NEWS

የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተመረጡ የቱሪዝም መስኮች ሊሰማሩ ነው

By Admin

April 27, 2017

የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ ባለሃብቶች በኢትጵያ በተመረጡ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ለመስራት ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ተወያይተዋል፡፡

ባለሃብቶቹ በዋናነት በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ለመሰማራት ባላቸዉ ፍላጎት ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ቢሆንም፥ በሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይም ሰፊ ውይይት ከሚኒስቴሩ ጋር አድርጓል።

የትግራዩ አልነጃሽ መስጊድ፤ የሰሜንና ባሌ ተራሮች፤ ሃረሪና አዲስ አበባ ለልኡኩ ከቀረቡ የተመረጡ ስፍራዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልቃድር ርዝቁ እንዳሉት፥ ባለሃብቶቹ በቱሪዝም ዘርፉ የካበተ ልምድ ካለው ሃገር የመጡ ናቸዉ።

ይህንን ተሞክሮ ወደ ሃገራችን በማምጣት በዘርፉ ያለውን የቱሪስት ቁጥር ለማሳደግ፣ ለዜጎች የስራ እድልን ለማስፋትና የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግ ባለሃብቶቹ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ እየሰራን ነው ብለዋል።

አንድ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ባለ ሃብት በአዲስ አበባ ከተማ በሆቴል ግንባታ ስራ ላይ መሰማራቱንም አምባሳደሩ ጨምረው ተናግረዋል።