Artcles

የአንድነታችንንና የትብብራችን ማሳያ ፕሮጀክት

By Admin

April 11, 2017

የአንድነታችንንና የትብብራችን ማሳያ ፕሮጀክት

ታዬ ከበደ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ የሚያመነጭ ፕሮጀክት አይደለም። ከሁኩ በላይ የሀገራችን ህዝቦች ለአንድ ዓላማ በጋራ ተሰልፈው በጋራ ክንዳቸው ሁሉንም ጉዳዩች ሊፈፅሙ እንደሚችሉ የትብብራቸው ማሳያ ነው። መቻላቸውን ለዓለም ያሳዩበት ፕሮጀክትም ጭምር ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ የሚገኘው በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ ተመስርቶ ነው። በዚህም ሳቢያ ግድቡ ቀደምት የተመፅዋችነት አስተሳሰብን የቀረፈ፣ ለፀረ- ድህነት ትግሉ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ፣ የ“ይቻላል” መንፈስን መፍጠር የቻለና ከራሳችን አልፈን ለጎረቤቶቻችን እንድንተርፍ የሚያደርገን ነው። እናም ቢያንስ በእነዚህ ሁኔታዎች ብቻ የሀገራችንን ፍትሐዊና “ኑ አብረን እንጠቀም” የሚል ቀና አስተሳሰብን ለመገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም፤ ለየትኛውም ወገን ቢሆን።

ምንም እንኳን ትናንት ሐብትን በጋራና በፍትሐዊ ሁኔታ የመጠቀም መርህን ተከትላ የህዳሴውን ግድብ በመገንባት ላይ የምትገኘው ሀገራችን፤ ዛሬም ከዚህ መርህዋ ዝንፍ የምትል አይሆንም። ግድቡም ወንድም የሆነውን የግብፅ ህዝብ እንደማይጎዳ፣ ይልቁንም ከግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ እንደሚሆን በፅናት ታምናለች። ይህ እምነቷ ከምንም ተነስቶ የሚባል አይደለም—መሬት ላይ ያለውን የግድቡን ግንባታ መሰረት ያደረገ እንጂ። ከዚህ በመነሳትም እምነቷንና የትኛውንም ወገን ያለመጉዳት መርህዋን በተለያዩ ወቅቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መንግስታትና ህዝቦች አስረድታለች። በሰፊ የዲፕሎማሲ ጥረቷም ግንዛቤም ማስያዝ ችላለች።

እርግጥ ፕሮጀክቱ የሀገራችን ህዝቦች ድህነትን ድል ለመንሳትና ወደ ህዳሴያቸው ማማ ለመንደርደር ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት አንድ ማሳያ ነው። የትልቅነት መንፈስንና አስተሳሰብን እንድንሰንቅ ያደረገን የኩራት ካባችን ነው ማለትም ይቻላል። ይህ የትልቅነት መንፈስ በጋራና በአብሮነት የምናድግበትን መስመር የሚያሳይ እንጂ እንደ ደሴት ለብቻችን ከዓለም ተነጥለን የምንኖርበት ከእንግዲህ በሩ ተከርችሞ የተዘጋ መሆኑን የምናሳይበት ነው። የዓለም ህዝብም ይህን ታላቅ ስራችንን እንዲገነዘብና ተዘግባሩ የዘመናችን ትውልድ ትሩፋት መሆኑን እንዲያውቅ የምናደርግበት ነው። ፕሮጀክቱ ድህነትን በታሪክነት የመሰናበታችን አንድ መንገድ መሆኑን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ ከቴክኖሎጂ ጥገኝነትም በመላቀቅ የራሳችንን አቅም የምንፈጥርበት ይሆናል።

የግድቡ ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ እንደመሆኑ መጠን፤ ለአንድም ሰከንድ ቢሆን አይቋረጥም። ግድቡ ገና በተበሰረበት ወቅት በዜጎች ውስጥ ከፍተኛ ተነሳሽነት፣ እልህና ወኔ ተፈጥሯል፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውንና ሙያቸውን ለግድቡ ግንባታ ለማበርከት ቁርጠኛ አቋም ይዘው ዘልቀዋል፡፡ ሕዝቡ በፈጠረው ብሔራዊ መግባባት፤ ከድህነት አረንቋ ለመላቀቀ ወኔውን ሰንቆ በራሱ ተነሳሽነት ቦንድ በመግዛትና ከደመወዙ በማዋጣት በፍፁም ኢትዮጵያዊ ስሜት ከዳር እስከ ዳር እየተነቃነቀ ነው፡፡

በመሆኑም ህዝቡ ቃሉን በየጊዜው እያደሰ ግድቡ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ዛሬም ድረስ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ከጨለማ ውስጥ ወጥቶ በጭላንጭል ብርሃን ውስጥም ቢሆን መመልከት ያስፈልጋል። የግድቡ ሁሉም ነገር አከናዋኞች እኛው ሆነን ሳለ የሚቋረጥበት አንዳችም ምክንያት የለም። መቼም ቢሆን። የአንድነታችንንና የትብብራችን ማሳያ በመሆኑም መቼም ሊቆም አይችልም።

ያም ሆኖ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህልውና ጉዳይነቱ የዜጎችንና የሀገራችንን ዕድገት በማፋጠን ብቻ የተወሰነ አይደለም—የጎረቤቶቻችንን ተጠቃሚነት በማሳደግ የሰላማችን ዋስትናም ጭምር እንጂ፡፡ እናም ግድቡ ከከፍተኛ የኤሌትሪክ ሃይል እጥረት ለሚሰቃዩት እንደ እነ ኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ለመሳሰሉ ጎረቤቶቻችን ለችግራቸው ምላሽ የሚሰጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩተን የሚያሳድግ፣ ግንኙነታችንንም የማጠናከር ሚናው በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የግድቡ ግንባታ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር ለአካባቢው ሠላምና መረጋጋት የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡

እንደሚታወቀው የዘመናት የድህነት ታሪካችንን ለመቀየርና ከተጫነን ድህነት ለመውጣት በምናደርገው ትግል ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው የኢፌዴሪ መንግስት በግድቡ ግንባታ ስፍራ ላይ የመሰረት ድንጋይ ካኖረበት ሰዓት ጀምሮ፤ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለ አንዳች ልዩነት ስኬታማነቱን ዕውን ለማድረግና በራሳችን ተነሳሽነት ማናቸውንም ጉዳዮች ለመከወን ቃል ገብተናል፡፡ በዚህም ሁሉም የሀገራችን ህዝብ የዘመናት ቁጭትና ብሔራዊ ሀብቱ የሆነውን የዓባይ ወንዝን የመጠቀም ምኞትና ፍላጎት በአዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት ተደርጓል፡፡

በህዝቦች የማይነጥፈና ሙሉ ተሳትፎ የሚገነባው እንዲሁም የዜጎች ሀብት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሳችን ገንዘብና ተሳትፎ የሚገነባ ብቸኛው የዓለማችን ፕሮጀክት ለመሆን በቅቷል፡፡ ዜጎች ከዕለት ምግባቸው ቀንሰው የሚገነቡትና እንደ አይናቸው ብሌን የሚንከባከቡት ግድብ መሆኑም ታሪካዊነቱ የትየሌለ ነው፡፡ እርግጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በብሔራዊ መግባባት መንፈስ ግድቡን ካለአንዳች ልዩነት በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ለመገንባት ሲነሱ ተርፏቸው አይደለም— በድህነት አለንጋ መገረፉ ማብቃት እንዳለበት በማመናቸው እንጂ፡፡ አዎ! ለስኬታማነቱ ህዝባዊ ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ ሲነሱም የማንንም ጉትጎታ ያለመሻታቸው ለድህነት ካላቸው ከፍተኛ ጥላቻ የመነጨ መሆኑም ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡

ህዝቡ ግድቡን ዕውን የማድረግ ህዝባዊ ስሜት ዛሬ ላይ ባለበት የግለት መንፈስ ውስጥ ይገኛል። በመሆኑም በእኔ እምነት ህዝቡ ዛሬም ተግባሩን በብቃት እንዲወጣ ቀስቃሽ የሚያስፈልገው አይመስለኝም—ስለ ግድቡ ያለውን ዕውነታ በሚገባ ይገነዘባልና። ስለሆነም የህዳሴው ግድብ የሚገነባው በህዝቦች ተሳትፎ እንደ መሆኑ መጠን የሚያወዛግቡ ጉዳዩችን ወደ ጎን በማለት ለግድቡ ዕውን መሆን አሁን ካለው በበለጠ ሁኔታ መረባረብ ይኖርበታል።

እንደ ህዝብ ስራችንን መስራት ይኖርብናል። እኛ ኢትዮጵያዊያን በታሪካችን የየትኛውንም ሀገር መብት የማንጋፋ ከህዝቦች ጋር ተባብረን የምንኖር ነን። ይህ ህዝባዊ እምነታችን በመንግስታችን ፍትሐዊነትን ዕውን በሚያደርጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የታጀበ ነው። ዋነኛው ጠላታችን ድህነት ነው። ግድቡን የምንገነባው ይህን ጠላታችንን ድል ለመንሳት እንጂ የትኛውንምወገን ለመጉዳት አይደለም።

ከዘመናት በፊት ያለፈው ትውልድ ለእኛ አወርሶን የሄዱው የአክሱምና የላሊበላ ስልጣኔ- ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ጥበብ በመሆኑ በኩራት ለቱሪስት መስህብነት እየተጠቀምንበት ያን ትውልድ እያስታወስነው ነው፡፡ የእኛው ትውልድም ይህን ታላቅ የልማት ፕሮጀክት ዕውን አድርጎ ለቀጣዩ ትውልድ ለማውረስ በአዲስ ምዕራፍ ደማቅ የዕድገት ታሪክ ለመፃፍ ሌት ተቀን እየሰራ ነው። ይህም ለመጪው ትውልድ ልማትንና ብልፅግናን እንጂ ልመናን ያለማውረስ ራዕይን የሰነቀ ነው፡፡ የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ጀምሮ መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት በመነሳሳት ለግንባታው አጋርነታቸውን መግለፃቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ይህን ለማደግ ያላቸውን ፍላጎትንና መልካም ተግባራቸውን አሁንም በልበ ሙሉ አጠናክረው እየቀጠሉ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱ የአንድነታችንና የትብብራችን ማሳያ በመዸሆኑም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡