CURRENT

የዳያስፖራውን ተሳትፎ ከፈዘዘበት የማንቂያ ደውል

By Admin

April 30, 2017

በተለያዩ የዓለም ሀገራት ተበትኖ የሚኖረው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ  ቁጥር ከሶስት ሚሊዮን በላይ እንደሚገመት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። የዚህ ማህበረሰብ ሀገራዊ  የልማት ተሳትፎ ከአስርት ዓመታት በፊት እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መነቃቃት እየታየበት ነው። ያም ሆኖ ግን ዲያስፖራወ ካለው የቁጥር ብዛት አንፃር በኢንቨስትመንት፣ በእውቀትና በቴክኖሎጂ ሽግግር  እንዲሁም ገንዘብ ወደ አገር ውስጥ በህጋዊ መንገድ በማስተላለፍ እና ሀገሪቱን በመደገፍ ረገድ ዛሬም ገና ዳዴ በማለት ላይ ነው ለማለት ይቻላል።

ይህንን የዳያስፖራ  ተሳትፎ ከተኛበት በማንሳት ለማቀላጠፍና መስመር ለማስያዝ  በ 2004 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ባለፉት አምስት ዓመታት ማህበሩን ፈር ከማስያዝ ጎን ለጎን የዳያስፖራውን ልማት በማስፋፋቱም ረገድ ብዙ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። ማህበሩ በቅርቡ  ባካሄደው አጠቃላይ ስብሰባ ቀዳሚዎቹን የቦርድ አባላት አሰናብቶ አዳዲስ አባላትንም ሾሟል። በእለቱ የተገኙት ተሳታፊዎች  ማህበሩን በማጠናከርም  ሆነ  ዳያስፖራውን በማሰባሰቡ በኩል ከአዲሶቹ ተመራጮች ብዙ እንደሚጠበቅ  ነው የተናገሩት።

«በኢትዮጵያ ዳያስፖራውን የማሳተፍ ጅምር ቢኖርም  በቂ  አይደለም። ዳያስፖራው ካለው ቁጥርና ሊሰራ ከሚችለውም አንጻር  እንደ ሀገር ገና ብዙ ያልተጀመሩ ስራዎች ይቀሩናል። ይህን የማስተባበር ስራ የሚጠበቀው ደግሞ  ከአዲሶቹ ሹመኞች ነው» ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡን  በሀገረ አሜሪካ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ገነት ሀይሉ ናቸው።

ወይዘሮ ገነት ያለፉትን ሃያ ዓመታት በኖሩባት አሜሪካ የሚገኙ ብዙ ኢትዮጵያኖችን ወደ ሀገራቸው ፊታቸውን በመመለስ በኢንቨስትመንት፣ በእውቀትና በሌሎችም የልማት ዘርፎች እንዲሳተፉ ማድረጋቸውን ይገልፃሉ። ብዙዎችም በቀጣይም ወደ አገር ቤት መጥተው በተለያዩ የልማት  ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት አላቸው። ሆኖም ግን ይላሉ ወይዘሮ ገነት  ዳያስፖራው ሀገር ቤት ስላለው ሁኔታ በቂ መረጃ የለውም። በአብዛኛው ዳያስፖራ ስለሀገሩ እየሰማ ያለው ጥሩ  ወሬም አይደለም። እዛ ሆኖ የሚሰማውና እዚህ መጥቶ የሚታየው ነገር  በጣም የተለያየ ነው። ስለዚህ በውጭው ዓለም ላለው ዳያስፖራ በቂና እውነተኛውን መረጃ ማድረስ የማህበሩ ሃላፊነት ነው። ማህበሩ የተቋቋመበትም አንዱ አላማ ይሄው ነው። በመሆኑም አዲሶቹ ተመራጮች በዚህ በኩል የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረው ሊሄዱ ይገባል ይላሉ።

ወይዘሮ ገነት  ጨምረው እንደተናገሩት  ውጭ ካሉትም ዳያስፖራዎች መካከል አንዳንዶቹ  በሀገር ውስጥ ጥሩ ያልሆነ  ነገር እንዳለ በማስወራት እንቅፋት የሚፈጥሩ አሉ። አንዳንዴ ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ ቤተሰብ እንኳ መጠየቅ እንደማይቻል ተደርጎ ይወራል። በመሆኑም መንግስት በዳይስፖራው ማህበረሰብ ላይ ያለውን አመለካከትና  እያካሄደ ያለውንም  የልማት ስራ በማስተዋወቅ  ከመንግስት ጋር ያለውን ክፍተት ለማጥበብ መስራት ይጠበቅበታል። የማስተባበሩንም ስራ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰኑ በየሀገሩ ላሉትም ዳያስፖራዎች ተደራሽ መሆን ያስፈልጋል። ስለዚህም ተመራጮቹ የማህበሩ አባላት አዳዲስ አካሄዶችንም በመፍጠር  መንግስትንና ዳያስፖራውን የማገናኘት ሀገራዊ ሃላፊነት አለባቸው ሲሉ አስረድተዋል።

በሲውዘርላንድ ነዋሪ የሆኑት አቶ ፀጋዬ አስፋው በበኩላቸው  እንዳሉት ማህበሩ ገና ጅምር ነው። ባለፉት ዓመታት  በተሰሩ ስራዎች የማህበሩን ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ለመለየት ተችሏል። በመሆኑም አዲሱ አመራር ደካማዎቹን ጎኖች  በማስወገድ ጠንካራዎቹን ማስቀጠል ይጠበቅበታል።

እንደ አቶ ፀጋዬ አስተያየት አሁን ያለው የማህበሩ አባል ቁጥር በውጭ ከሚኖረው ኢትዮጵያ  እንዲሁም ወደ ሀገሩ ከተመለሰውም አንጻር   እጅግ ዝቅተኛ ነው። በመሆኑም ማህበሩ ሀገር ቤት ያሉትን በማሰባሰቡና አባል በማድረጉ በኩል  ትልቅ ስራ የሚጠበቅበት ነው የሚሆነው።

«በልማቱም በመሳተፉ በኩል ከሌላ ሀገር የመጡ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ብዙ እድሎችን እየተጠቀሙ ነው። እኛ ቀስ በቀስ ተመልካች እየሆንን ነው ያለነው። ይሄ  በጣም አሳሳቢ ነው። ከህንድ ከየመን እንዲሁም ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ኢንቨስተሮች እየገቡ ነው ወደፊት  ቦታም ሆነ ሌሎች ሁኔታዎች  እየጠበቡ ነው የሚሄዱት። እኔ የምሰራበትን  የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ጨምሮ ብዙ በኢንቨስትመንት የሰለጠነና ከፍተኛ ሙያ ያለው ኢትዮጵያዊ በየሀገሩ ይገኛል። እንዲሁም በየሀገራቱ የተበተኑ  ብዙ ዶክተሮችና ኢንጂነሮች አሉ። እነሱን የመሳብ ስራም  የሚጠበቅ ይሆናል፡፡»

እንዲሁም በመንግስት በኩል ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሌሎች ብዙ ስራዎች አሉ ስለዚህም ለዳያስፖራው በቂ መረጃ እንዲያገኝ በማድረግ፣ በአገር ውስጥ ምቹ የስራ ሁኔታዎችን በመፍጠር ፤መንግስት ወደእኛ ይምጣ ማለት አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም ማህበሩ መሃል ላይ ሊቆም መንግስትና ዳያስፖራውን በማቀራረብ  ሚናውን መወጣት ይገባዋል። በአጠቃላይ አዲሶቹ ተመራጮች ዳያስፖራው ወደ ሀገሩ የሚመጣው ዘመድ ለመጠየቅና ለመዝናናት ብቻ እንዳይሆን የማድረግ ሃላፊነትም አለባቸው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

«አዲሶቹ ተመራጮች ዳያስፖራው ወደሀገሩ ለመምጣት ሲሞክር የሚገጥሙትን ችግሮች በየወቅቱ ለመንግስት በማቅረብ  የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ  ማድረግ ቀዳሚ ስራቸው ሊሆን ይገባል» የሚሉት ደግሞ  ሌላው  በአሜሪካ  ነዋሪ የሆኑት የማህበሩ አባል  አቶ ዮሴፍ ገብረማርያም ናቸው።« ዳያስፖራው ሀገርህን አልማ ተብሎ ሊነገረው አይገባም፤ይሄን ማድረግ እንዳለብን ሁላችንም ይገባናል» የሚል መልዕክት  አላቸው።

መደረግ ያለበትና ከማህበሩ አመራሮችም የሚጠበቀው ዳያስፖራው ወደ ሀገሩ እንዳይመለስ ያደረጉትን ችግሮች በመለየት መፍትሄ ለሚሰጠው አካል ማቅረብ ነው። አብዛኛዎቹ ዳያስፖራዎች ይኖሩበት የነበረው የተሻለ ዴሞክራሲ ባለበትና የቢሮክራሲ ውጣ ውረዶች በማይኖሩበት ሁኔታ ነው። ወደ አገር ቤት ሲመጡ ትንሹም ትልቁም ነገር ሊያበሳጫቸው ይችላል። ይሄ በወቅቱ ለመንግስት መድረስ አለበት። ይሄን ለማድረግ  ደግሞ የማህበሩ አመራሮች  ከፍተኛ ሃላፊነት አለባቸው። ለዚህም በመንግስትና በዳያስፖራው ማህበረሰብም መካከል ተከታታይነት ያለው  ውይይት ማድረግ ይጠበቅበታል።    ሌላዋ አስተያየት ሰጪ  በሳውዲ አረቢያ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሀያት አምር አህመድ በበኩላቸው «ቀዳሚዎቹ የማህበሩ የቦርድ አባላት ብዙ ሰርተዋል። ዳያስፖራው ማህበረሰብም  በመንግስት በኩል እውቅና  እንዲያገኝና ትኩረት እንዲሰጠው አስችለዋል። ከአዲሶቹም የሚጠበቀው ይሄንን  በተሻለ ሁኔታ ማስቀጠል ነው።»

እንደ ወይዘሮ ሀያት አስተያየት ያለፉት የቦርድ አባላት ጀማሪ ቢሆኑም ጥሩ መሰረት አስቀምጠዋል።  ዳያስፖራው  እንደ ያለበት ሀገርና እንደየጉዳዩ የተለያየ ፍላጎት ስላለው  የማስተባበሩ ስራ  አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ቢሆንም ግን ተመራጮቹ ለገንዘብ ሳይሆን ህዝብን ለማገልገል የመጡ ስለሆነ  ይሄንን ያደርጋሉ የሚል ተስፋ አለን። የበፊቶቹ አመራሮች በተደጋጋሚ በያለንበት እየመጡ ሲያወያዩን ቆይተዋል። የአሁኖቹም ለሁሉም ጆሮ ሰጥተው የሚያዳምጡና  ለየችግሩ አብሮ በመቆም መፍትሄ የሚያፈላልጉ  ሊሆኑ ይገባል የሚል አስተያየት አላቸው።

በእለቱም  ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኙት  የዳያስፖራ   ጉዳይ  አስተባባሪ አቶ ሚካኤል ጦቢያ  እንደተናገሩት  በመንግስት በኩል ማህበሩንም ሆነ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራውን ጉዳይ በተመለከተ በዳይሬክቶሬት ጀኔራል ደረጃ  አንድ ክፍል አዋቅሮ በመስራት ላይ ነው። በዚህም ዳያስፖራውን በተመለከተ የወጡ ፖሊሲዎችን ለማስፈጸም  እንዲረዳ ህጎች በየደረጃው በመረቀቅ ላይ ናቸው። ዳያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ ይመለከተኛል ብሎ ሊሳተፍ ይገባል ያሉት አስተባባሪው ሀገሪቱ የምታካሂደውን ልማትም  ለማፋጠን ጉልህ ድርሻ እንዳለው በማስታወስ። ይህን ማድረግ ደግሞ የማህበሩ ሃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።  ኃላፊው ጨምረውም ማህበሩ ለሚሰራቸው ስራዎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን ሌሎች  ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርጉ  ነው ያስገነዘቡት።

የዳያስፖራው ማህበር ዳያስፖራውን ከፈዘዘበት በማንቃት በአገሩ የልማት ጉዳይ በያገባኛል መነፈስ እንዲሳተፍ የማንቂያ ደውሉን  በተከታታይ ማሰማት ይጠበቅበታል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ