NEWS

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

By Admin

April 28, 2017

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዘይድ ራአድ አል ሁሴን ከሚያዝያ 24 ጀምሮ ኢትዮጵያን ለሶስት ቀናት ይጎበኛሉ፡፡

ኮሚሽነሩ የኢፌዴሪ መንግሥት ባደረገላቸው ግብዣ መሰረት ሀገሪቱን እንደሚጎበኙ ታውቋል፡፡

እግረ መንገዳቸውን ከአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጋር እንደሚወያዩም ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሀገሪቱን የሰብአዊ መብት ሁኔታና የመንግሥታቱን ድርጅት የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ተግባራት በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣

ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ አባዱላ ገመዳና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ምክክር ያደርጋሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኮሚሽነሩ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር፣ ከኢትዮጵያ ሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶችና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተገናኝተው እንደሚነጋገሩም ታውቋል፡፡

ኮሚሽነር ዘይድ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማትን ጨምሮ ከህብረቱ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር ስማይል ቼርጉይና ከህብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሴሱማ ሚናታ ሳማቴ ጋር ተገናኝተው የሁለቱን ተቋማት የሰብዓዊ መብቶች ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ያደርጋሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የተጠናከረ ትብብር ለማድረግ በኒዮርክ በተፈረመው የስምምነት ትግበራና መሰል የትብብር ዘርፎች የውይይታቸው አጀንዳዎች እንደሚሆኑም ተገልጿል፡፡

ኮሚሽነሩ በጉብኝታቸው ማጠቃለያ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡም በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮ ይፋ ማድረጉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡