Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጎርፍ ስጋት እንቅልፍ የነሳቸው ነዋሪዎች

0 723

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ቀበና ወንዝ አካባቢ ተገኝቻለሁ፡፡ በወንዙ ዳርና ዳር ከትልልቅ ዛፎች እስከ ትንንሽ ቁጥቋጦዎች ይታያሉ፡፡ በዛፎቹ መካከል ወንዙ የሸረሸረው ገደል አፋፍ ላይ የተሰሩት ቤቶች ውስጥ «ከነገ ዛሬ በጎርፍ እንወሰዳለን» በሚል ስጋት የሚኖሩ ሰዎች አሉ፡፡

የአካባቢው ነዋሪዋ ወይዘሮ አዛለች አስፋው በሰማይ ላይ ደመና በዞረ ቁጥር በቤት ውስጥ መቀመጥ እንደሚጨንቃቸው ይናገራሉ፡፡ «በሌሊት ዝናብ ከጣለ እንቅልፍ አልተኛም፤ ወንዙ ከፍተኛ ድምጽ ባሰማ ቁጥር ከአሁን ከአሁን ወደቤት መጣ እያልኩ እጨነቃለሁ» ይላሉ፡፡ የቤታቸውን መሠረት የያዘው አፈር በጎርፍ እየተጠረገ በሂደት የቤቱን ደረጃ ለመዋጥ ተቃርቧል፡፡

አሁን አሁን ወይዘሮ አዛለችም ሆኑ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ሕፃናትን በቤት ውስጥ አስቀምጦ መሄድ የምጥ ያህል እየከበዳቸው ነው፡፡ ሌላኛዋ የዚሁ አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ ዓለምነሽ ታደሰ እንደሚሉት፤ አሁን የበጋ ወቅት ቢሆንም ክረምት ላይ ጎርፍ እስከ ደጃፋቸው ድረስ የሚመጣ በመሆኑ አደጋ ያጋጥመናል የሚል ስጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡

ወይዘሮ ገነት ካሳ የተባሉ ነዋሪ በበኩ ላቸው እንደተናገሩት፤ አካባቢው ወንዝ ዳር መሆኑ ከሚያመጣባቸው ጎርፍ ባሻገር የወረዳው ነዋሪ ሁሉ ቆሻሻውን የሚጥለው በዚያው ስፍራ በመሆኑ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ተዳርገዋል፡፡ በሌላ በኩል ከየመንደሩ የሚወጣው ፈሳሽ ቆሻሻ የሚገ ባው በዚያው ወንዝ ላይ መሆኑ ደግሞ ችግሩን አባብሶታል፡፡

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ አየር ጤና አካባቢ ከሚያልፈው ወንዝ ዳር የሚገኙ ነዋሪዎችንም በተመሳሳይ ተዘዋውሬ አነጋግሬአለሁ፡፡ በወንዙ ዳርና ዳር ጎጇቸውን ከቀለሱ ነዋሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሁሴን አሊ ጎርፉ ሲከሰት ከወዲሁ ለመከላከል ታሳቢ አድርገው አፈር በማዳበሪያ እየሞሉ ሲደለድሉ ነው ያገኘኋቸው፡፡

ግለሰቡ በችግሩ ዙሪያ ሲጠየቁም «ምን ማድረግ እንዳለብንም አናውቅም፡፡ እኛ እየኖርን ያለነው ፈጣሪን እየለመን ብቻ ነው፡፡ እኔ ለሚመለከተው አካል አቤት የምልበት ጊዜ እንኳን የለኝም፡፡ የምኖረው የቀን ሥራ እየሰራሁ ነው፡፡ ለአንድ ጉዳይ አመልክቶ መፍትሔ ለማግኘት ረጅም ቀን ይወስዳል፡፡ ለዚያውም ምፍትሔ የሚገኝ ከሆነ ነው፡፡ አንድ ቀን ሥራ ብፈታ ቤተሰቤ ፆሙን ነው የሚያድረው» በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በቦታው ላይ ለስምንት ዓመታት መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ሁሴን ዝናብ በመጣ ቁጥር ከወንዙ ውስጥ አሸዋ በማውጣትና አፈር በማዳበሪያ በመሙላት ለመከላከል ጥረት እንደሚያደርጉ ነው የሚጠቁሙት፡፡ ለሚመለከተው አካል አቤት ቢሉም ምላሽ እንደማይገኝ ስለተረዱም ምርጫቸው ያደረጉት ይህንኑ የመከላከል ዘዴ በመጠቀም የሚመጣውን መጠበቅ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የጎርፍ ስጋት ያለባቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ለመታደግ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ተጠይቀው እንደተናገሩት፤ የነዋሪዎቹ ጉዳይ ገና በጥናት ላይ ያለ ነው፡፡ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች መንስኤና እንዴት መከላከል እንደሚቻል ከክፍለ ከተማና ከወረዳ አካላት ጋር በመሆን ለመስራት ታቅዷል፡፡ በዋናነትም ተጋላጭ አካባቢዎች የተለያየ ባህሪ ስላላቸው በዝርዝር እንዲጠኑና ወደ መፍትሔ እንዲገባ ከክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አዳነ አብርሃ በበኩላቸው እንዳመለከቱት፤ ጥናቱ ገና ባይጠናቀቅም እስካሁን 32 አካባቢዎች ለአደጋ ተጋላጭ ሆነው ተለይተዋል፡፡ የጎርፍ ተጋላጭነታቸውም በጣም ከፍተኛ፣ ከፍተኛና መካከለኛ ተብሎ የተለየ ነው፡፡ በጣም ከፍተኛ ተብለው የተለዩት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10፣ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7፣ በዚያው በየካ ክፍለ ከተማ ላምበረት አካባቢ፣ ኮልፌ ቀራንዮ ወረዳ 1 ረጲ አካባቢዎች ናቸው፡፡

እንደ አቶ አዳነ ገለጻ፤ እነዚህ አካባቢዎች ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑት በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ነው፡፡ በተለይም በሰው ሰራሽ ምክንቶች የቱቦዎች በቆሻሻ መደፈንና የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት መዛባት ይጠቀሳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በወንዝ ዳር የሰፈሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስላሉ እነዚህም ለጎርፍ ይጋለጣሉ፡፡

በወንዝ ዳር የሰፈሩ ነዋሪዎች አደጋ ከመድረሱ በፊት የሚመለከተው አካል ቦታ እንዲያመቻች ላቸው አቶ አዳነ ያሳስባሉ፡፡ በሌላ በኩል ኅብረተሰቡ የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓትን በአግባቡ ቢጠቀም መፍትሔ እንደሚሆን ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ባለሥልጣኑ ከወረዳዎች ከሚመለከታቸው አካላትና ከኅብረተሰቡ ጋር እየሰራ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡

በቀበና ወንዝ አካባቢ ስላሉ ነዋሪዎችና በወረዳው ምን እየተሰራ እንደሆነ ለማወቅ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 አስተዳደር ጋዜጣው ማተሚያ ቤት እስከገባበት ዕለት ድረስ በአካልም ሆነ በስልክ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሊሳካልን አልቻለም፡፡

 ዋለልኝ አየለ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy