Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የከሰሙት የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች

0 1,845

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ነው፤ የፕሬስ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ እንደ ድንገተኛ ጎርፍ በርካታ ጋዜጦችና መጽሔቶች ወደ ገበያው የተቀላቀሉት፡፡ በተለይም በምርጫ 97 የወቅቱን የፖለቲካ ትኩሳት የሚያትቱ ጋዜጦች ህትመት መጠን በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያሳየውም በወቅቱ እስከ 100ሺ ቅጂዎች ማሳተም የቻሉ ከ400 በላይ የግል ጋዜጦችና 170 መጽሔቶች ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ግን 13 ጋዜጦችና 11 መጽሔቶች ገበያ ላይ ያሉ ሲሆን፣ ከፍተኛው የቅጂዎች ብዛትም በአማካይ ከ10 ሺ አይበልጥም፡፡ ለመሆኑ በአንድ ወቅት ገበያውን ያጥለቀለቁት የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች ምን አከሰማቸው?

በሪፖርተር ጋዜጣ የፖለቲካ አምድ አዘጋጅ አቶ የማነ ናግሽ እንደሚናገሩት፤ በተለይም በ1997 .ም እንደ አሸን የፈሉት ጋዜጦች ሲጀመርም እውነተኛ ጋዜጦች አልነበሩም፡፡ አብዛኞቹ የወቅቱን የፖለቲካ ትኩሳት ለማራገብ የተቋቋሙ የፓርቲ ልሳኖች ነበሩ፡፡ አጀንዳቸውም ትክክለኛ የጋዜጠኝነትን መርህን ያልተከተለ በመሆኑ ዕድሜያቸው አጥሯል፡፡

«ትኩረት ለማግኘት ብቻ ታሳቢ አድርገው ያለኃላፊነት ይፃፉ በነበሩ ጽሑፎች ምክንያት የበርካቶች አስተሳሰብ ተበርዟል፡፡ያኔ የተባለሸ ጭንቅላት እስካሁን ማስተካከል አልተቻለም» የሚሉት አቶ የማነ፤ ጋዜጦቹ በፕሬሱ ዓለም አብዮት ያስነሱ ናቸውቢባልም እንኳ በሕዝቦች መካከል የማይበርድ ፀብን በማስነሳትም ወደር የማይገኝላቸው እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ ይህን ተከትሎም መንግሥት ሕጎችን በማውጣት ሕገወጦችን የማረም ሥራ መስራቱን ያመለክታሉ፡፡ ሂደቱ ግን ጥሬውን ከብስሉ ያልለየ መሆኑ በሕጉና በሙያ ሥነምግባራቸው ይሰሩ የነበሩ ጋዜጦችን ሳይቀር ከገበያ ማስወጣቱን ይጠቅሳሉ፡፡

በተለይም ደፈር ብለው የሚፅፉ ጸሐፊዎች በመታሰራቸው ምክንያት ሌሎችም «የእነርሱ ዕጣ ይደርሰናል» በሚል ሥራቸውን የተዉ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ አንዳንዶቹም ይደርስብናል በሚሉት ዛቻ ተደናግጠው ከአገር የወጡበት አጋጣሚ መኖሩን ያስረዳሉ፡፡ ጤነኛውን ከበሽተኛው ያልለየው ቁጥጥር አብቦ የነበረውን የግሉ ፕሬስ እንደጠዋት ጤዛ እንዲረግፍ ምክንያት ሆኗል ባይ ናቸው፡፡

«ለግል ጋዜጦች ቁጥር መመናመን በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋናነት ግን መንግሥት የፕሬስ ነፃነትን ከማወጅ ባለፈ በተጨባጭ እንዲተገበር ምቹ ሁኔታን አለመፍጠሩ ነው» የሚሉት ደግሞ የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ፍሬው አበበ ናቸው፡፡ «መንግሥት አዋጁን ቢያወጣም በተግባር የሚታየው ግን የግሉን ፕሬስ እንደጠላት ፈርጆ በአንድ ቅርጫት ጠቅልሎ ማስቀመጡን ነው» ሲሉ ይጠቅሳሉ፡፡

በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ መንግሥት ሰዶ የማሳደድ ተግባር ውስጥ የገባበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁንም ፖለቲካዊ ተፅዕኖው አለመቀነሱን ያመለክታሉ፡፡ መንግሥትን የሚተቹ ጽሑፎች እንዳይወጡ ማተሚያ ቤቶችን ሳይቀር የሚያሳድምበት አጋጣሚም አለ፡፡ ይህም የግሉ ፕሬስ ወደፊት እንዳይራመድና ከህትመት ውጪ እንዲሆን አድርጎታል ባይ ናቸው፡፡

እንደ አቶ ፍሬው እምነት፤ መንግሥት በሕገመንግሥቱ መሠረት የግሉ ፕሬስ ነፃነቱን እንዲጎናፀፍ ምቹ ሁኔታን ካለመፍጠሩም ባሻገር ዘርፉ እንዲጠናከር የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ አይደለም፡፡ የህትመት ዋጋ በየጊዜው እየናረ መምጣቱን ተከትሎ ልክ እንደሌላው ዘርፍ በወረቅት ላይ ድጎማ እንዲያደርግ፣ የማተሚያ ማሽኖችም ያለቀረጥ እንዲገቡ የቀረበለትን ጥያቄ ችላ ብሏል፡፡ በሆደ ሰፊነት ለዘርፉ ማደግ አለመስራቱ አጠቃላይ ፕሬሱ ከሚገባው በላይ ቀጭጮ በመኖርና ባለመኖር መካከል እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህር አቶ ተሻገር ሽፈራው በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በተለይም ለጋዜጦቹና መጽሔቶቹ ቁጥር መመናመን ዋነኛው ምክንያት በአገሪቱ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ቁጥር መበራከትና በተመሳሳይ የማህበራዊ ድረገፅ ተጠቃሚዎች በከፍተኛ መጠን መጨመራቸው ነው፡፡ እነዚህን የመገናኛ ብዙኃን ተመራጭ የሚያደርጉትም በነፃና በፍጥነት በማግኘታቸው ነው፡፡ በተጨማሪም በመረጃ እጦት ምክንያት የሚገባውን ያህል የማይሰሩ መሆናቸው በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ተዓማኒነት ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ ከገበያ ለመውጣት ተገደዋል፡፡

«የፀረ ሽብር አዋጁም ሆነ ሌሎች አዋጆች በተወሰነ መልኩ ተፅዕኖ ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከገበያ ለመውጣት ቁልፍ ችግር ነው ብዬ አላምንም፤ ምክንያቱም በሰለጠኑት አገራትም ተመሳሳይ ሕጎች ይወጣሉ፤ በዚህ ምክንያት ግን ከገበያ የሚወጣ የለም» የሚሉት አቶ ተሻገር፣ በተለይም ተፅዕኖችን ተቋቁመው እስካሁን የቆዩ ጋዜጦች ባሉበት አገር ይህ ሃሳብ ውሃ የማያነሳ መሆኑን ነው የሚጠቅሱት፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩም በአቶ ተሻገር ሃሳብ ይስማማሉ፡፡ እንደ እርሳቸው እምነትም፤ በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልጉ አካላት ቁጥር የቀነሰው ሥራውን ከባድና ውስብስብ አድርጎ በመቁጠር እንጂ መንግሥት ለዘርፉ አፍራሽ አመለካከት የለውም፡፡ ነባሮቹም ከገበያ የሚ ወጡት ማስታወቂያ ባለማግኘታቸውና ወጪውን ተቋቁመው መቀጠል ባለመቻላቸው ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚወጡ አዋጆችና መመሪያዎች ለዘርፉ ማደግ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ እንጂ የሚያቀጭጩ አይደሉም፡፡

በመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የሚዲያ ልማትና ብዝሃነት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታምራት ደጀኔ ደግሞ ዋናው ችግርም ገና ከጅምሩ አበቃቀሉ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም ስለሙያው በቂ እውቅት የሌላቸው አካላት በጋዜጠኝነት ስም የራሳቸውን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ለማራመድ የሚንቀሳቀሱበት መሆኑ የዘርፉ ልማት በእንጭጩ እንዲቋጭ ማድረጉን ነው የሚያብራሩት፡፡

የቀድሞው ነባራዊ ሁኔታ ለኪራይ ሰብሳቢዎች በአቋራጭ መክበሪያ መንገድ ከፍቶላቸዋል፡፡ አንዳንዶቹም ካልታወቀ ምንጭ ጭምር ድጋፍ በማግኘት በሬ ወለደመረጃዎችን በማሰራጨት እስከተወሰነ ርቀት መጓዛቸውን ያመለክታሉ፡፡ ይሁንና የኅብረተሰቡ የንቃተ ህሊና ደረጃ እያደገ ሲመጣ እንዲሁም በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቁጥር ከፍ በማለቱ በተወሰነ መልኩ መሻሻሎች መታየታቸውን ያምናሉ፡፡

አቶ ታምራት «መንግሥት በዘርፉ ላይ ጫና ያሳድራል» በሚለው ሃሳብ አይስማሙም፡፡ ለዚህ አቋማቸው ማሳያ የሚያደርጉትም ገዢው ፓርቲ ሥልጣን ላይ በወጣ ማግስት ካወጃቸው አዋጆች መካከል የፕሬስ አዋጁ መሆኑን ሲሆን፣ በዚህም ተጨቁነው የነበሩ አስተሳሰቦች በነፃነት እንዲራመዱ ማድረጉን ያመለክታሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር በሕገመንግሥቱ አንቀፅ 29 መረጃን የማግኘት ነፃነት በይፋ አረጋግጧል፤ ቅድመ ምርምራ እንዲነሳም አድርጓል፡፡

በተለይም የግሉ ፕሬስ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ማስታወቂያ እንደመሆኑ በፍትሃዊ መንገድ እንዲጠቀሙ የተደረገው ድጋፍ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ «ብዙዎቹ ሙያውን እየወደዱና በአግባቡ እየሰሩ በገቢ እጥረት ምክንያት ከሥራው በጊዜ የተሰናበቱበት ሁኔታ አለ» ሲሉ የሚናገሩት አቶ ታምራት፤ መንግሥት ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ የድጋፍ ማዕቀፎችን አዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በዋናነት መንግሥታዊ ማስታወቂያዎችን በፍትሃዊ መንገድ እንዲከፋፈሉ የሚያደርግ መመሪያ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ ይህም ጋዜጦቹ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ የላቀ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ነው ያስገነዘቡት፡፡

«ማንም ከሕግ በላይ መሆን እንደማይችል እየታወቀ አንድ ሰው ጋዜጠኛ ስለሆነ ብቻ ለምን ተነካሁ ማለት ተገቢ አይመስለኝም» የሚሉት አቶ ታምራት፤ የወንጀለኛ ሕጉም ሆነ የሽብር አዋጁ ሕገወጦችን በመረጃና በማስረጃ መሠረት እንዲቀጡ የሚያደርግ እንጂ የዘርፉን ተዋናዮች ተስፋ ለማስቆረጥ ታሳቢ ተደርገው የተዘጋጁ አለመሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

እንደ ባለሙያዎቹ እምነት፤ ዘርፉን ለመታደግና ዳግም እንዲያሰራራ የግሉ ፕሬስ በራሱ ከፍራቻ መውጣትና በትክክለኛ መረጃዎች ላይ የተመሰረቱ ዘገባዎችን ለኅብረ ተሰቡ ሊያቀርብ ይገባዋል፡፡ መንግሥትም የህትመት ዋጋን ለመቀነስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ዘርፉን የሚያበረታታ የፖሊስ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ አላሰራ ያሉ አዋጆች ከአሉ መፈተሽና ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በመምከር የጋራ መግባባት ላይ መድረስ አለበት፡፡ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ከተቃውሞ የመነጠል አመለካከት መፈጠርም ይገባዋል፡፡

 ማህሌት አብዱል

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy