Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሶማሊያ ወጣ…..ወግ

0 266

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሶማሊያ ወጣ…..ወግ  ! /ይነበብ ይግለጡ/

የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሶማሊያ መሬት ለቆ ወጣ የሚለውን ዜና የተለያዩ አለም አቀፍ  የሚዲያ አውታሮች ሲያሰራጩት ከርመዋል፡፡ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት በአገር ውስጥ ሰላም ስለሌለ ነው የሚል ነው፡፡በተመሳሳይ ሁኔታም የኢትዮጵያ ሰራዊት  በሶማሊያ ለቆት የወጣውን ቦታ የአልሻባብ ተዋጊዎች ተቆጣጥረውታል የሚል ዜናም በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡

እነዚህን አይነት የተምታቱ ዜናዎች የሚያሰራጩት የውጭ የሚዲያ ተቋማት ዋነኛ ግባቸው ምንድነው የሚለውን ነጥብ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ ሶማሊያ እንዲገባ የተደረገው በሶማሊ እየተንሰራፋ የመጣው አክራሪነትና አሸባሪነት ድንበር አልፎ ወደኢትዮጵያ ግዛት የገባበት ሁኔታ ስለነበር ይህንን በሀገር ላይ የተቃጣ አደጋ ከመመከትም አልፎ ዋነኛ ይዞታቸው ወደሚገኝበት ዘልቆ በመግባት ማምከን አስፈላጊም ወሳኝም በመሆኑ ነበር፡፡

ይሄን ግዳጁን አሳክቶ ወደ ሀገሩ ተመልሶም ነበር፡፡በሁለተኛው ዙር የተገባበት ምክንያት ደግሞ በሶማሊያ ያለው የአክራሪ እስላማዊ ሀይሎች እንቅስቃሴ እያደገና እየሰፋ በመምጣቱ ለአካባቢውም ሆነ ለቀጠናው አደጋ በመሆኑ የአፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የአለም አቀፉ ሰላም አስከባሪ ኃይል አካል ሁኖ የተሰማራበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

ኢትዮጵያ የሶማሊያ ቅርብ አጎራባችና በምስራቅ በኩል ሰፊ ወሰኖችን የምታጋራ ሀገር እንደመሆንዋ መጠን በሶማሊያ ውስጥ የሚደረገው ማንኛውም አይነት የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ ድንበርዋን ሊያልፍ ስለሚችል ከማንም በላይ ይመለከታታል፡፡ስለዚህም ጉዳዩን የራስዋ ጉዳይ አድርጋ በቅርበት የምትመለከተው ነው የሚሆነው፡፡

ሰፊ በሆነው የጋራ ድንበር የአካባቢውም ሆነ የውጭ አለም አቀፍ አሸባሪ ኃይሎች እንደልባቸው ሊገቡና ሊወጡ ብሎም የኢትዮጵያን ሰላም ሊያደፈርሱ የሚችሉበት እድል እንዳያገኙ በድንበር አካባቢ ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ ሰርጎ ገቦችን መከላከል ሀገራዊ ግዴታም ሀላፊነትም ነው፡፡

በተለይም ከዘመኑ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በአለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው እስላማዊ አክራሪነትና አሸባሪነት ድንበር ዘለው ወደ ኢትዮጵያ ክልልና ይዞታ እንዳይዛመቱ መሰረትም እንዳይኖራቸው የማድረጉ ብሔራዊ ደህንነትንና ሉአላዊነትን የማስጠበቁ ስራ የማንም ሳይሆን የኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የራስዋን ሰላም ጸጥታና ደሕንነት ለማስከበር ከማንም ፈቃድና ይሁንታ የምትጠይቅ ሀገር አይደለችም፡፡

በዚህም መሰረት ከሶማሊያ በመነሳት ቀደም ባሉ አመታት ወደኢትዮጵያ ግዛት ሰርጎ በመግባት ወታደራዊ መሰረት ለመጣልና ማዘዣ ጣቢያ ለመመስረት ጥረት ያደረገውን አለም አቀፍ የአሸባሪዎችና የአክራሪ እስላማዊ ኃይሎች ስብስብ የነበረውን አልኢትሀድ አልኢስላሚያ የተባለውን ቡድን የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ሙሉ በሙሉ ደምስሶታል፡፡ ከዚህ በኃላ በሶማሊያ ውስጥ የተፈጠሩት ተለዋዋጭ ሁኔታዎችና በባሕርያቸው የተለያዩ አክራሪና አሸባሪ እስላማዊ ድርጅቶች ዋነኛ የጥቃታቸው ኢላማ አድርገው የወሰዱት ኢትዮጵያን መሆኑ ግልጽ ነበር፡፡

በቀድሞው የሶማሊያ መሪ ጀነራል መሐመድ ዚያድ ባሬ ሠራዊት ውስጥ ኮሎኔል የነበረው ዳሂር አዌይስ የሚመራው እስላማዊ ምክርቤት በኤርትራም ጭምር እየታገዘና እየተረዳ የኦጋዴንን መሬት የሶማሊያ መሬት ነው እንዋጋለን የሚል መግለጫ ለመስጠት የደፈረበትና ከአስመራ የሚላክ የጦር መሳሪያና ትጥቆች በገፍ በአውሮፕላንና በመርከብም በርበራ ባይደዋና መቋዲሾ ጭምር ይራገፍለት ነበር፡፡

የዚህም አክራሪ እስላማዊ ቡድን የጥቃት ኢላማ በዋነኛነት ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ይህ ቡድን ሙሉ ድጋፍና እገዛ ያገኝ የነበረው ከኤርትራ መንግስትና በውል ተለይተው ከሚታወቁ ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ካላቸው አንዳንድ የአረብ ሀገራት መንግስታት ነበር፤፤የነዚህ ኃይሎች መሰረታዊ አላማ የአፍሪካን ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ አክራሪ እስላማዊ እምነትን በጠመንጃ ኃይልና በሽብር ተግባር ታግዘውና ተደግፈው ለማስፋፋት አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ለማድረግ ሞክረዋል፡፡የመከላከያ ሠራዊታችን ይሄንንም ሴራ ማምከን ችሎአል፡፡

ኦብነግ የተባለውን ኦጋዴንን ከኢትዮጵያ እገነጥላለሁ ብሎ ጠመንጃ ይዞ የሚዋጋውን ድርጅት መረማመጃ በማድረግ በምስራቅ ኢትዮጵያ በመሳሪያ ኃይል የተደገፈ ብዙ ትግል አድርገዋል፡፡የኮሎኔል ዳሂር አዌይስ እስላማዊ ምክርቤት ከፈረሰ በኃላ በእግሩ የተተካው አክራሪና አሸባሪ የሆነው እስላማዊ ሀይል አልሻባብ ሲሆን ከውልደቱ ጀምሮ ኢላማ ያደረገው ኢትዮጵያን ነው፡፡

ይህንን የመከላከል የመመከት ብሎም በሐገሪቱ ሕልውና ላይ የተነሳውን አክራሪና አሸባሪ ኃይል አቅም አግኝቶ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ አስቀድሞ የመከላከል ግዴታ የኢትዮጵያ መሆኑ ይታወቃል፡፡በሶማሊያ ማእከላዊ መንግስት ባለመኖሩ ሀገሪቱ የአለም አቀፍና የአካባቢው የሽብር ኃይሎች መናሀሪያና መፈንጫ የሆነችበት ደረጃ ላይ የደረሰችበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር፡፡

ለኢትዮጵያ የነበረው ብቸኛ የግዴታ አማራጭ ድንበር አልፎ በመግባት አሳዶ መምታት አቅማቸውን ማመናመን ብሎም መደምሰስ አስፈላጊና ተገቢ ራስን የመከላከል እርምጃ ስለሆነ ነው የኢትዮጵያ ሰራዊት ድንበር አልፎ አልሻባብን በመሸገበት ቦታ ሁሉ እያሳደደ ያራገፈው፡፡ይሄን ማድረግ ባይቻል ኖሮ ዛሬ በሶማሊያና በእኛ ድንበር አካባቢ ያለው ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ሌላ መልክ ይኖረው ነበር፡፡አደጋው የከፋ ሊሆን ይችልም ነበር፡፡

በመጀመሪያው ዙር በተደረገው ዘመቻ አልሻባብ የያዛቸውን ቦታዎች በሙሉ ያስለቀቀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነው፡፡የሠራዊቱ ወጪም የተሸፈነው በኢትዮጵያ ነበር፡፡ በዚህም የአልሻባብን የውጊያ አቅም የሠራዊት ኃይል ድርጅትና ትጥቅ በከፍተኛ ደረጃ መስበር ተችሎአል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራዊት በመጀመሪያው ዙር ወደ ሶማሊያ አልፎ የገባው የማንንም ጥቅም ለማስከበር ሳይሆን የራሳችንን ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ሰላም ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ነው፡፡አደጋው ድንበር አልፎ ወደ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመዛመቱ በፊት በነበረበት ቦታና ይዞታ ላይ ዘምቶ በመዋጋት ማምከን ይገባ ስለነበረም ነው፡፡ሠራዊቱ ለቆ እንዲወጣ የተደረገው በሀገራችን የኢኮኖሚ አቅም ሙሉ ወጪው እየተሸፈነ ረዥም ጊዜ ለማቆየት ስለማይቻል ብቻ ነው፡፡ሌላ ምክንያት የለውም፡፡

በሁለተኛው ዙር የተፈጠረው ሁኔታ የኢትዮጵያ ሠራዊት ግዳጁን ጨርሶ ወደ ድንበሩ ከተመለሰ በኃላ አልሻባብ ዳግም በመንሰራፋቱ በርካታ ቦታዎችን ለመቆጣጠር በመቻሉ የአፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ሠራዊት የአለም አቀፉ ሰላም ማስከበር ተልእኮ አባል ሁኖ በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ግዳጅ እንዲሰማራ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የኢትዮጵያ ሠራዊት ዳግም በሶማሊያ መሬት በመዝመት በአልሻባብ ይዞታ ስር የነበሩ በርካታ ቁልፍ ቦታዎችን በውጊያ አስለቅቆ በመቆጣጠር በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን አድርጎአል፡፡

በዚህ ተልእኮ ውስጥ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሁለት መንታ ግዳጆችን ተወጥቶአል፡፡ የመጀመሪያው ወደራሱ ግዛት አልፎ ለመግባት አሰፍስፎ የነበረውን አክራሪና አሸባሪ እስላማዊ ኃይል አልሻባብን በራሱ ግዛትና መሬት ላይ ውጊያ ገጥሞ አሳዶ መምታት ችሎአል፡፡ሁለተኛው ነጥብ አለምአቀፍ ሰላም የማስከበር ግዳጁን በአፍሪካ ሕብረትና በተባበሩት መንግስታት ጥላ ስር ሁኖ ለመወጣት ችሎአል፡፡

የኢትዮጵያን ሠራዊት የግዳጅ አፈጻጸምና ብቃት በተመለከተ የአፍሪካ ሕብረትም ሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጦር አዛዦች በአድናቆት የሰጡት ምስክርነት ከበቂ በላይ ነው፡፡ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሶማሊያ መሬት ለቆ ወጣ፤አልሻባብ ሰፊ ይዞታዎችን እየተቆጣጠረ ነው የሚለውን ዜና የሚያሰራጩት የውጭ ሚዲያ ተቋማት አልሻባብ መሬቶቹን በመቆጣጠሩ የተሰማቸውን ደስታ እየገለጹ ያሉ ይመስላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሠራዊት ይዞአቸው የነበሩትን መሬቶች በሌሊት ነው ለቆ የወጣው በማለት አልሻባብ መሬቶቹን እንዲቆጣጠር ጭምር ግፊት እያደረጉ ያሉም ናቸው፡፡የውጭው ሚዲያ ከአሸባሪዎች ጎን በመሰለፍ መረጃ የማቀበል የመጠቆም ስራ እየሰራም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሲጀመር ጦሩ አካባቢውን ለቆ ወጣ የሚለው መረጃ መሰረተ ቢስ ነው፡፡

በውጊያ ብቃትና ችሎታው የማይታማው የኢትዮጵያ ሠራዊት በሶማሊያ አልሻባብን አስለቅቆ  ከያዛቸው መሬቶች ለምን ለቆ ወጣ? እንዴት ለቀቀ ? ምንስ ሊያደርግ አስቦአል ወይንስ አቅዶአል የሚለውን ጥያቄ ማንም ሊመልሰው አይችልም፡፡ ምን አልባት መጠነኛ የሆነ ስለታዊ የጦር ስለቶች ሊከተል ይችላል፡፡ ሶማሊያን ለቆ ወቷል የሚለው ግን ፈጠራ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እነዚህ የላቁ ከፍተኛ ወታደራዊ ምስጢሮች ናቸው፡፡ ሀገር ቤት ውስጥ ችግር ስላለ ነው የሚለው ደካማ ምክንያታቸውም አሳማኝ አይደለም፡፡ሊሆንም አይችልም፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy