Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የ“አፍሪካዊቷ ሰሜን ኮሪያ” ሳልሳዊ ማዕቀብ

0 779

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የ“አፍሪካዊቷ ሰሜን ኮሪያ” ሳልሳዊ ማዕቀብ
ቶሎሳ ኡርጌሳ
በአንድ ሰው የምትመራው ኤርትራ ማዕቀብ የሚደንቃት አይደለችም። በማዕቀብ ላይ ማዕቀብ ቢደራረብ በአቶ ኢሳይያስ ለሚራው “ህግደፍ” (ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ) /ይህ ስያሜው ከተግባራዊ ማንነቱ ጋር አብሮ / ጉዳዩ አይደለም። ትናንት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከአንዴም ሁለቴ ማዕቀብ ቢጥልበትም፤ የአቶ ኢሳይያስ ሻዕቢያ ግን በዓለም አቀፍ ውድድር ተወዳድሮ ያገኘው “እፁብ ድንቅ ሜዳሊያ” ይመስል ማዕቀቡን አንገቱ ላይ አንጠልጥሎ በኩራት ይንጎራደዳል። እናም እንደ ህፃን ልጅ አታድርግ የተባለውን እያደረገ ሲያሻው የጎረቤት ሀገሮች አሸባሪዎችንና ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ያሰለጥናል፣ ያስታጥቃል፣ ሀገራቱን እንዲያውኩም አስርጎ ለማስገባት ይጥራል። በል ሲለው ደግሞ የጦር መሳሪያዎችን ለአሸባሪዎች ያቀብላል፣ በላሸቀ ኢኮኖሚው የጦር ቁሳቁሶችን በመሸመት የጦረኝነት አባዜውን እየተወጣ ይኸው ዛሬም ድረስ ያለ አንዳች “ተው” ባይ ያሻውን ይፈፅማል።

ታዲያ አንዳንዴ እነዚህን የአስመራውን አስተዳደር ነገረ-ስራዎች በአንንክሮ ስታዘባቸው፤ ለይስሙላም ቢሆን “ታግዬለታለሁ” ከሚለው “ህዝባዊ አስተሳሰቡ” ያፈነገጡ ብቻ ሆነው አላገኛቸውም። ከዚህ ይልቅ በማዕቀብ ውስጥ ተወልዶ ያደገ ይሆንብኛል— ምነም እንኳን ሻዕቢያ እንዲህ ዓይነቱን ያፈነገጠ ባህሪ ያዳበረውና አጎልምሶ ወደ አስመራ ይዞት የገባው ዛሬ እንደ ዳዊት እየደጋገመ የሚያወሳው ትግሉ፣ ነገር ግን የትግሉ ፍሬ ወንድም ለሆነው የኤርትራ ህዝብ ከስቃይ በስተቀር ጠብ ያላደረገለት፣ ግን ደግሞ ነገር ዓለሙን ትቶት እንዳሻው የሚሆንበትን ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት እጅግ የሚበዛውን ዕድሜ ካሳለፈባቸው ከሳህል ተራራዎች ቆይታው ወቅት ልቅም አድርጎ የተማራቸው መሆኑን ባውቅም። እናም ያኔ በሳህል ተራራዎች ቆይታው ወቅት ሲጠቀምባቸው የነበሩት “የጫካ ህጎች” ዛሬም የሚሰራ እየመሰለው ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ሊያዳምጠው አይፈልግም።
ሻዕቢያ ባለፉት ጊዜያት የመሳሪያ ግዥንና የባለስልጣኖችን ዝውውር እንዲሁም በውጭ ከሚገኙት ዜጎቹ ላይ በግዳጅ የሚቆርጠው የሁለት በመቶ ቀረጥ ክልከላን ሁሌም እንደተላለፈ ነው። ሆኖም የኤርትራንና የሶማሊያን ጉዳይ በቅርበት እንዲከታተል በመንግስታቱ ድርጅት የተመደበው አጣሪ ቡድን ባለፈው ወር ለመንግስታቱ ድርጅት አዲስ ሪፖርት የያዘ ሰነድን ይፋ አድርጓል። ሰነዱም የኤርትራ መንግስት የተጣለበትን የጦር መሳሪያ ግዥ ማዕቀብን በመተላለፍ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ከሰሜን ኮሪያ መግዛቱን የሚያረጋግጥ ነው። ሰነዱ ኤርትራ በቻይና በኩል ከሰሜን ኮሪያ የገዛቻቸውን ወታደራዊ የመገናኛ ራዲዮ መሳሪያዎች ለባህር ኃይሏ አገልግሎት እንዲውሉ የታሰቡ መሆናቸውን ያብራራል። ኤርትራ ከሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ስትገዛ ይህ የመጀመሪያዋ አለመሆኑን የገለፀው ሰነድ፤ መሳሪያዎቹ በህገ ወጥ ሁኔታ የተገዙት እ.ኤ.አ በ2016 መሆኑንም ያስረዳል።
ይህን ሰነድ መነሻ በማድረግም በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ከሻዕቢያው ባህር ኃይል ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደማይኖራት የሚያትት ሳልሳዊ ማዕቀብን ጥለዋል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከኤርትራ ባህር ኃይል ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ላለማድረግ የወሰነበትን የማዕቀብ ውሳኔ ሰነድን ይፋ ማድረጉ አሁንም በሻዕቢያ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ያመጣል ተብሎ ባይታሰብም፤ ማዕቀቡ በኤርትራ መንግስት ላይ መጣሉ ግን አንድ ርምጃ ይመስለኛል።

በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ላይ ሻዕቢያ ማዕቀብ ምንም የማይመስለው ቢሆንም ቅሉ፤ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ የኤርትራ መንግስት አዲሱን የአሜሪካ መንግስትን ፕሬዚዳንት ቀልብ ለመሳብ በ“ወትዋቾች” (lobbyist) አማካኝነት ያደረገው ጥረት ከንቱ ሆኖ መቅረቱን የሚያሳይ ይመስለኛል። ከባድ ኪሳራም ነው። ሻዕቢያ የዶናልድ ትራምፕን ቀልብ ለመያዝ በሌለ ማንነቱ “የቀበሮ ባህታዊ” ሆኖ ለመቅረብ ያደረገው ሙከራ ምላሹ በሻዕቢያዊያን ዓይን የሚያስቆጭ ነው። የዋሽንግተን አስተዳደር የኤርትራው መንግስት የሰላም ቀበኝነቱን ደብቆ ለመቅረብ ያደረገውን ጥረት በምላሹ ‘አያ ጅቦ ሆይ! እኛ ስለምናውቅህ የማያውቁህ ሀገር ሄደህ ቁርበት አንጥፉልኝ በል!’ የማለት ያህል የሚቆጠር ነው። እናም ይህ ሁኔታ የአስመራውን አስተዳደር እንደ እግር እሳት የሚለበልበው ይመስለኛል። የሚያስቆጨውና የሚያናድደውም ጭምር። እናም ሁኔታው አስመራና ምፅዋ ቤተ-መንግስቶች ውስጥ ሊፈጥር የሚችለውን አሳዛኝ ድባብ ለመገንዘብ፤ የግድ ነብይ መሆንን የሚጠይቅ አይመስለኝም—ግልፅ ነውና።
የኤርትራ መንግስት በተለያዩ ወቅቶች ከሚያከናውናቸው ተግባሮች በመነሳት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በሚገባ ያውቀዋል። አዎ! ሻዕቢያ አሜሪካን ጨምሮ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አዲስ አይደለም—ከራስ ፀጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ በሚገባ ይታወቃል። የገዛ ህዝቦቹን ቁም ስቅላቸውን እንደሚያሳይ፣ በተጠናወተው የጦረኝነት አባዜ የጦር መሳሪያዎችን እንደሚሸምት፣ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሀገራትን ስራዬ ብሎ እንደሚያተራምስ፣ እንደ ኢትዮጵያና ጂቡቲ ያሉ ሀገራትን ከዓለም አቀፉ ድንጋጌ ውጭ በመሆን ድንበር ጥሶ በመግባት ሰላማቸውን የማደፍረስ ልምድ ያለው መሆኑን፣ አልሻባብን ለመሳሰሉ አሸባሪዎች የገንዘብና የሎጀስቲክስ ድጋፍ በማድረግ የአንድ ጣት ያህል ድንበር የማይዋሰናትን ሶማሊያንና ህዝቧን እንደሚያተራምስ እንዲሁም አዲስ በተቋቋመችው ደቡብ ሱዳን የውስጥ ሳይቀር እጁን በማስገባት ሰላሟን እንደሚያውክና ሌሎች የትርምስ ስራዎችን እንደሚከውን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሰወረ ጉዳይ አይደለም።

ሻዕቢያ አስመራ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦችን እንቅስቃሴ በመገደቡ፣ የግል ሚዲያ ባለመፍቀዱ፣ የሚቃወሙትን ሁሉ በአሰቃቂ ሁኔታ ኮንቴይነሮች ውስጥ አጭቆ በማሰር በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲሞቱ በማድረጉ፣ በዚያች ሀገር ውስጥ ህገ መንግስት እንኳን እንዲኖር ባለመፍቀዱና ይህም ኤርትራ ውስጥ የበላይ አንድ ሰው እንጂ የህግ የበላይነት አለመሆኑ በምስጢራዊነቱ ይፈረጃል። በዚህም ሳቢያ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች በአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ፈላጭ ቆራጭ አስተዳደር የምትመራው ኤርትራን “አፍሪካዊቷ ሰሜን ኮሪያ” ሲሉ ይጠሯታል። ታዲያ የዚህ ፅሑፍ አንባቢ ከሰሞነኛው የአሜሪካ መንግስትን ማዕቀብ በመነሳት፤ ‘አፍሪካዊቷ ሰሜን ኮሪያ ከእውነተኛዋ ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን በመግዛቷ በትራምፕ አስተዳደር ማዕቀብ ተጣለባት’ ሊል ይችላል። ወይም ሰሜን ኮሪያ ከራሷ መሳሪያ በመግዛቷ የማዕቀብ ሰለባ ሆነች ቢልም ያስኬዳል።…ሌላ ሌላም።…
ያም ሆኖ ግን ሻዕቢያ ያለፉትን ሁለቱን ማዕቀቦችና ከመሰንበቻው የዋሽንግተን አስተዳደር የጣለበትን ማዕቀብንም ጭምር “ዓይኔን ግንባር ያድረገው” በሚል የለየለት ቅጥፈት ይቃወማል። ህገ ወጥነቱ በየቀኑ እየባሰበት መሆኑ እየታወቀ ቢሆን እንኳን፤ የሰሞኑን የአሜሪካው ማዕቀብም የተቃወመው “ፍርደ ገምድል ነው” በማለት ነው። ምንም እንኳን በኤርትራ መንግስት መዝገበ ቃላት ውስጥ “ፍርደ ገምድል” ምን ማለት እንደሆነ ባይታወቅም፤ አንድ ወገን ሌላውን “ፍርደ ገምድል ነህ” ሲለው፤ ያ ወገን ወይም አካል ወገንተኛ እንዳሻው ሆኖ ፍርድ ይሰጣል ማለት ነው። እናም ከዚህ ትክክለኛ ትርጉም አኳያ ‘ፍርደ ገምድሉ ማነው?’ የሚል ጥያቄ ቢነሳ፤ ምላሹ ሊሆን የሚችለው ዓለም አቀፉን ህግ በመጣስ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን እየገዛ የሚያከማቸው ሻዕቢያ ነው። እናም የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሳልሳዊ የማዕቀብ ውሳኔ ትክክለኛነት በምንም ዓይነት ሚዛን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ለህግ የበላይነት መቆርቆር ፍርደ ገምድል የሚያሰኝ ሰምም አያሰጥም። ለሻዕቢያ ህገ ወጥነትን መቆጣጠር ፍርደ ገምድልነት ከሆነ፤ ፍድረ ገምድል አለመሆን ህጋዊነትን መፃረር ነውን?…የህግ የበላይነት ባለበት ዓለማችን ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ “ህግ ለምኔ” የሚል አስተሳሰብ ቦታ አይኖረውም። ያም ሆኖ “ለአፍሪካዊቷ ሰሜን ኮሪያ” ህጋዊነት ማለት በህገ ወጥ መንገድ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን በመሸመት አሸባሪዎችን መደገፍ ከሆነ፤ ህጋዊነት ማለት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሁለት ማዕቀቦች አታድርግ ያለውን ነገር መፈፀም ሊሆን ነው ማለት ነው።

ዳሩ ግን እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በማን አለብኝነትና “በጫካ ህግ” ለሚመራ ቡድን እንጂ ህግና ስርዓት እውን በመሆኑባት ዓለም ውስጥ ሊሰራ አይችልም። እናም ሻዕቢያ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” በሚል ዓይን ያወጣ አባባል ይህን ጉዳይ ለመካድ ከመሞከር ይልቅ እውነቱን አምኖና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ተስማምቶ መስራት የሚጠቅመው ይመስለኛል። ሆኖም ሃቁን ከሻዕቢያ ጦር አምላኪነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ባህሪ አኳያ ስንመለከተው፤ የአቶ ኢሳይያስ መንግስት ይህን ሊያደርግ አይችልም። ምክንያቱም ሻዕቢያ ያለችውን (ከህዝቡ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ነጥቆ የሰበሰበውንና ከአረቦችም በኪራይ ሰብሳቢነት የተቀበለውን ጭምር) ሽርፍራፊ ሳንቲም አሟጦ የጦር መሳሪያ የመግዛት ልምድ ያለውና ይህን መተው ማለት ደግሞ ራሱን የማጣት ያህል ስለሚቆጥረው ነው። ከሳህል ተራራዎች ጀምሮ ሲከተለው የመጣውን ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት እግፍ አድርጎ በመተው በህግና ስርዓት ሊመራም አይችልም።

በአጠቃላይ የትራምፕ አስተዳደር በሻዕቢያ ላይ የጣለውና ካለፉት የመንግስታቱ ድርጅት ሁለት ማዕቀቦች ጋር ተደምሮ በ“ሳልሳዊ” ማዕቀብነት የጠቀስኩት ዕቀባ የሻዕቢያ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ምንም ይሁን ምን፤ ማዕቀቡ በራሱ የሚያስተላልፈው ነገር ቢኖር ሻዕቢያ ህገ ወጥ መሆኑንና የትኛውም ዓይነት ዓለም አቀፍ ህግ የማይገዛ መሆኑን ነው። እናም የቀጣናው ሀገራት በሻዕቢያ ጦር ሰባቂነት አንፃር፤ ሰላማቸውን፣ ልማታቸውንና ዴሞክራሲያቸውን ለመታደግ የሚወስዱት የተናጠል ራስን የመከላከል ተግባር (የኢፌዴሪ መንግስት በሻዕቢያ ላይ እከተለዋለሁ እንዳለው አዲስ ፖሊሲ ዓይነት ማለቴ ነው) እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በኤርትራ መንግስት ላይ ሪፖርት ከማውጣት በዘለለ ተጨማሪ ጠንካራና የማያላውስ ርምጃ ሊወስድ የሚገባ ይመስለኛል። ይህም ምናልባት ሻዕቢያ ጫናው በዝቶበት ዓለም አቀፉን ህግ እንዲያከብርና የቀጣናው ሀገራትም ድህነትን ለመዋጋት እያደረጉ ያሉትን ርብርብ በማገዝ ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy