NEWS

የስድስት ወሯ ነፍሰ ጡር በሠራተኛዋ ተገደለች

By Admin

April 15, 2017

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ የነበረችውና የስድስት ወራት  ነፍሰጡር መሆኗ የተገለጸው የ29 ዓመት ወጣት ወ/ሮ ሔዋን ሳህሌ፣ በሠራተኛዋ በደረሰባት ድብደባ ተገደለች፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ደሳለኝ ሆቴል አካባቢ ነዋሪ የነበረችው ወ/ሮ ሔዋን ትዳር ከመሠረተች ስድስት ወራት እንደሆናትና የስድስት ወራት ነፍሰጡር መሆኗን የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በተጠርጣሪ ሠራተኛዋ ተደብድባ ግድያ የተፈጸመባት መጋቢት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ከምሽቱ 12 ሰዓት አካባቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሠራተኛዋ የግጭታቸውን ምክንያት ገና በግልጽ ባትናገርም፣ ‹‹ተጋጨንና ገደልኳት›› በማለት በቁጥጥር ሥር በዋለችበት ወቅት ለፖሊስ መናገሯን በሥፍራው የነበሩ ሰዎች ተናግረዋል፡፡

ሠራተኛዋ ለቤት ውስጥ ማሞቂያ (ቺሚኒ) የተዘጋጀ ፍልጥ እንጨት በማንሳት፣ የሟችን ጭንቅላት ደጋግማ በመምታት ሕይወቷ እንዲያልፍ ካደረገች በኋላ በግቢው ውስጥ በሚገኝ ጢሻ ነገር ውስጥ የደበቀቻት ቢሆንም፣ አስከሬኗ በፖሊሶች ፍለጋ ወዲያው ሊገኝ ችሏል፡፡

ሠራተኛዋ ድርጊቱን እሷ እንዳልፈጸመች ለማስመሰል ያልታወቁ ሰዎች ግቢ  ገብተው እሷን ካፈኗት በኋላ ሟችን ይዘዋት እንደሄዱ ለመናገር ብትሞክርም፣ ፖሊሶች ግቢውንና ቤቱን ሲፈትሹ በቀላሉ ሊያገኟት እንደቻሉ ታውቋል፡፡ ግድያው በተፈጸመበት ወቅት የሟች ባለቤት ከቀድሞ ባለቤቱ የወለደው የ13 ዓመት ልጅ በቤት ውስጥ የነበረ ቢሆንም፣ እየተጫወተ ስለነበር ድርጊቱን እንዳልሰማም ተጠቁሟል፡፡

ልጁ የሆነውን በወቅቱ አውቆ ቢሆን ኖሮ፣ ምናልባትም ድርጊቱ እሱም ላይ ሊፈጸም ይችል እንደነበር የገመቱም አሉ፡፡ የወ/ሮ ሔዋን የቀብር ሥነ ሥርዓት ቅዳሜ መጋቢት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በጴጥሮስ ወጳውሎስ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች መካነ መቃብር መፈጸሙም ታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ሳምንት ውስጥ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ የባንክ ሠራተኞች የኅብረት ማኅበር በሚባለው አካባቢ፣ የ50 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አቶ ተወልደ ገብረአምላክና ሠራተኛቸው ትህትና ውብሸት በቤታቸው ውስጥ በስለት ታርደው መገኘታቸው ታውቋል፡፡

አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኛ የነበሩና ባሁኑ ጊዜ ጡረተኛ እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ግድያውን የፈጸመባቸው አብሯቸው የሚኖር የ35 ዓመት ዘመዳቸው መሆኑ ታውቋል፡፡ ወጣቱ ግድያውን ፈጽሞ በቤት ውስጥ የነበሩ ጌጣጌጥና ሞባይሎች ይዞ መሰወሩም ተገልጿል፡፡ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለመያዝ ፍለጋውን አጠናክሮ መቀጠሉም ታውቋል፡፡ reporte