Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የማር፣ የወተት እናት

0 891

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምንም እንኳን ብዙ ጊዜ ከተሞች ላይ ስላለው እንቅስቃሴ ብንሰማም ከሰማንያ በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርሶ የሚያድር ገበሬ ነው። በአብዛኛው አርሶ አደር ዝናብን ጠብቆ፣ በሬውን እየነዳ፣ ሻል ካለም ዘመናዊ ማረሻ መሣሪያዎችን እየተከራየ፤ ከብዙ ድካም በኋላ ከተሜው በቀላሉ ገበያ ላይ የሚያገኘውን የግብርና ምርት ያቀርባል። በዘመናዊ የአሠራር ሥራው የቀለለለት እንዳለ እናውቃለን። ከአዝዕርት ጀምሮ የእንስሳትና ከእንስሳት የሚገኙ ምርቶች የገበሬው የድካም ውጤት ናቸው።

ከገበሬው ጀርባ ብርቱ ሴት እንዳለች ልብ ይሏል። ያም ብቻ አይደለ፤ አሁን አሁን ከፊት አንጸባርቃ የወጣች እማወራም ብዙ ናት። «ማንጸባረቅስ ድሮም የራሷ ነው፤ አሁን እውቅና ተሰጣት እንጂ» አትሉኝም?! ጉዳዩን እንዳነሳ ምክንያት ወደሆነው ጉዳይ እንግባ፣ ከትናንት በስቲያ በሆለታ የግብርና ምርምር ማዕከል ተገኝቼ ነበር። በዛም የዘንድሮን ሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ለሽልማት የበቁ አርአያ ወይም ሞዴል ለሆኑ ሴቶች የተዘጋጀላቸው የሦስት ቀናት ሥልጠና ነበር።

ሥልጠናው በማር እንዲሁም በወተት ምርት ላይ ለሚሠሩ የተዘጋጀ ነው። ይህን ዝግጅት ሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል በሙሉ ፈቃድ ሲያስተናግድ ሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ማለትም የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት እንዲሁም ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ተባብረውበታል። ለሰው ልጅ ምርጥ ምግብ የሚባለውን ወተት እናት ለልጇ እንድትሰጥ እነዚህ ሴቶች ደግሞ ከበረት ገብተው ከብቶቻቸውን አልበው ለገበያ ያቀርባሉ፣ እናት የነካችው ሁሉ እንዲጣፍጥላት የጣፈጠ ማር ከንብ ቀፎ አውጥተው እንካችሁ ይላሉ፤ ሥልጠናው የተዘጋጀው ለእነዚህ ሴቶች ነው።

ወይዘሮ ፀሐይ ቢያድግልኝ በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስቴር የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ናቸው። መሥሪያ ቤታቸው በኢትዮጵያ ያሉ ሴቶችና ወጣቶች በምን ዓይነት የሥራ ዘርፍ ተሳታፊ ቢሆኑ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ያነሳሉ። በዚህም መሰረት በተለይ ሴቶች ተደራጅተው ሊሠሩበት የሚገባውን ዘርፍ መምረጥ ቀዳሚው ተግባር እንደሆነ ነው የሚናገሩት። ይህን ተከትሎም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ 101 የሥራ ዝርዝሮችን በ13 የሥራ ዘርፎች እንደለየ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሯ አያይዘውም «ሥራ መፍጠር ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ እንዲሆኑ የሥራ ዝርዝር ተግባራትን መለየት፣ ፓኬጅ ማዘጋጀት፣ ፖሊሲ መቅረጽ፣ ስትራቴጂ ማውጣት ላይ ስንሠራ ነበር» ብለዋል። «ሴቶችን ለማብቃት ድጋፍ ያስፈልጋል» የሚሉት ወይዘሮ ፀሐይ፤ ተግባራዊ ሥልጠናዎች ለእዚህ ተጠቃሽ እንደሆኑ ይናገራሉ። እንደባለሙያ እንደምሳሌ ብለው ያነሱትን ልንንገራችሁ« ሴቶች በዶሮ እርባታ ላይ እንዲንቀሳቀሱ የተወሰኑ ዶሮዎች ይሰጧቸዋል። ነገር ግን ውጤታማ ሳይሆኑ ይቀራሉ፤ ዶሮዎቹም ይሞቱባቸዋል፤ ይከስራሉም። ይህን ለማስቀረት እነዚህ ሴቶች አንድም ሙያዊ ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ በተጨማሪም በዘርፉ ሊሰማሩበት የሚገባውን የሥራ ዓይነት፣ አዋጪ የሚሆነውን በማመላከት በኩል ተግተን እንሠራለን» ይላሉ።

ሴቶች ላይ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉ ያነሳሉ። በእርግጥ እንኳን በዝቅተኛ የኑሮና የተሰሚነት ደረጃ ላይ ሆነው በአመራር ቦታ ያሉ ሴቶች አልተናገሩትም እንጂ ፈተና መኖሩ መች ይቀራል? ምን ያለ ፖሊሲ፣ አዋጅና መመሪያ ቢወጣ ከአውጪው ጀምሮ ያንን የሚተገብር የሰው ልጅ ነውና አስቀድሞ አመለካከት ሊለወጥ እንዲገባ እሙን ነው። ያ እስኪሆን ድረስ አይደል ስለሴቶች መብት፣ እኩልነት እና ተጠቃሚነት የምንነጋገረው? እዚህ ላይ ወይዘሮ ፀሐይ እንዲህ ይላሉ «ሴቶች ተባብረን ከሠራን ለውጥ እናመጣለን»

ወደቀደመ ነገራችን እንመለስ፤  ከላይ ያነሳናቸው የወተት ተዋጽኦ እንዲሁም የማርና የማር ተረፈ ምርቶች በቀላሉ እንደተጨማሪ ሥራ ሊሠሩ የሚቻሉ መሆናቸው የሴቷን ተሳትፎ የበለጠ ሊያካትት የሚችል ነው። የቤት እመቤት የሚሏት የቤቷ አገልጋይ ሴት በዚህ ዘርፍ ስትሰማራ የራሷ የገቢ ምንጭ እንዲኖራት ያስችላል። ታዲያ ቀላል የገቢ ምንጭ መሰላችሁ! ስለዚህ ነገር ከሐረሪ ክልል የመጣችው  ወይዘሮ ጽጌ ቦጋለ ትናገራለች።

ወይዘሮ ጽጌ የወተት ላም እርባታ ላይ ተደራጅታ፣ የግል ንግድ ድርጅት ከፍታ ነው የምትሠራው። ለእዚህ ሥራ ማንቀሳቀሻ አስቀድማ የወሰደችውን ብድር ከፍላ ሁለተኛ ዙር ብድር ጀምራለች። የአንድ ልጅ እናት የሆችው ጽጌ ይህን ሥራ በ2006ዓ.ም ነው የጀመረችው። ከዛ በፊት በነበሩት ዓመታት የመንግሥት ሠራተኛ እንደነበረች ታስታውሳለች።

ታዲያ በዚህ ሥራዋ ለሦስት ሰዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በቅታለች። በአካባቢዋ ካሉ አነስተኛ ማኅበራት ጋር እርስ በእርስ የገበያ ትስስር በመፍጠርም ወተትና እርጎ ላይ በደንብ እየሠሩ መሆኑን ታወሳለች። «ሰው የሚያገኘው የሠራውን ነው፤ የከብትና የወተት ሥራ በአግባቡ ከተያዘ ከሠሩትም በላይ የሚያስገኝ ነው» ትላለች። ሐረሪ ክልል ላይ የሴቶች ጥረት እና ስኬት ምን ይመስላል? ብያት ነበር። «በአካባቢዬ ብዙ ሴቶችን አይቻለሁ…»አለች ጽጌ፣ ይሄኔ ፍላጎት ብቻውን ውጤታማ እንደማያደርግ ነገር ግን ቦታና ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ትናገራለች።

ጥረትና የሥራ ፍላጎት ሳያንሳቸው ነገር ግን የተለያዩ ጉዳዮች እንቅፋት እንደሚሆኑ ትገልጻለች። አንዳንዶች የሚሠሩበት ቦታ ኖሯቸው ብር የሌላቸው ሲሆኑ በአንጻሩ ደግሞ ብር ይዘው ቦታ የሚቸገሩ አሉ። በዛም መካከል ግን በአካባቢዋ ያሉ ሴቶችን እንድታደንቅ የሆነችው በተለይም ተጨናንቀው ግን ውጤታማ መሆን የቻሉ፤ ቤት ተከራተው እየሠሩ ያሉም ሴቶችን አንስታ ነው። እነዛን ሴቶች ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ትገልፃለች።

ወይዘሮ አስቴር ወልዴ ንብ እርባታ ላይ ትሠራለች። ሃያ ሆነው ተደራጅተው መሥራት ከጀመሩ ጥቂት ጊዜያት ብቻ ናቸው ያለፉት። ሥራቸው ሊያስገኝላቸው የሚችለውንም ውጤት ገና አላዩም። ጊዜው ሲደርስ የማር ምርታቸውን በደቡብ ክልል ላይ ነው የሚያቀርቡት። ከዚህ ቀደም እንዲሁ ሥራውን ጀምረው በቦታ ችግር ምክንያት ተቋርጦባቸው እንደነበር አስቴር ታስታውሳለች። ግን አሁን ያ እንደማይደገም እርግጠኛ ሆናለች።

ይህም በአንድ በኩል በዋናነት የቦታ ችግራቸው የሚፈታ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ባሉበት አካባቢ በሚያገኙት ድጋፍና ትኩረት ምክንያት ነው። «የጠየቅነውን አላጣንም፤ እየመጡም ይጎበኙናል። የቦታው ችግር ዳግም አይመጣም። የሴቶች ተሳትፎ በተለይ ቁጠባ ላይ በጣም ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ አለ» ብላለች።

ነገሮች እንዲህ መስመር የያዙና የተስተካከሉ ሲሆኑ ደግሞ ሴቶች ተባብሮ መሥራቱ ላይ የሙጥኝ ሊሉ ይገባል። «ሴት ለሴት ጥሩ አይደለችም» የሚባለውና በብዛት እየሆነ የሚስተዋለው ነገርም ሊቀር ይገባል። ወይዘሮ አስቴርም ብዙ ችግሮች የሚነሱት ካለማወቅ መሆኑን በማንሳት በመመካከር ለራሳቸው የኑሮ ለውጥ ራሳቸው ሴቶቹ እንቅፋት እንዳይሆኑ ጥረት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ።

እነዚህ ሁለት ሴቶች በወተትና በማር ምርት ላይ የሚወስዱት ሥልጠና በጣም እንደሚጠቅማቸው ነግረውኛል። ወይዘሮ ጽጌ ያለችውን ላንሳላችሁ «ሥልጠናው ያለምንም ጥርጥር በጥራት ለመሥራት ይረዳል። ለተሻለ ሥራም የሚያተጋ ነው»። አንድ ትልቅ መልዕክት ደግሞ ታስተላልፋለች «ልንገራችሁ፣ አዎን ከየክልሉ ተመርጠው አርአያ ናቸው የተባሉ ሴቶች ለእዚህ ሥልጠና ተልከዋል። ሥልጠናቸውን ጨርሰው ተመልሰው ሲሄዱስ? እዚህ ላይ በመካከለኛና በቅርብ ከሚገኙ አመራሮች ጀምሮ ሊታሰብበት ይገባል።

«የሚያስፈልገን ነገር ባለንበት ክልል በኩል ቢደርሰን ውጤታማ እንሆናለን። ከአመራሮቹ ጋር ነው መሥራት ያለብን። ሥልጠናውም ገንዘብ ወጥቶበታል፤ ጊዜም ወስዷልና መባከን የለበትም። እንደሄድን ወደሥራ መግባት አለብን። ለእዚህም አመራሮቹ ሊረዱን ይገባል» ባይ ናት። ለለውጥ አይደለ እንደው ብቻ ፖሊሲ ለማስፈጸምና ለሪፖርት እንዲጠቅማቸው ሳይሆን ችግር ካለ ችግሩን ለመፍታት መሠራት አለበት ብላም ታሳስባለች።

እነዚህን ሴቶች እንደማሳያ በቅርብ ስላገኘን ጠቀስናቸው እንጂ በርካታ ስኬቶችና ችግሮች አሉ። ከዚህም ሦስት ዋና ዋና ነጥቦችን እናገኛለን፤ በአንድ በኩል ትልቅ የተባሉ ተቋማት በሴቶች ሕይወት ላይ ለውጥ ለማምጣት እንደሚቻላቸው ማየት እንችላለን። የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴርና የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሚኒስቴር እኩል በእኔነት ስሜት ሠርተዋል። ተግባራዊ ሥልጠናው ለፍሬ የበቃ ጊዜ ደግሞ ሽልማታቸው ያ ይሆናል።

ሌላው በግብርና ዘርፍ ሴቷ ልትሰማራበት የምትችለው መስክ መኖሩና ይህም ራሷን የሚያስቻላት መሆኑ ነው። ወተት ለፈላጊው ማቅረብ፣ እርጎና መሰል የወተት ተዋጽኦን ማሰናዳት፤ በዚህ በኩል ደግሞ ንብ ማነብ፣ ማር ማቅረብና ሰምና ሙጫ የመሳሰሉ ተረፈ ምርቶችን ማውጣት። እዚህ ላይ ብልሽትና ብክነት እንዳይኖር እንደ ግብርና ምርምር ማዕከል ባሉ ተቋማት የተደረጉ ጥናቶች ወደኅብረተሰቡ ወርደው ለባለሙያዋ ሴት ተደራሽ በሚሆኑ ጊዜ ደግሞ የበለጠ ነገሮች ቀላልና ምቹ መሆናቸው አይቀሬ ነው።

ዋናው ደግሞ የሚከተለው ነው። ሴቶች ተባብረው ከሠሩ፣ተ ባብረው ድምጽ ካሰሙ፣ ተጋግዘው ችግራቸውን ከገፉ በትክክል የተነሱለትን ዓላማ ማሳካት እንደሚችሉ፣ እናድርገው ያሉትን ማድረግ እንደማይከብዳቸው ማሳያ ነው። የሰው ልጅ እችላለሁ ካለ ምን የማይችለው አለ? በተፈጥሮ ብልሃትን የታደለች ሴት ደግሞ እንዴት አትበልጥ? እናም ልጨርስ፣ በተፈጥሮ ግብሯ ህይወትን እንደማር እና ወተት የምታጣፍጥ ሴት ይኸው በዚህ ዛሬ በሚጠናቀቅ የሥልጠና መድረክ የማርና የወተት እናት ሆና አይቻለሁ። ቴክኖሎጂውና ሳይንሱ ከጎኗ ቆሟልና ስኬታማ መሆኗ አይቀሬ ነው። እኔም እንደወትሮው እላለሁ «ሴትን መደገፍ ከራሷ ከሴቷ በላይ አገርን የሚጠቅም ነው» ቸር ቆዩኝ!

 

ሊድያ ተስፋዬ

– See more at: http://ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/society/item/12101-2017-04-08-20-01-13#sthash.IjATkn1R.dpuf

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy