CURRENT

የኦዲት ግኝት መረጃዎችን ለማጥፋት ሲባል ላፕቶፖችን እስከ መስረቅ የደረሰ ወንጀል እየተፈፀመ ነው ተባለ

By Admin

April 29, 2017

የኦዲት ግኝት መረጃዎች ለማጥፋት ሲባል ሰነዱ የተቀመጠባቸውን ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን እስከ መስረቅ የደረሰ ወንጀል እየተፈፀመ መሆኑ ተገልጿል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ ግዥና አሰተዳደር ቋሚ ኮሚቴ አባላት በኦዲት ቁጥጥር ወቅት ከኦዲት ተደራጊው መስሪያ ቤት ለባለሙያ ተብለው የተሰጡ ቢሮዎችን በመገንጠል የሚፈጸሙ የላፕቶፕ ኮምፒዪተር ስርቆት መፍትሄ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል።

እስካሁን ድርጊቱ በአዳማ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እና በኢትዮጵያ ምግብ፣ መድሀኒትና ጤና ክብካቤ ቁጥጥር ባለስለጣን መስሪያ ቤቶች ተፈፅሟል።

በኦዲት ቁጥጥር ወቅት ለኦዲት ባለሙያው ከተሰጠው ቢሮ ውስጥ የኦዲት ግኝት የሰፈረባቸው የላፕቶፕ ኮምፒውተሮች ተሰርቀዋል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቺ ዲቢሶ፥ ስርቆቱን በመፈጸም የተጠረጠሩት ግለሰቦች ለህግ መቅረባቸውን ተናግረዋል።

በተሰረቁት ላፕቶፖች ውስጥ የነበሩት የኦዲት ግኝት መረጃዎች አስተማማኝ በሆነ መንገድ በሌሎችም ስፍራዎች በመቀመጣቸው ምንም አይነት መረጃ አለመጥፋቱንም ዋና ኦዲተሩ አረጋግጠዋል።