም መክረዋል።

የሃሳብ ፍጭት ሁለት

በአዋጁ ላይ ከተደረገው የሃሳብ ፍጭት በተጨማሪ በተሳታፊዎች የተነሳው ጉዳይ መንግሥት በሰብዓዊ መብትና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ መግባትና ጫና ማድረግ በርከት ባሉ ተሳታፊዎች የተነሳና የሃሰብ ፍጭት የተካሄደበት ጉዳይ ነበር።

የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪያዎችን ማህበር ወክሎ የመጣው አቶ ደሳለኝ ሀይሉ፤ ከሦስት ሺህ ዓመት በላይ ከለማው ልማት ይልቅ በ25 ዓመት የለማው የበለጠ ነው፤ በኪነጥበብ ፈጠራ ያለው ሁኔታ ግን በጣም አሳሰቢ ነው ሲል ሃሳቡ ጀምሯል። በመቀጠልም ኪነጥበባዊ በሆነ መንገድ ዜጎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የአስተሳብ ለውጥ እንዲያመጡ ከምሥራት ይልቅ በካድሬ ጩኸት ብቻ አገር ለመለወጥ ጥረት ይደረጋል ሲል ተከራክሯል። ስለሆነም መንግሥት ቆም ብሎ በሙያ ማህበራት ያሉትን ችግሮች ያስጨነቁኛል ብሎ ማስብና የሙያ ማህበራት የተዳከሙበትን ምክንያት ፈትሾ ከባለሙያዎቹ ጋር አብሮ መሥራት አለበት ሲል ተደምጧል።

ሌላ ተሳታፊ ደግሞ፤ ጠንካራና ሞጋች ሚዲያ፣ ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትና ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ በሌለበት ሁኔታ እንዴት ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት ሊከበር ይችላል ሲሉ ጠይቀዋል። የሲቪክ ማህበራትም ሊጠናከሩ አይችሉም ነው ያሉት። በጋራ አገራችን እስከመቼ ነው የውሸት እየኖረን የእውነት የምንሞተው? ይህ አይገባንም። መንግሥት ከግማሽ በላይ በጀቱን ከውጭ አገር እየተቀበለና እየበጀተ ስለምን የሲቪክ ማህበራት ይከለከላሉ? ሲሉ ተከራክረዋል።

በተለያዩ ኮሌጆች የሥነ ምገባርና ሥነዜጋ መምህር መሆናቸውን የገለጹትና አቶ ታዩ ቦጋለ የተባሉ ተሳታፊ፤ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ለውጥ መኖሩንና ህገ መንግሥቱም ምንም ዓይነት ጉድለት እንደሌለበት አንስተዋል። ጽንፍ የወጣ የተቃዊምና የመንግሥት የፖለቲካ ልሂቃን የአገሪቱ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጨቆኑ አድርገዋል ሲሉ ወቅሰዋል። ተቃዋሚዎች ከእነሱ ውጪ ያለ አስተሳሰብ እንትን የነካው እንጨት አድረገው ይመለከታሉ፤ መንግሥትም እሱ ያለው ካልሆነ ፀረ ልማት፣ ፀረ ህዝብ ሁሉንም ይፈርጃል፤ በዚህ መካከል ህዝብ እየተሸማቀቀ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱ በአግባቡ ሳይከበርለት እንዳለ አለ ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ፌዴሬሽን የመጡት ብርሃኑ ድሪባ፤ ፌዴሬሽናቸው ከ500 ሺ በላይ አባላት ያሉት መሆኑና በአገር አቀፍ ደረጃ ነፃ ሆኖ እየሠራ ያለ ማህበር መሆኑን በማንሳት፤ አንዳንድ ማስተካከያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ቢኖሩም ከመንግሥት ነፃነታቸውን ጠብቀው እየሠሩ መሆናቸውንና ጫና እየተደረገባቸው እንዳልሆነ ጠቅሰው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መምሁራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስም፤ ማህበራቸው መምህራን የቤት ባለቤት፣ የደመወዝ ማሻሻያና ሌሎች የመምህራን መብት ለማስጠበቅ የሚያስችል ሥራ ማከናወ ናቸውን ይናገራሉ። የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደሌ ለባቸውም እንደዚሁ። «ሁሉም ነገር የሚመጣው በችሮታ ሳይሆን በሥራ ነው። በመንግሥት ውስጥ መልካም የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ ቢሮክራሲ የሚያበዙ አሉ። ከመንግሥት ጋር አብረን በመሥራት የአባሎቻችንን ጥቅም ለማስከበር ርቀታችንን ጠብቀንና ተጠንቅቀን አብረን እንሠራለን ቀይ መስመር የሚባል ነገር ግን የለም» በማለትም ተናግረዋል።

የአማራና የአዲስ አበባ ሴት ማህበራት ተወካዮችም፤ ሥራ ለመሥራት የማያስችል ችግር አለመኖሩን ያነሳሉ። ነገር ግን በአሠራር መስተካከልና ትግል የሚጠይቁ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ያነሳሉ። የሲቪክ ማህበራት እራሳቸውን ነፃ አድርገው ከመሥራት ይልቅ መንግሥት የሚለውን ብቻ አለበለዚያም ከመንግሥት ጋር አብሬ ከሠራሁ ተለጣፊ እባላለሁ በሚል እራሳቸውን የሚያሥሩ አሉ። «በህገ መንግሥቱ የተቀመጠውን መብታችንን ተግባራዊ እስካደረግን ድረስ ማንም ተፅዕኖ ሊያደርግብ አይችልም» ብለዋል።

አያሌው መስፍን የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ፤ «በመንግሥትና በህዝብ መካከል ያለው ግንኙነት የቁጥጥር መሆን የለበትም። የሲቪክ ማህበራት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ተግባራዊ እንዲሆን ቁጥጥሩ መላላት አለበት። ዝቅተኛ ቁጥጥር በማድረግና ነፃነት በመስጠት መተማመንን መገንባት ይቻላል» ሲሉ ገልጸዋል።

የወጣቶች ፌዴሬሽን ተወካይ አቶ ታረቀኝ አብዱልጀባር፤ «ወጣቶች መብታቸውን ለማስከበርና ከመንግሥት ጋር መሥራት የሚገባንን እየሠራን ነው። ነገር ገን በህዝብ ዘንድ እንደተለጣፊ አድርጎ የማሰብ። በአስፈፀሚው በመንግሥት ሳንባ ትነፋሽ የሚተነፍሱ አድረጎ የማሰብ የተዛባ አመለካከት አለ። ይህ መታረም አለበት። የበለጠ የወጣቶችን ጥቅም ለማስከበር የምክር ቤቶች ውክልና ሊኖርን ይገባል። የሚቆራረጡ የወጣቶች መደረኮችም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው» ብሏል።

ማጠቃለያ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ማኅበራት ነፃና ገለልተኛ በመሆን በአገሪቷ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ግንባታ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል። ማኅበራት ሚናቸውን በመለየት የአባሎቻቸውና የዜጎች መብትና ጥቅም እንዲከበርና የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲጎለብት መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርጉበት ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር አለባቸው ነው ያሉት። ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ከበጎ አድራጎት መሪዎች ጋር በዓመት ሁለት ጊዜ በመገናኘት ውይይት እንደሚደረግም አስታውሰዋል፡፡

በውይይቱ መቋጫም ላይ ከላይኛው የመንግሥት መዋቅር እስከታችኛው ድረስ መንግሥት በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን በአቶ አብዱላዚዝ ተገልጿል። የሲቪክ ማህበራቱም በአገሪቱ ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና ከውጭ አካላት ተጽዕኖ ነፃ በሆነ መልኩ አገራዊ አንድነ ታቸውን በማጎልበትና ማህበራቱ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና ግንባታ ውስጥ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

አጎናፍር ገዛኽኝ

– See more at: http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/technology/item/12366-2017-04-26-18-12-46#sthash.eFZQABv9.dpuf

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy