NEWS

የግድቡ ግንባታ ለጋራ ተጠቃሚነት አርቆ አሳቢነትን ያበሰረ ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

By Admin

April 03, 2017

የግድቡ ግንባታ ለወዳጅና ጎረቤት ሃገራት የጋራ ተጠቃሚነትንና አርቆ አሳቢነትን ያበሰረ መሆኑን የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

የግድቡ ግንባታ የተጀመረበት ስድስተኛ ዓመት ክብረ በዓል በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉባ ወረዳ “የታላቁ ህዳሴ ግድባችን የሀገራችን ሕብረ ዜማ የህዳሴያችን ማማ” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ ተከብሯል።

አቶ ደመቀ በዚህ ጊዜ እንዳሉት፥ የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን የሃይል ፍላጎት ጥያቄ ከመመለስ ባሻገር የምስራቅ አፍሪካ ሃገራትን የኃይል ፍላጎት የሚያሟላና የአካባቢውን ስነ ምህዳር የሚጠብቅ ጉልህ አህጉራዊ ፕሮጀክት ነው።

በኢትዮጵያውያንና በመንግስት ሃብት እየተገነባ ያለው ይህ ግድብ በብዙ መንገድ ለጋራ ጥቅም እንደምንሰራ ያረጋግጣልም ብለዋል አቶ ደመቀ።

የህዳሴውን ግድብ ከዳር ለማድረስ ህብረተሰቡ በተለያዩ መንገዶች ተግባራዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፥ የክልሎች እየተዘዋወረ ያለው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ከ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማስገኘቱን አንስተዋል።

ግንባታው የፈጠረው ሃገራዊ ንቅናቄ ከግድቡ አልፎ በሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችም በህዝቡ ዘንድ ዳር የማድረስ ቁጭት እንዲፈጥር አድርጓልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አዜብ አስናቀ በበኩላቸው፥ ግድቡ በሃገሪቱ እየጨመረ የመጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው የላቀ ትኩረት በርካታ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው እየተሰሩ ነው ያሉት ስራ አስፈጻሚዋ፥ የህዳሴው ግድብም ዋነኛ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እንደሚሆን ገልጸዋል።

ከኢንዱስትሪ ፓርኮችና ግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ግንባታ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሃይል ፍላጎቱ በዚያው ልክ በየአመቱ እያደገ በመሆኑ ግድቡ ክፍተቱን በመሙላት የማይተካ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

የግድቡ ግንባታ በተደረገለት የማሻሻያ ሥራ ኃይል የማመንጨት አቅሙ ወደ 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት ከፍ ማለቱን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።