NEWS

የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሕንፃ በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው

By Admin

April 15, 2017

የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ሊያስገነባ ነው:: የሕንፃው መሠረት ድንጋይ ማክሰኞ ሚያዚያ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. የኦሮሚያ ክልልና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት በይፋ ተቀምጧል:: የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የኦሕዴድ ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦሕዴድ ምክትል ሊቀመንበርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) እና የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሥራና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓብይ አህመድ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማና ሌሎችም ተገኝተዋል:: ሕንፃው በቦሌ መንገድ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት በሚገኝ 4,882 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ 14 ፎቆች ይኖሩታል ተብሏል:: አረንጓዴ ተክሎች በሕንፃው አናት ላይ እንደሚኖሩ የሕንፃ ንድፍ (ዲዛይን) ያመለክታል:: የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ የሕንፃው ግንባታ ድርጅቱ የሚዲያ ተልዕኮውን በብቃት ለመፈጸም ያስችለዋል ብለው፣ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆንም እንደሚያግዘው ገልጸዋል:: የሕንፃው ግንባታ ዋጋና የሥራ ተቋራጩ ማንነት አልተገለጸም:: ከባለሥልጣናቱ በስተጀርባ የሚታየው የሕንፃው ንድፍ (ዲዛይን) ነው:: (ፎቶ በመስፍን ሰለሞን)