Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የወጣቱ ስራ ፈጠራ ይጎልብት!

0 591

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የወጣቱ ስራ ፈጠራ ይጎልብት!  /ታዬ ከበደ/

ወጣቱ ዛሬ በምቹ ሁኔታ ላይ ይገኛል። መንግስት ለእርሱ በሚመቸው መንገድ የሀገሪተን ኢኮኖሚ ታሳቢ በማድረግ በርካታ ተግባሮችን ከውኖለታል። በፌደሬራልም ይሁን በክልል መንግስታት በጀት ተይዞለት ወደ ስራ ገብቷል። ሆኖም ይህን ምቹ አጋጣሚ ተጠቅሞ የትኛውንም ዓይነት ስራ መናቅ አይኖርበትም።

እርግጥ አንድ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ድርጅት በባህሪው ህዝባዊ ከሆነ፤ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያማከሉ መሆናቸው አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በባህሪው ህዝባዊና ልማታዊ በመሆኑ፤ ላለፉት 26 ዓመታት በአብዛኛዎቹ መስኮች ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

ከ26 ዓመት በፊት በማንነቱም ይሁን በኑሮው አንገቱን ደፍቶ ይሄድ የነበረው ወጣት፤ ዛሬ ቀና ብሎ በሀገሪቱ በመመዝገብ ላይ ከሚገኘው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በኢኮኖሚው ላይ ባበረከተው አስተዋጽኦ መጠን በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገሰገሰ ነው፡፡ ለአብነትም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ተደራጅተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ማንሳት ይቻላል። እናም ወጣቱ በአሁኑ ወቅት የላቀ ተጠቃሚ ለመሆንም ቁርጠኛ አቋም ከመንግስት ጋር መስራት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ የትኛውንም ዓይነት ስራ መናቅ የለበትም፡፡

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ወጣቱ ከመንግስት የሚሻው ነገር ተጠቃሚነትን ነው። ይህን ለመከወንም መንግስት ለወጣቱ ስራ ፈጠራ ሊውል የሚችል የ10 ቢሊዮን ብር መድቧል። ገንዘቡ የወጣቱን የስራ ፍላጎት ለማሟላት የተበጀተ ሲሆን፤ ከመሰንበቻው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአፋጣኝ ወደ ስራ እንዲገባና ወጣቱም ተጠቃሚ እንደሚሆን ማዘዛቸው ይታወቃል። እርግጥ ይህ ሁኔታ ወጣቱ ከስራ ፈጠራ አኳያ የሚጠብቀው ብሩህ ተስፋ መኖሩን የሚያመላክት ይመስለኛል። ዳሩ ግን ይህን የወጣቱን ብሩህ ተስፋ ለማጣጣል የሚሞክሩ አንዳንድ የውጭ ፅንፈኛ ዲያስፖራዎችን አሉባለታዎችን መስማት አይኖርበትም። ወጣቱ ያለበት ችግር በሀገሩ መንግስትና ህዝብ እንጂ በፅንፈኛ ዲያስፖራዎች ምላሽ የማያገኝ መሆኑን በሚገባ መገንዘብ ያለበት ይመስለኛል።

እርግጥ ወጣቱ ክፍል በዕድሜ ለጋ ቢሆንም ይህን ዕውነታ ይዘነጋዋል እያልኩ አይደለም።  የሀገራችንን ብሩህ ተስፋ ለማጨለም ለሚሯሯጡ የውጭ ሃይሎች ተላላኪ በመሆን የሚሰሩ የከሰሩ ፖለቲከኞችንም ዓላማና ግብ አይገነዘብም እያልኩም አይደለም። በግልፅ ለመናገር ወጣቱ ተስፋውና መፃዒ ዕድሉ የተያያዘው ሀገረሪቱን ከሚመራው መንግስት እንጂ በቅጥረኝነት ተሰልፈው የሀገራችንን ሰላም ለማወክ ከሚጥሩ ኃይሎች አለመሆኑን ነው። እናም መጪው ጊዜ ከሀገሩ መንግስትና ህዝብ ጋር እንጂ ለአንድም ሰኮንድ ቢሆን ከፅንፈኛ ዲያስፖራዎች የሚያስገኝለት ምንም ነገር አለመኖሩን ሁሌም ሊዘነጋው የሚገባ አይመስለኝም።

እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ተግባሮች ተግባራዊ ሆነዋል። ለአብነት ያህልም በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅት ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች ተደራጅተው በተለያዩ የስራ መስኮች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪም በግብርና የሥራ መስኮች 2 ነጥብ 21 ሚሊዮን እንዲሁም ከግብርና ውጭ በሆኑ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች 2 ነጥብ 43 ሚሊዮን ወጣቶች ተሰማርተው ተጠቃሚ ሆነዋል። እንዲሁም በ553 ወረዳዎች 1 ሺህ 684 የወጣት ማዕከላት በማስፋፋት በአሁኑ ወቅት ነባሮችን ጨምሮ የማዕከላቱ ቁጥር ወደ 2 ሺህ 284 እንዲደርስ ማድረግ ተችሏል። በእነዚህ ማዕከላትም ከ6 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የተለያዩ አገልግሎቶች እንዲያገኙ መደረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ይህ ዕውነታም ወጣቱ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ወቅት ምን ያህል ተጠቃሚ መሆኑን የሚያሳይ ነው። እርግጥ የወጣቱ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በልማቱ ልክ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ ሆኗል ማለት አይቻልም። ያም ሆኖ ግን ዛሬም ከትናንቱ በተሻለ ሁኔታ የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሩህ ተስፋዎች ተወጥነዋል። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ወጣቶች የዛሬ አፍላ የልማትና የዴሞክራሲ ኃይሎችና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች እንደመሆናቸው በትምህርት የታነፀና የተገነባ አቅም እንዲኖራቸው ከፍተኛ ትኩረት ለመስራት ታቅዷል።

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ብቃት በማሳደግ በሀገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም ልማታዊ አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተደራጀና በተቀናጀ አኳኋን የነቃና ግንባር ቀደም ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከውጤቱም በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዟል።

የሀገራችን ወጣቶች አካበባቢ ከሥራ ስምሪት ጋር ተያይዞ የሚታየውን የተሳታፊነትና ፍትሐዊ ተጠቀቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ መረጃዎች ያስረዳሉ። በዚህም በተለያዩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ዘርፎች የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሆኑ፣ ወጣቶች በህብረት ሥራ ማህበራት በመደራጀት የብድርና ቁጣባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ታስቧል።

በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከቴክኒክ ሥልጠና ማዕከላት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት የወደፊት የሀገራችን ተስፋ በሆኑ አምራች ዘርፎች ማለትም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ በኢንዱስትሪዎችና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ተሰማርተው የወደፊት የሀገራችን ልማታዊ ባለሃብቶች መፍለቂያ እንዲሆኑ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እርግጥ እነዚህን ተግባራት ዕውን ለማድረግም ለወጣቶች ስራ ፈጠራ የሚውልና ቀደም ሲል የጠቀስኩት የ10 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞ በአፋጣኝ ወደ ስራ ለመግባትም ጥረት እየተደረገ ነው። ይህም የወጣቱን የነገ ተስፋ የሚያለመልምና ከሀገሩ ሁለንተናዊ ዕድገት ተጠቃሚ የሚሆነው በመንግስት ብቻ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ያም ሆነ ይህ ወጣቱ ይህን ብሩህ ተስፋ በሚገባ መመልከት ያለበት ይመስለኛል። ትናንት የነበረው ተጠቃሚነቱ ነገም ሆነ ከነገ በስቲያ ተጠናክሮ የሚቀጥል እንጂ የሚቋረጥ አለመሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል።

በመንግስት የስልጣን መዋቅር ውስጥ በተፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር ወጣቱን ከተጠቃሚነት ጎራ ያፈናቀለውና በተገቢው መንገድም ከልማቱ ተጠቃሚ አላደረገውም። ይህ ሁኔታም ወጣቱ ለፅንፈኛ ዲያስፖራዎች የተሳሳተ ተልዕኮ እንዲጋለጥ አድርጎታል። ያ የትናንት ታሪክ ነው። አሁን ደግሞ አዲስ መድረክ ተፈጥሯል። የወጣቱ ስራ ፈላጊ ድምፅ ይበልጥ ሰሚ፣ ይበልጥ ተደማጭ ሆኖ ገንዘብም ተመድቦለታል።

ይህን ገንዘብ በአግባቡ ከመጠቀም ባለፈ፣ ስራ ፈጣሪነትን በማጉላት ማናቸውንም ስራዎች ለማከናወን የስነ ልቦና ዝግጅት ሊኖረው ይገባል። እናም እያንዳንዷ ሳንቲም ማናቸውንም ስራ ከውና ሌላ ተደማሪ ትርፍ እንድታመጣ ወጣቱ ስራን ባለመናቅ ከወዲሁ ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy