Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከግብፅ ፕሬዚዳንት ጋር የጋራ መተማመን መፍጠራቸው ተነገረ

0 347

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

  • ሁለቱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በወር ሁለት ጊዜ ለመገናኘት ወስነዋል
  • ሽብርተኛነት የጋራ ጠላት መሆኑን መተማመናቸው ተገልጿል
  • ግብፅ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ማናቸውም ድርጊት አትፈጽምም ተብሏል

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በካይሮ ቆይታቸው ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር መክረው፣ የጋራ መተማመን መፍጠራቸው ተሰማ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለስ ዓለም በተለይ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ዶ/ር ወርቅነህ ካይሮ ላይ በነበራቸው የአንድ ቀን ቆይታ ከግብፅ ፕሬዚዳንት አልሲሲና ከአገሪቱ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ወሳኝ በተባሉ ጉዳዮች ላይ በመምከር መተማመን ፈጥረዋል፡፡

ቃል አቀባዩ እንዳሉት፣ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ጥልቀት እንዲኖረውና ሙሉ መተማመን ለመፍጠር ‹‹ስትራቴጂካዊ ውሳኔ›› ላይ መድረሷን፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ነግረዋቸዋል፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል አንዳንድ አለመተማመኖችና ጥርጣሬዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ በሁለቱም አገሮች ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች መካከል መተማመን ለመፍጠር ቅድሚያ ለመስጠት ተነጋግረዋል ብለዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች ሚዲያዎች ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ፣ ሽብርተኝነትን በጋራ ጠላትነት ፈርጀው እንዲዋጉና እንዲንቀሳቀሱም መስማማታቸውን ቃል አቀባዩ አክለዋል፡፡

‹‹የሁለቱ አገሮች ዕጣ ፈንታ አንድ ዓይነት ነው›› በሚል መንፈስ መነጋገራቸውን የተናገሩት አቶ መለስ፣ ኢትዮጵያ በግብፅ ሕዝብ ላይ አንዳች ጉዳት ሳታደርስ በራሷ ሀብት የመልማት መብት እንዳላት ግብፆች ሊረዱት የሚገባ ቀዳሚ ጉዳይ እንደሆነ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማስረዳታቸውንም ተናግረዋል፡፡

አልሸባብን ጨምሮ ማንኛውም አሸባሪ ድርጅት የጋራ ጠላት መሆኑንና በአንድነት ለማዋጋት መስማማታቸው የተሰማ ሲሆን፣ ዶ/ር ወርቅነህ በቅርቡ በአሌክሳንደርያና በሌሎች የግብፅ አካባቢዎች በክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ የደረሰውን የሽብር ጥቃት አውግዘው፣ የኢትዮጵያ መንግሥትንና ሕዝብ የሐዘን መግለጫ አቅርበዋል፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር እስካሁን ከአሥር ጊዜ በላይ በግንባር መነጋገራቸውን ገልጸው፣ ሁሉም ንግግሮች በመግባባትና በመተማመን ላይ መካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጊዜው ወደፊት የሚገለጽ ሆኖ፣ ግብፅን እንዲጎበኙ ፕሬዚዳንት አልሲሲ እንደጋበዟቸው ተጠቁሟል፡፡  reporter

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy