Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዳያስፖራውን የልማት ክንድ የመዘነ ፕሮጀክት

0 629

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ይፋ መሆንን ተከትሎ በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን አሻራ ለማኖር በየሚኖሩበት አገር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋም የፋይናንስ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ድጋፍ በማሰባሰብ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ፕሮጀክቱ የዳያስፖራ አባላት የፖለቲካ፣ የብሔርና የሃይማኖት ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በኢትዮጵያዊነት መንፈስ የጋራ መግባባት እንዲፈጥሩ ማስቻሉም በመረጃው ተመላክቷል። በመሆኑም የዳያስፖራው ማህበረሰብ ለህዳሴ ግድቡ ያበረከተው አስተዋፅኦ ምን ነው? ምን ተሰርቶ ምን ቀረ የሚመለከታቸው አካላት ይናገራሉ።

በሚኒስቴሩ የዳያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ደመቀ አጥናፉ እንደሚናገሩት፤ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዢ፣ በስጦታ፣ በሙያ እና በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህም በአገራቸው እድገትና ብልጽግና የድርሻቸውን እንዲወጡ ዕድል የፈጠረ አገራዊ ፕሮጀክት ነው፡፡ በዚሁ  መሠረት ለግድቡ ግንባታ እስካሁን በቦንድ ግዥና በስጦታ 41ነጥብ2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አድርጓል፡፡

የዳያስፖራ ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ አብረሃም ስዩም በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ በመላው ዳያስፖራ ማህበረሰብ ብሔራዊ አንድነት የፈጠረና በአንድነት ያሰባሰበ አገራዊ ፕሮጀክት ነው። በዚህም ዳያስፖራው በገንዘብ ልገሳና በቦንድ ግዢ የድርሻውን አበርክቷል፤ እያበረከተም ይገኛል። የዳያስፖራ ቀን ሲከበር ይህን መሰባሰብ ምክንያት በማድረግ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ጉባ ድረስ በአካል ተገኝቶ ጎብኝቷል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የህዳሴ ግድቡን በመደገፍ ረገድ ከዳያስፖራው ሊገኝ የሚገባውን ያህል ድጋፍ ማግኘት ባለመቻሉ በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረሥላሴም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። ይሁን እንጂ ጠንከር ያለና ተከታታይ የማስተዋወቅ ሥራ ባለመሰራቱ አሁን ከተገኘው ድጋፍ በላይ ማግኘት አለመቻሉን በቁጭት ይናገራሉ። ሆኖም ከዚህ በላይ መሄድ ይቻል ነበር፡፡

«በአገር ውስጥ ደሃዋ እናትና ጉልት የምትሠራው ሴት እንኳን ብዙ ዓይነት ድጋፍ እያደረገች ነው። ከዚህ አኳያ ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ብዙ ይጠበቃል፡፡ የማይካደው ግን ዳያስፖራው እስከ አሁን በእውቀቱና በገንዘቡ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ የሚያበረታታ ነው። የመካከለኛው ምሥራቅ ዳያስፖራ ማህበረሰብ ደግሞ የላቀ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ዳያስፖራው በአብዛኛው እየተንቀሳቀሰ ያለው በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ ብቻ በመሆኑ ሌሎች አማራጮችን በቀጣይ መጠቀም እንደሚገባ ይመክራሉ።

አቶ ደመቀ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ከፋይናንስ ድጋፍ በተጨማሪ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የዲፕሎማሲ ሥራ እያከናወነ እንዳለ ይናገራሉ፡፡ በሚኖሩባቸው አገሮች ለሚገኙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት፣ ለከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ ለፓርላማ አባላት፣ ለሲቪክ ማህበራት፣ ለታዋቂ ሚዲያዎችና ሌሎች አካላት ገለጻና ማብራሪያ በመስጠት የግድቡ ግንባታ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለታችኛው ተፋሰስ አገራት ጭምር በሚሰጠው ጠቀሜታ ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እያከናወኑ እንዳለ አመልክተዋል። በምህንድስና ሙያ የተሰማሩ ምሁራንም ማህበር በማቋቋም በየደረጃው አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንዳሉ አቶ ደመቀ ያብራራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና በዘርፉ ተመራማሪ ዶክርተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ እንደሚገልጹት፤ ቀደም ሲል ዳያስፖራው በአገሩ ልማት በቀጥታ የሚሳተፍበት ዕድል የፈጠረ ፕሮጀክት ባለመኖሩ ግድቡ የዳያስፖራውን ቀጥተኛ ተሳትፎ በዘላቂነት ያረጋገጠ የመጀመሪያ ፕሮጀክት ነው፡፡ በመሆኑም በዲፕሎማሲውም ሆነ በገንዘብ ማዋጣቱ ረገድ ጥሩ ጅምር መኖሩን መታዘባቸውን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ዳያስፖራዎች በሚኖሩበት አገር መሳተፍ የሚችሉት ገንዘብ በማዋጣት ወይም የህዳሴውን ቦንድ በመግዛት ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ላይ አሁን ካለው የማስተዋወቅና ተደራሽ የመሆን አቅም በበለጠ በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትኩረት ሊሰራ ይገባል።

አቶ አብረሃም እንደሚሉት፣ ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ማግኘት የሚገባውን ያህል ለማግኘት ከመቼውም ጊዜ በላቀ የተቀናጀ ሥራ መስራት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጥረት ውስጥ ከዳያስፖራው ምን እንደሚጠበቅ ለይቶ በማሳወቅ በተሳትፎም ሆነ በድጋፉ ረገድ የአገሩ ዲፕሎማት ሆኖ ዘላቂ ሥራ እንዲሰራ የማስተዋወቅ ሥራው ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

እንደ ወይዘሮ ሮማን አስተያየት፣ የዳያስፖ ራውን ተሳትፎ በተመለከተ እስከአሁን በተሰራው ሥራ በቂ ልምድ ተገኝቷል፡፡ ይህም ባሉበት አገር ቦንድ እንዲገዙ የማይፈቀድ ከሆነ እንደየአገሩ አሠራርና ሁኔታ በማስተሳሰር በተለያዩ አማራጮች ሥራውን መስራት ይቻላል የሚለው መልዕክታቸው ነው። ከዚህ አንጻር የቶምቦላና መሰል የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎችን ለማካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቆ ሥራዎች እየተሰሩ ነው።

አቶ ደመቀም ይሄን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ዘንድሮም ቀኑ ከዳያስፖራው ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ እና ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር በሁሉም የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በተለያዩ መርሃ ግብሮች ይከበራል፡፡ አምና በዕለቱ ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ተገኝቷል፡፡ ዘንድሮም ከዚህ በላይ ይጠበቃል፡፡ ይሄን ተሳትፎውን ለማጠናከርም አማራጭ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራ ይሰራል ብለዋል። ከእነዚህም ውስጥ ለዳያስፖራው የሚሆን በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች የመኖሪያ ቤት የሚያስገኙ የቶምቦላ ሎተሪዎች ለማዘጋጀት በእቅድ ተይዟል።

ከዳያስፖራው መገኘት ያለበት ድጋፍ ማህበሩ እየሰራ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አብረሃም፤ በግድቡ ዙሪያ በተዘጋጁ ዘጋቢ ፊልሞች ውስጥ ጉልህ ድርሻ የነበራቸው የዳያስፖራ አባላት እንዲካተቱ በማድረግ በመላው ዓለም የሚኖረው ዳያስፖራ ስለ ህዳሴ ግድቡ መረጃ በማግኘት ተሳትፎና ድጋፉን እንዲያጠናክር የማነሳሳት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል፡፡ በርካታ ቁጥር ያለውን ዳያስፖራም ቦታውን እንዲጎበኙ መደረጉን፤ ይህም የዳያስፖራው ማህበረሰብ በወሬ ከሚሰሙት ይልቅ ሥራውን በዓይናቸው አይተው እንዲያምኑ እና እንዲነሳሱ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዳያስፖራው የሚጠበቀውን ለማግኘት ዳያስፖራውን ማስተባበር የኤምባሲዎች ቁልፍ ሥራ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ደመቀ ኤምባሲዎቹ ንቅናቄን ሊፈጥር በሚችል መልኩ ከተለያዩ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ጋር እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለዘንድሮው በዓል የህዳሴ ግድቡን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያሳይ ቪዲዮ ለዳያስፖራው እንዲደርስ ለሁሉም ሚሲዮኖች መላኩን አስታውሰዋል፡፡

«ዳያስፖራውን በሁለት ቦታ ከፍሎ ማየት ይገባል» የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ አንዱ ጎራ በጣም ጥቂት የሆኑት ኢትዮጵያ እርዳታ እንዳታገኝ የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮችን እያነሱ የሚሰብኩ ናቸው። በሌላ ጎራ ደግሞ አገሩን የሚወድና «በማንኛውም መንግሥት ቢሆን የሚከናወነው ልማት አገርን ማልማት ነው» ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱንም ጎራ በማቀራረብ ስለአገራቸው ተገቢውን ግንዛቤ ይዘው በልማቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር የሚሰራው ሥራ አናሳ በመሆኑ በተለይ መንግሥት በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባ መክረዋል።

ወንድወሰን ሽመልስ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy