Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለምን ተራዘመ?

0 283

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለምን ተራዘመ? (ቶሎሳ ኡርጌሳ)

የኢፌዴሪ መንግስት የዛሬ ስድስት ወር ገደማ በአንዳንድ የአማራና የኦሮሚያ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከት መቀልበስ እንዲቻል በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 መሰረት የአስቸኳይ አዋጅ ማወጁ የሚዘነጋ አይደለም። በወቅቱ አዋጁ ሲታወጅ በእነዚህ አካባቢዎች ለተወሰኑ ጊዜያት በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ በተለመደው የህግ ማስከበር ስርዓት መቀልበስ አልተቻለም ነበር። እናም ሁከትና ብጥብጡ ለማስቀረት እንዲሁም ሰላምንና ፀጥታን ለማስፈን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት አዋጁ ገቢራዊ እንዲሆን አድርጎ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተፈፃሚ ሆኗል።

ሰሞኑን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባም አዋጁ ለለቀጣዩቹ አራት ወራት እንዲራዘም በሙሉ ድምፅ ወስኗል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ተገኝተው አፈፃፀሙን በተመለከተ ሪፖርትም አቅርበዋል። ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው የተለያዩ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል።

ታዲያ በእለቱም ይሁን ከዚያን ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ወገኖች በተለይም ፅንፈኛው ዲያስፖራ የመራዘሙን ምክንያት ገልብጠው በመመልከት እንዲሁም ከጭፍን ጥላቻ በመነሳትና ለዚህ ሀገር ህዝብ ያሰቡ ይመስል ተቆርቋሪ በመሆን ‘አዋጁ ለምን ይራዘማል?’ ሲሉ ይደመጣሉ። እናም በእኔ እምነት ለእነዚህ ወገኖች በቂ ምላሽ መስጠት የሚገባ ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ሁከት የህዝቡ ድጋፍ ባልተለየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አማካኝነት መቆጣጠር ተችሏል። በዚህም በተለይም በኦሮሚያና በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ያመራ የነበረው ሁከት በበቂ ሁኔታ እንዲገታ ተደርጓል።

ለዚህም በዋነኛነት የሰላሙ ዋስና ጠባቂ የሆነው የሀገራችን ሰላም ወዳድ ህዝብ የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል። በየአካባቢው የሚገኙ የታጠቁ ሃይሎችን በመምከር፣ ከሁከት የሚገኝ ምንም ዓይነት ጥቅም እንደማይኖር በማስተማር ከፍ ሲልም በኮማንድ ፖስቱ አማካኝነት የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ የሰላም ቀናዒነቱን አሳይቷል። በዚህም ሳቢያ በሁከቱ ዋነኛ ተዋናይ የነበረውን ወጣቱን ሃይል ወደ ልማትና ወደ ተጠቃሚነት ፊቱን እንዲያዞር ማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ በህዝቡ ያልተቋረጠ ክትትልና ከመንግስት ጋር ችግሩን ለመፍታት በተደረገ ርብርብ ውጤት ተገኝቷል።

ይህ ሁኔታም ዛሬ ላይ ወጣቱ መንግስት ባመቻቸለት የስራ ሁኔታ ወደ ስራ እንዲገባ ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል። በተለይም መንግስት የመደበው የ10 ቢሊዩን ተዘዋዋሪ ፈንድን ለመጠቀምና የየክልሉ መንግስታትም በዚሁ ላይ ያደረጉትን ድጎማ አክሎ በመሉ መንፈስ ወደ ስራ እንዲገባ ከፍተኛ ፍላጎት አሳይቷል—ወጣቱ። በዚህም በተለያዩ የመልካም አስተዳደርና የስራ አጥነት ምክንያት ተስፋ አጥቶ የነበረው ወጣት ተስፋን አሻግሮ ከመመልከት ባለፈ፤ ለዚህች ሀገር ዕድገት ያለው ተስፋ ራሱ መሆኑን በማመን ቀደም ሲል በማወቅም ይሆን ባለማወቅ ያከናወናቸው ተግባራት ተገቢ አለመሆኑን ሲናገር አድምጠናል።

ወጣቱ እንደ ጃዋር መሐመድና የፅንፈኛው ዲያስፖራ ሚዲያዎች ዓይነት የዚህን ሀገር ሰላም ለማናጋት ይሰሩት የነበረውን ሴራ ዓይኑን ገልጦ መመልከት ችሏል። እናም ዛሬ ወጣቱ ለስራ የተነሳሱ ትኩስ ክንዶቹን በማስተባበር በዚህች ሀገር የልማት ግስጋሴ ውስጥ የበኩሉን አሻራ ለማሳረፍ እየተንቀሳቀሰ ነው። እርግጥ ይህ ሁኔታ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የኢትዮጵያን ሰላም የማይሹ ሀገሮች ሊያናድዳቸውና የትናንቱ ሁከት ዛሬም ተመልሶ እንዲመጣ የሚሺ ወገኖች የአዋጁ መራዘም ሊያበሳጫቸው ይችላል። ዳሩ ግን ወሳኞቹ የሀገራችን ህዝቦች እንጂ እነርሱ ባለመሆናቸው የሚሰማቸው አካል የለም።   

አዋጁ ገና ገቢራዊ ሲሆን እንደተገለፀው አዋጁ ሊነሳ የሚችለው ለአዋጁ መውጣት ምክንያት የሆኑ ጉዳዩች ሙሉ ለሙሉ በአስተማማኝ ሁኔታ ሲቀለበሱ መሆኑ ተገልጿል። እኔ እሰከሚገባኝ ድረስ ይህ ማለት የሀገራችንን ፀጥታ ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀድሞው ሁኔታ ካልተመለሰ አዋጁ አይነሳም ማለት ነው። ሰላምና ፀጥታው ሙሉ ለሙሉ መመለሱን የሚያውቀው ደግሞ ይህን ጉዳይ በበላይነት የሚመራው ኮማንድ ፖስቱና የአዋጁን አፈፃፀም የሚከታተለው መርማሪ ቦርዱ ናቸው።

የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ሰብሳቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ለፓርላማ እንዳስታወቁት፤ ኮማንድ ፖስቱ ባደረገው ግምገማ የተፈጠረውን ችግር ደረጃ በደረጃ በመፍታት ወደ መደበኛው የህግ ማስከበር የአሠራር ሥርዓት የሚያሸጋግር ሁኔታ በመፈጠሩ በአዋጁ መመሪያ ላይ ማሻሻሎች ተደርገዋልአብዛኛዎቹ ጉዳዩች እንደተጠበቁ ሆነው። ሆኖም ሁነኛ የሰላምና መረጋጋት መሻሻል እዚህ ሀገር ውስጥ ቢፈጠርም፤ አሁንም በተወሰኑ የሀገራችን አካባቢዎች ከኮማንድ ፖስቱ ጋር በጥምረት ለከናወኑ የሚገባቸው ክስተቶች መኖራቸው አልቀረም። የኮማንድ ፖስቱን ጣልቃ ገብነት የሚጠይቁ ክስተቶች በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች አሁንም ይስተዋላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ እንደገለፁት ከእነዚህ ክስተቶች ውስጥ፤ በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩ ግጭቶች፣ በአውራ ጎዳናዎች መኪና አስቁሞ መዝረፍና መስታወቶች የመስበር፣ በጥቂት ቦታዎችም ቢሆን በትምህርት ተቋማት ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስተጓጎልና ረብሻ ለመፍጠር የመሞከር፣ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በግለሰቦችና ድርጅቶች ቅጥር ጊቢ ውስጥ የሚፈነዱ መሳሪያዎች የመወርወር ጉዳዮች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ አዋጁ እንዲተገበር ያደረጉት ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ ያለመቀረፋቸውን የሚያሳዩ ናቸው።

ከዚህ በላይም መንግስት በህዝቡ ውስጥ ባደረገው ጥናት፤ 82 በመቶ የሚሆነው የጥናቱ አካል ህዝብ አዋጁ ለአንድ ጊዜ መራዘም ቢችል ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ እንደሚቻል እምነት እንዳለው ተገልጿል። ለዚህም ነው—ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝቡ ጋር ተጨማሪ ውይይቶችን በማካሄድ እነዚህን ብቅ ጥልም የሚሉ ችግሮችን በበቂ ሁኔታ ማምከን እንደሚገባ ለፓርላማው የገለፁት።    

ይህን ሁኔታም የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ሲራጅ ፈጌሳ ከመሰንበቻው ፓርላማ ተገኝተው አፅንኦት ሰጥተው አብራርተውታል። እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የሚነሱ ችግሮችን ለመጠቀም የሚፈልጉ ፀረ ሰላም ሃይሎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው፣ በሁከት እና ብጥብጡ ቀንደኛ መሪዎች ከነበሩት ውስጥ አብዛኛዎቹ ቢያዙም ቀሪ በመኖራቸው እንዲሁም በወረቀት ፅሁፎችን በመበተን አሁንም ሰላም እና መረጋጋትን ለማደፍረስ የሚጥሩ ወገኖች አልፎ…አልፎ በመታየታቸው አዋጁን ማራዘም አስፈላጊ እንዲሆን አድርጎታል። ከዚህ በተጨማሪም የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ሙሉ ለሙሉ እውን ለማድረግና ሰላማችን ዳግም የማይቀለበስበት ደረጃ እንዲደርስ አዋጁ እንዲራዘም ምክንያት ሆነዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩም ይሁን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት የአቶ ሲራጅ ፈጌሳ ሃሳብም፤ በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 መሰረት በገለልተኝነት በተዋቀረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድም የተደገፈ ነው። ቦርዱም በመላ ሀገሪቱ ያደረገውን ቅኝት መሰረት አድርጎ አዋጁ ቢራዘም ተገቢ ይሆናል የሚል አስተያየት አቅርቧል። ምክር ቤቱም የቦርዱን ሃሳብ ተንተርሶ አዋጁ ለቀጣዩቹ አራት ወራት እንዲራዘም ፈቅዷል።

እንግዲህ መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ይኸው ነው። አሁንም ለአዋጁ ምክንያት የሆኑት ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ እሰካልተወገዱ ድረስ፤ የአዋጁን ‘ልምን ይራዘማል?’ ብሎ መጠየቅ፤ የዚህን ሀገርና ህዝብ ሰላም አለመመኘት ነው። ሀገራችንንና ህዝቦቿ የጀመሩትን የዕድገት ጎዳና የማደናቀፍ ጥረትም ጭምር ይመስለኛል። እናም አዋጁ የሚቀጥለው አንድም በህዝቡ ፍላጎት፣ ሁለትም የተገኘው ሰላምና መረጋጋት የማይቀለበስበት ደረጃ ደርሶ ወደ ነበርንበት የቀድሞ ሁኔታ በአስተማማኝ ደረጃ እንድንደርስ ነው።   

ከዚህ ውጪ በአዋጁ የመራዘም ሁኔታ የተለያዩ ስሞች እየሰጡ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ አለመገንዘብ የህዝብን መብት አለማክበርና መብቱንም ‘በእኛ እናውቅልሃለን’ ዲስኩር ለመቀማት የመሻት ፍላጎት ከመሆን አይዘልም። ያም ሆነ ይህ፤ አዋጁ በተራዘመባቸው አራት ወራት ውስጥ ለሚከናወኑ ማናቸውም ህዝቡ እንደ ትናንቱ ዛሬም ዝግጁ መሆኑን እነዚህ ወገኖች ማወቅ ይኖርባቸዋል። በእነዚህ ወራቶች ውስጥም ከመንግስት ጋር ተገቢውን ውይይት በማድረግ ለአዋጁ መውጣት አነሳሽ የሆኑ ጉዳዩች ሙሉ ለሙሉ እንዲወገዱ እንደሚያደርግም አይቀሬ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy