NEWS

የአፍሪካ ትልቁ የገበያ ማዕከል በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው

By Admin

April 27, 2017

በአፍሪካ ትልቁ የተባለና “ህዳሴ ግራንድ ሞል” በሚል ስያሜ የሚጠራ የገበያ ማዕከል በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው።

ግንባታው በአገር ውስጥ ባለሃብቶች በተቋቋመው ህዳሴ አክሲዮን ማህበር በሶስት ቢሊዮን ብር ይከናወናል ተብሏል።

ይህ በአፍሪካ በአይነቱ የመጀመሪያ የተባለው ግዙፍና ዘመናዊ የገበያ ማዕከል በ125 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ የሚያርፍ ሲሆን ጠቅላላ የግቢው ስፋት 250 ሺህ ካሬ ሜትር ይሸፍናል።

የህዳሴ ግራንድ ሞል ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ መኮንን በሰጡት መግለጫ የገበያ ማዕከሉ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ከሚገኙት በስፋቱና በዘመናዊነቱ የላቀ ነው።

ግንባታው የከተማ አስተዳደሩ ለአክሲዮን ማኅበሩ ካመቻቻቸው ዘጠኝ ቦታዎች በአንዱ ላይ ይከናወናል።

የገበያ ማዕከሉ በውስጡ 5 ሺህ ሱቆች፣ 2 ዘመናዊ ባለ 4 ኮከብ ሆቴሎች፣ ባንክና ኢንሹራንስ፣ ካፌና ሬስቶራንቶችን የሚይዝ ነው።

ማዕከሉ በአንድ ጊዜ 8 ሺህ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግድ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ እንዲሁም የመኖሪያ አፓርታማዎች እንደሚኖሩትም ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

ግንባታው ሲጠናቀቅ ለ35 ሺህ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል እንደሚፈጥር የገለጹት አቶ ደረጀ፤ ነጋዴውና ሸማቹ ግብይታቸውን በአንድ ቦታ እንዲከውኑ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

ግንባታውን ለማስጀመር ተቋራጮችን በግልጽ ጨረታ ለማወዳደር ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የገበያ ማዕከሉ ግንባታ በሶስት ዓመት ጊዜ ተጠናቆ ስራ አንደሚጀምርም አቶ ደረጀ ጠቁመዋል።