Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰላም ዲፕሎማሲያችን

0 413

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰላም ዲፕሎማሲያችን

   ዳዊት ምትኩ

የኢትዮጵያ መንግስት ሀገራዊ ህልውናን የማስጠበቁ ጉዳይ ሊሳካ የሚችለው ሁለት ቁም ነገሮችን፣ ማለትም ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች ላይ መሰረት በማድረግ ብቻ እንደሆነ በማመን ለተግባራዊነቱ ሲንቀሳቀስ መቀየቱ የሚታወቅ ነው።  በመጀመሪያ ደረጃ በከፍተኛ ኋላ ቀርነትና የድህነት አዘቅት ተዘፍቃ ለቆየችው ሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ግንባታና ሰላምን የማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለመበታተን ተቃርባ የነበረችውን ሀገራችንን ለመታደግ የሚያስችል አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ወደ ተግባር የተሸጋገረበት ሁኔታ ነው፡፡

በሌላ በኩልም መንግስት የአካባቢያችን ሰላምና ልማት መረጋገጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለሀገራችን ፈጣን ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ቀጣይነት የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ሁሉ፤ በአካባቢያችን የተረጋጋ ሰላምና ልማት ያለመኖርም በሀገራችን ልማታዊ ጉዞ መሰናክል መሆኑ አይቀሬ መሆኑን በመገንዘብ ለውጫዊ ሁኔታዎችም ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ከፍተኛ ርብርብ አድርጓል፤ በማድረግ ላይም ይገኛል።

ለዚህም ነው— የኢፌዴሪ መንግስት ለአደጋ ተጋላጭነታችን በምክንያትነት የሚጠቀሰውን ድህነትንና ኋላቀርነትን በመዋጋት ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆነበትን ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን እውን በማድረግ ላይ ያተኮረ የውጭ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በመቅረጽ ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል ህዝባዊ ንቅናቄን በመፍጠር ተግባራዊ ማድረግ የቻለውና ዛሬ ለምንገኝበት ደረጃ ላይ መድረስ የተቻለው፡፡

እንደሚታወቀው የቀደሙት መንግስታት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ትኩረት ውጭውን የመመልከት አካሄድን የተከተለ ነበር፡፡ ይህ አካሄድም የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተስኖት ለከፍተኛ ድህነት ሊዳርገን እንደቻለም በአይናችን ያየነውና በጆሯችን የሰማነው ዕውነታ ነው፡፡

በተለይም ያለፋት መንግስታት የውጭ ፖሊሲ በውጭ ጠላቶች የመከበብ ስሜት ጐልቶ የሚታይበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በውጭ ተመልካችነት ላይ ተጠምዶ መቆየቱ፤ የሀገራችን ውስጣዊ ችግሮችና የአደጋ ተጋላጭነታችን እንዲጐለብት ከማድረግ ባሻገር በሀገራዊ ደህንነታችንና ህልውናችን ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ሲፈጥር መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

ታዲያ ይህን ጠንቅቆ የሚያውቀው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መንግስት ቀደምት መንግስታት ይከተሏቸው ከነበሩት ፖሊሲዎች የተለየና ለሀገራዊ ህልውናችን ወሳኝ በሆነው ውስጣዊ ችግሮች ላይ የሚያተኩር የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ መኖር አስፈላጊነቱ ከምንም በላይ መሆኑን በመገንዘብ ነው— ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጥ የቻለው፡፡

መንግስት ለሀገራችን ሰላምና ልማት  እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ጽኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ምርጫው ነው። ለምን ቢሉ የሀገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን በፅናት ስለሚያምን ነው።

ታዲያ በሀገራችን በመካሄድ ላይ ያለው የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም የተጀመረው የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ዓላማን የሰነቀና ውጤቱም ለሀገራችንም ሆነ ለአካባቢያችን ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ መሆኑ የሚታበይ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ሀገራዊና አካባቢያዊ ሰላምን ከማስፈን አኳያ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡

በአካባቢያችንና በአህጉራችን ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ የመጣው የኢትዮጵያ መንግስት ስኬቶች መካከልም ረጅም ኪሎሜትሮችን የምትዋሰነን በጎረቤት ሀገር ሱዳን የተቀሰቀሰውን ቀውስ ለማርገብ የተካሄደው ጥረትና የተመዘገበው አበረታች ውጤት ተጠቃሽ ነው፡፡ ሱዳን በአፍሪካ ውስጥ በቆዳ ስፋቷ ቀዳሚ ሀገር ስትሆን ለጥ ያለና ውሃ ገብ የሆነው መልከዓ ምድሯ እንዲሁም ሰፊ የተፈጥሮ ሃብቷ ለታላቅ ዕድገት መብቃት የምትችል እንደሆነች ብዙዎቹን ያስማማ ሃቅ ቢሆንም ቅሉ፤ ሀገሪቱ ግን ለበርካታ ዓመታት በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ለመቆየት ተገዳለች። በዚህም ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ቀውስ ልትዳረግ በመቻሏ ለተቀሰቀሰው አለመረጋጋት እልባት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። በጐረቤት ሀገር ሱዳን የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋት እልባት ከመስጠት አኳያ የአንበሳውን ድርሻ ከተወጡት የአፍሪካ ቀንድ ሃገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት፡፡ በርግጥ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል ግጭት የተቀሰቀሰው ሀገሪቱ ነፃነቷን ከተጐናፀፈችበት እ.ኤ.አ. በ1956 ነበር። ይህ ሁኔታም በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ያደረሰው አሉታዊ ተፅእኖ ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ምንም እንኳን በሀገሪቱ ለደረሰው ቀውስ እልባት የመስጠት ተደጋጋሚ ሙከራዎች የተካሄዱ ቢሆንም አንዳቸውም ግን ለፍሬ መብቃት አልቻሉም፡፡ ይልቁንም የሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ በየጊዜው “ከድጡ ወደ ማጡ” እንዲሉት ዓይነት ሆኖ እየተባባሰ ሊሄድ ችሏል፡፡

ዳሩ ግን የኢትዮጵያ መንግስት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚነትና መልካም ግንኙነት መስፈን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተለይም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን መጠናቀቅ  ተከትሎ የሀገራቱ ግንኙነት እያደገ ከመምጣቱ ባሻገር የላቀ ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡

ዛሬ ላይም ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፤ የባህል ትስስር፤ የፀጥታና ደህንነትና ሌሎች ተግባራት በመከናወናቸው ጠንካራ ግንኙነት ተፈጥሯል፡፡ ለዚህም ነው በሁለቱ ሃገራት መካከል የመተማመን መንፈስ መፍጠር የተቻለውና የሱዳን መንግስትና ህዝብ ከኢትዮጵያ በላይ ችግሩን ሊፈታለት የሚችል ሃይል እንደሌለ በማመን በዳርፋር ለተከሰተው ቀውስ እልባት ለመስጠት የኢትዮጵያ መከላከያ የሰላም አስከባሪ ሃይል መሰማራትን ቀዳሚ ምርጫ ያደረገው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለው የውጭ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲ ውጤት በሆነውና በጥርጣሬ ከመተያየት ይልቅ መተማመንን የፈጠረው የመንግስት ጥረት የሱዳን መንግስት ላቀረበው ጥሪም ከ5ዐዐዐ በላይ ሠላም አስከባሪ ሃይሉን በመላክ ፈጣን ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ይህም የሱዳን ህዝብ በጐ እይታ እንዲኖረው ያደረገ ተግባር ነው::

ታዲያ እዚህ ላይ መንግስት በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ያደረገው ጥረት የሚመነጨው ሌሎች ሃይሎች እንደሚሉት ሳይሆን የጐረቤቶቻችን ሰላም ለሀገራቸን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን መፋጠን ካለው ፋይዳ አኳያ እንደሆነ ሊጤን ይገባል፡፡ ለምን ቢሉ እኛ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመዋጋት የምናደርገው ትግል ሊሳካ የሚችለው ጐረቤቶቻችን ሰላም ሲሆኑ በመሆኑ ነው። አዎ! የእነርሱ ሰላም መሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለእኛ ሰላም መጐልበት ያለው ሚና የላቀ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡

እርግጥም በሀገራችን ሰላም ላይ የቅርብ ተጽዕኖ ያላት የሱዳንን ችግር ለመቅረፍ በመንግስታችን የተካሄደው ጥረት ምንጩ ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሰላሟን ዘላቂ ለማድረግ ምንጊዜም ቢሆን ወሳኙ ነገር  በውስጥ የምታካሄደው የፀረ-ድህነትና ኋላ ቀርነት ትግል ሊሳካ የሚችለው ተጋላጭነታችን ሲወገድ ብቻ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በጐረቤቶቻችን ላይ የሚያጋጥም ትርምስንና ቀውስን መፈታት ካልተቻለ ጦሱ ለእኛም የሚተርፍ ስለሆነ ነው፡፡

እንደሚታወቀው በየትኛውም አካባቢ የሚኖር ችግር ዳፋው በአንድ ቦታ ላይ ሳይወሰን እንደ ሰደድ እሳት መስፋፋቱ አይቀሬ በመሆኑ “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ የራሳችንንና የአካባቢያችንን ህዝቦች ጥቅም ማዕከል በማድረግ የመደጋገፍ አቅጣጫን መከተል አስፈላጊነቱ የጐላ ነው። እናም ለዚህ ተግባራዊነትም መንግስታችን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ተፈላጊውን ሰላም በማስፈን ረገድ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

ከዚህ ነባራዊ ሃቅ በመነሳት በሱዳንና በደቡብ ሱዳን አማፅያን መካከል የተካሄደው ዘግናኝ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ትልቁን ድርሻ ለተጫወተው የኢትዮጵያ መንግስት ያላቸውን  ጠንካራ እምነት የገለፁበት ሁኔታ መፈጠሩን መመልከት እንችላለን። ይህም ለሀገራችን ታላቅ ድል ነው፡፡ ለነገሩ በሁለቱ ወገኖች መካከል የአብዬን ግዛት የይገባኛል ጥያቄ ለመፍታት በቅድሚያ የሰላም አስከባሪ ሃይል እንዲሰፍር በተወሰነበት ወቅት ብቸኛዋ አማራጫቸው ኢትዮጵያን ማድረጋቸው ይህን ዕውነታ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

እርግጥ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር፤ በአለም አቀፋ የሰላም ማስከበር  ተልዕኮ ታሪክ በብቸኝነት የተሳተፈች ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗና በሁለቱ ወገኖች በብቸኝነት ተመርጣ ተልዕኮውን የመወጣት አቅሟ በብዙዎች ዘንድ አመኔታን ማትረፍ ችላለች። አንዳንድ የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ሀገራት ይህን ተጨባጭ ሁኔታ ሊያጣጥሉት ቢሞክሩም፤ ሃቁን የሚያውቁት የደቡብ ሱዳንና የሱዳን መንግስታት ግን ሌላ ሰላም አስከባሪ ሀገርን ለመቀበል ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡ ይህም ሁለቱ ወገኖች ሃገራችን የምትከተለው በሰላም የመኖርና ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ያላትን ጽኑ እምነት በትክክል መገንዘባቸውንና አመኔታ መስጠታቸውን ለአለም አቀፋ ማህበረሰብ ማስገንዘብ የቻሉበትን ሁኔታን ፈጥሯል፡፡

የመንግስታችን ከጐረቤት ሃገሮች ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት የመፍጠር ጥረት በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሀገሪቱ ለጀመረችው የፈጣን ልማት ቀጣይነት መረጋገጥ ብቸኛው አማራጭ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ይህን መነሻ ታሳቢ ባደረገ መልኩም መንግስታችን ለሰላም ካለው ጽኑ አቋም በመነሳት ለዘመናት የእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ለቆየችው ጐረቤት ሀገር ሱዳን፣ በተለይ ደግሞ በቅርቡ ሰላሟ እየደፈረሰ ለምትገኘው ደቡብ ሱዳን  ሰላም መስፈን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ለዘመናት በአንድ ድርጅት ጥላ ስር ሆነው ለህዝባቸው ነጻነትና እኩል ተጠቃሚነት ሲታገሉ ቆይተው፣ የናፈቁትን ሰላምና ልማት ማጣጣም የጀመሩት የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ድርጅታቸው “ኤስ ፒ ኤል ኤ ”ዳግም ወደ እርስ በርሰ ጦርነት በመግባቱ ለከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጥፋት መዳረጋቸው ወቅታዊው ዕውነታ ነው፡፡

እርግጥ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ወቅታዊ ችግር የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ መሳብ ቢችልም እልባት ከመስጠት አንፃር ግን የኢፌዲሪ መንግስትና ኢጋድን ያህል የተንቀሳቀሰ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ሁላችንም እንደምንገነዘበው የዓለማችን አዲስ ሀገር በሆነችው ደቡብ ሱዳን የተከሰተው ቀውስ የአደጋው ተጋላጭ የሚያደርገው በዋነኝነት የሀገሪቱን ዜጎች መሆኑን እስካሁን ከደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ መገንዘቡ ከበቂ በላይ ማሳያ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ዳፋው ለአካባቢው ሀገራት መትረፉ አይቀሬ ነው፡፡

ኢጋድና የኢፌዲሪ መንግስት የደህንነት መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ ሀገራዊ ህልውናን ማረጋገጥ ብቻ እንደሆነ በማመን፣ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ቀውስ እልባት ለመስጠት ቁርጠኝነታቸውን በተግባር የማስመስከር እንቅስቃሴያቸውን በመጀመር ግምባር ቀደም ሚናቸውን በመጫወት ላይ የሚገኙትም ለዚህ ነው፡፡

ቀጣናዊው ድርጅት ኢጋድና የኢትዮጵያ መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ እልባት ለመስጠት በፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲትና ምክትላቸው በነበሩት ሪክ ማቻር የሚመሩት ተቀናቃኞች ተኩስ እንዲያቆሙና ወደ ድርድር እንዲመጡ ቀነ ገደብ እስከ ማስቀመጥ ደርሷል፡፡ አደራዳሪ ልዑክ በማቋቋምም በጁባ፣ በናይሮቢና በአዲስ አበባ የሰላም መፍትሄ የማፈላለግ ጥረት አድርገዋል፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት በበኩሉ ይህን ቀውስ ለመፍታትና ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ቁርጠኝነቱን በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የተመራ ልዑክ አማካኝነት በሀገሪቱ ርዕሰ ከተማ ጁባ በመገኘት ገልጿል። ወንድማዊነቱን አስመስክሯል። በዚህም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር ውይይት ከማድረጋቸው ባሻገር በእስር ላይ የሚገኙ ባለስልጣናት ደህንነትንም መታዘብ ችለዋል።

በርግጥ ሃገራችን ለአካባቢው ሰላም መስፈን የምታደርገው ጥረት ከውጭና ደህንነት ፖሊሲዋ የሚመነጭ መሆኑን በተደጋጋሚ ለመጠቆም ተሞክሯል። በመሆኑም ይህ ከሰላም ወዳድነት የሚመነጨው ጥረት እንደ ከአሁን በፊቱ ሁሉ ለፍሬ የሚበቃበትን መንገድ በመጠቀም ሁለቱ ወገኖች ወደ ሰላማዊ ድርድር የመጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

የደቡብ ሱዳን መንግስትም ይሁን ተቃዋሚዎች በሃገራችንና በኢጋድ ለቀረበው የሰላም ጥሪ ተወካዮቻቸውን ወደ አዲስ አበባ በመላክ በጎ ምላሽ መስጠት ችለዋል። የሰላም ድርድሩ መቋጫ ላይ ባይደርስም፣ ጅምሩ ግን ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ነው የሚነገረው።

በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ወገኖች መካከል እየተካሄደ የሚገኘው የሰላም ድርድር በስኬት እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ነው። በተለይም ኢጋድ በአደራዳሪነት የመደባቸው የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን ያላቸውን የካበተ ዲፕሎማሲያዊ ልምድ ተጠቅመው ድርድሩን ለፍሬ እንደሚያበቁት የብዙዎች እምነት ነው።

እርግጥ ሁለቱ ወገኖች ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት በመዲናችን አዲስ አበባ በተቀመጡበት በአሁኑ ወቅት የእርስ በርስ ጦርነቱ ተጠናክሮ መቀጠሉ የኢትዮጵያ መንግስትን ማሳሰቡ አልቀረም። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ መንግስት ሁለቱም ወገኖች የራሳቸውን ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ፤ ለሀገራቸውና ህዝባቸው ህልውና ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው በተደጋጋሚ በማስገንዘብ ላይ የሚገኘው።

እንደሚታወቀው በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ቀውስ በዋናነት በሀገሪቱ ዜጎች ላይ ለከፍተኛ አደጋ የጋረጠ ቢሆንም፤ በአካባቢውና በሀገራችን ሰላምና ልማትም ያለው አሉታዊ ጫናም ቀላል የሚባል አይሆንም። ምክንያቱም ጦርነቱን ሸሽተው ወደ ጎረቤት ሀገሮች በመሰደድ ላይ ያሉ ደቡብ ሱዳንያውያን ቁጥር እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ነው።

እርግጥ በአህጉራችንና በአካባቢያችን ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ የሚገኘው የኢፌዴሪ መንግስት፤ በጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰውን ቀውስ የማርገብ ጥረት አበረታች ውጤት እንደሚያስመዘግብ የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የሀገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው ቀናዒ አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑንን በፅናት ስለሚያምን ነው፡፡

ከዚህ አኳያም በሶማሊያ ያደረጋቸው ተጋድሎዎችና እያከናወነ ያለው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሌላኛው ተጠቃሽ ነው። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ህዝቦች የዕድገት ተስፋ ከሠላም፣ ከልማትና ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ብቻ ነው፡፡ እናም ለዘመናት የህዝባችንን አንገት ያሰደፋውን ድህነት አቸንፈን ለድል ለመብቃት እየተደረገ ባለው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ትልቁ ፈተና ሊሆን የሚችለው የአካባቢያችን ቀጣና ያለመረጋጋት ችግር አንዱ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከአካባቢያችን ሀገራት የሚመነጨው የሽብርተኝነት አደጋ መጥቀሱ ተገቢ ይሆናል።እርግጥም ይህ አደጋ ለእኛ ብቻ ሳይሆን፣ በክፍለ-አህጉሩ አካባቢ ለሚገኙ እንዲሁም ለሌሎች ሀገራት ጭምር ምን ያህል አስጊና አስከፊ እንደሆነ በተጨባጭ በዓይናችን እያየን ያለነው ዕውነታ ነው፡፡

ታዲያ እውነቱ ይህ ከሆነ ዘንዳ፤ የአካባቢያችን ሁኔታ ምን ጊዜም በትኩረት በመከታተል በአንድ በኩል በጎ ተጽዕኖዎችን ለማስፋፋትና ለማጎልበት፣ በሌላው በኩል ደግሞ ጎጂ ተፅዕኖዎችን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘን መረባረቡ ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በመሆኑም የሰላም ዲፕሎማሲያችን አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ እንዲል የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ ይሻል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy