CURRENT

የኢጣሊያ ኩባንያ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት በመመደብ በኢትዮጵያ የቡና ኢንዱስትሪ ሊሰማራ ነው

By Admin

April 11, 2017

የጣሊያን ኤጀንሲና የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት በኢትዮጵያ ለቡና ልማት የሚውል የ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ስምምነት መፈራረማቸውን ዴይሊ ኮፊ ኔውስ መጽሔት በድረ ገፁ ላይ አስፍሯል፡፡

ስምምነቱ በሁለቱ አጋሮች ትብብር በፕሮጀክት የሚፈጸም ነው ተብሏል፡

ፕሮጀክቱ የጣሊያንኑን ታዋቂ የቡና አቅራቢ ኢሊኮፊ እና ኤርኔስቶ ኢሊ ፋውንዴሽንን የያዘ ነው፡፡ የኢሊ ቤተሰብ የሚያንቀሳቅሰው ተቋም ለትርፍ ያልተቋቋመና ቡናን በተመለከተ የሚደረጉ ሳይንሳዊ ምርምሮች የሚደግፍ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ የቡና አምራቾች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የገለጸው ኢሊ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ግብይት ባለስልጣን ቀዳሚ አጋሩ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ሶስት አመት የሚወስደው ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ቡና ጥራት፣ ተደራሽነትና አለም አቀፍ ተቀባይነት በማሳደግ ከወጪ ንግዱ የሚገኘውን ገቢ እንደሚያሳድገውና አነስተኛ ቡና አምራች ገበሬዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ታምኖበታል፡፡

በአዲስ አበባ፣ ኦሮሞያና ደቡብ ክልል የሚተገበረው ፕሮግራም ለአነስተኛና በማህበር ለተደራጁ ቡና አምራቾች ቀጥተኛ ድጋፍ በመስጠት የቡና አመራረት እውቀታቸውን እንዲያሳድጉና ከምርት በኋላ ያለውን የአለቃቀም ክፍተት እንዲሞሉ እንደሚያስችላቸው ተጠቅሷል፡፡

ፕሮጀክቱ በተጨማሪ ለቡናና ሻይ ልማት ግብይት ባለስልጣን የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ አዲስ አበባ ላይ የቡና አቆላል ማሰልጠኛ በመክፈት የአገር ውስጥ የተቆላ ቡና ግብይትን የማሳደግ ግብ አስቀምጧል፡፡

የጣሊያን የልማት ኤጀንሲና የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት  በጋራ በሰጡት መግለጫ የኢሊካፌና የኤርኔስቶ ኢሊ ፋውንዴሽን የገንዘብ እገዛ የፕሮጀክቱን አጋሮች በቀጥታ በማካተት የአገር ውስጥ አምራቾችን አቅም በማሳደግ በቡና ንግድ ያላቸውን የገበያ ትስስር እውቀት እንዲያሳድጉ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ከዚሁ ጎን ለጎን ንግዱን በማመቻቸትና በማማካር እገዛ እንደሚሰጡም አስታውቀዋል፡፡

“ የቡና ገበያ ትስስር ለዚች አገር በጣም አስፈላጊ ነው “ በማለት የጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ የአዲስ አበባ ቢሮ ተጠሪ ጂኤቭራ ሌቲዚያ የስምምነት ፊርማው በተከናወነበት ወቅት ተናግረዋል፡፡ “ ቡና የኢትዮጵያ ባህላዊ ቅርስ ነው፡፡ እናም የቡና ምርትን ማሳደግ የሁሉም ሀላፊነት ነው ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ያለው የቡና ዝርያ በአለም ላይ ተፈላጊ መሆኑን የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግስት ስትራተጂ በመቅረጽ የግብይቱን ተደራሽነትና የአገሪቱን ቡና ጥራት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ተጠሪው መናገራቸውን ጠቅሶ ድረ ገጹ ዘገባውን ደምድሟል፡