Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጎንደር ነዋሪዎች እሮሮ ዛሬም አልተፈታም

0 467

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የከተማዋ መንገዶች ዕድሜ ጠገብ መሆናቸው፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግሩ ዛሬም ድረስ መዝለቁ፣ የከተማዋ ዕድገት የቀጨጨ መሆኑ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሩ ስር እየሰደደ መምጣቱንና ሌሎችን ጉድለቶች በማሳያነት በመጥቀስ ከተማዋን መንግስት ረስቷታልብለው እንደሚያምኑ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

አቶ ታደሰ ፋንታሁን በጎንደር ከተማ ደብረብርሃን ስላሴ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ጎንደር ታሪካዊ ከተማ ብትሆንም ዕድገቷ ግን አዝጋሚ ነው ይላሉ። «አብዛኛዎቹ ህንፃዎችና መንገዶች በጣሊያን ጊዜ የተሰሩ ናቸው። በጎንደር ህዝቡ በትራንስፖርት፣ በውሃና በኑሮ ውድነት እየተቸገረ ነውሲሉ ነግረውናል።

ማረሚያ ቤቱ ከከተማው ይርቃል። ዘመድ አዝማድ የታሰረበት ሰው ሄዶ ለመጠየቅ ሁሌም በትራንስፖርት እጦት ይቸገራል። መንገዱም ውጣ ውረድ የበዛበት ነው። ስለዚህ መንገዱም ሊስተካከል፤ ሲጠጣ ገንዘብ የሌለው ለውሃ ጥምና እንግልት እየተደረገ ነው። ስለዚህ መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል።

«የምንኖርበት አካባቢ በከተማው አስተዳደር ስር ቢሆንም እስካሁን ድረስ የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ አይደለንምየሚሉት አቶ አለኸኝ፤ ለማብሰያም ሆነ ለብርሀን እየተገለገሉ ያሉት አገዳ መሆኑን በመግለጽ፤ ችግሮቹ ተለይተው መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል። ትራንስፖርትም ሊመደብ ይገባልሲሉም ነው የትራስፖርት ችግሩን የገለጹት።

በዚሁ ከተማ የቀበሌ19 ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ገዳምነሽ ማሞ የውሃ ችግሩ ከአቅም በላይ መሆኑን ያነሳሉ። ውሃ በአምስት ቀናት አንድ ቀን ነው የምናገኘው። ይህም ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት ዳርጎናል። የከተማ አስተዳድሩም በቆላድባ ወረዳ እየተገነባ የሚገኘው የጎድጓድ ውሃ በመጠናቀቅ ላይ በመሆኑ ችግሩ በዛላቂነት ይፈታል የሚል ምላሽ ሰጥቶናል። ያንን ቀንም በጉጉት እየተጠባበቅን ነንሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።

አቶ አለኸኝ ሙሉዓለም ደግሞ በሚኖሩበት በአርበኞች አደባባይ ክፍለ ከተማ ስር የሚገኘውንና በተለምዶ ወለቃ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ያለውን የመንገድና ውሃ ችግር ይጠቅሳሉ። መንገዱ ለትራስፖርት ምቹ አይደለም።በዚህ የተነሳ ህዝቡ እንደፈለገው ወጥቶ መግባት አልቻለም።የውሃ ችግርም ህዝቡን ያማረረ ጉዳይ ሆኗል። ህዝቡ በአማራጭነት የአንገርብ ወንዝን እንዳይጠቀም እንኳን ደርቋል። በዚህ የተነሳ ሰዎችም ሆኑ እንሰሳዎች የሚጠጡት ውሃ የለምነው ያሉት።

እርሳቸው እንዳሉትም፤ የከተማ አስተዳደሩ ውሃ በመኪና ማቅረብ ቢጀምርም በቂ ስላልሆነ ለሁሉም ህዝብ ሊዳረስ አልቻለም። በዚህም ምክንያት ወለቃ አካባቢ ህዝብ የሰው ያለህ እያለ ነው። ገንዘብ ያለው ውሃ ገዝቶ እየተጠቀመ እንደሆነ አመልክተዋል።

«ጎንደር ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ታሪክ ያላት፣ የንግድ፣ማዕከልና የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ ናትየሚሉት አቶ አየልኝ ገዳሙ ደግሞ፤ እንደ ዕድሜዋ መንግስት ዕገዛ ቢያደርግላት ኖሮ ታድጋለች፤ ነዋሪዎቿም ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር የሚል እምነት አላቸው። አሁንም ጊዜው አልረፈደም ብዙ መስራት ይጠይቃል እንጂ» ሲሉ ሀሳባቸው ቋጭተዋል።

አቶ እንድሪስ ታደሰ የተባሉት የከተማዋ ነዋሪም የአቶ አየልኝ ሀሳብን ይጋራሉ። ጎንደር ውስብስብ ችግር እንዳለባት ጠቅሰውም እንደ ንግድና ቱሪስት መዳራሻነቷ በመንግስት እገዛ ቢደረግላት ኖሮ የተሻለች ከተማ ትሆን ነበር ሲሉ ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባው አቶ ተቀባ ተባበል ነዋሪዎች ያነሷቸውን ቅሬታዎች ተገቢነት ይቀበላሉ። አስተዳደሩም ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፀው፤ መንገድን በተመለከተ የመጠገንና የመስራት ጅምር ስራዎች መኖራቸውን አንስተዋል። በከተማዋ ያለውን የውሃ ችግር ለመፍታትም በቆላድባ ወረዳ ተገንብቶ እየተጠናቀቀ ያለው የጉድጓድ ውሃ መፍትሄ ይሆናል። በአሁኑ ወቅት የተወሰኑ የቴክኒክ ሥራዎች ናቸው የቀሩት፤ አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም አሁን 45 በመቶ የሆነውን የጎንደር ከተማ የውሃ ሽፋን ወደ 80 በመቶ እንደሚያሳድገውና የህዝቡ የቆየ ጥያቄ የሚመለስ መሆኑን ገልፀዋል ።

የመብራት ያልተዳረሰባቸው አካባቢዎችንም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ተጨማሪ የማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ እየተካሄ በመሆኑ ችግሩ በዘላቂነት ይፈታል ብለዋል። ከንቲባው በከተማዋ ያሉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እንደዘገዩ አምነው፤ ከአሁን ወዲህ ከህዝቡ ጋር በመተባበር ጥያቄዎችን ለመመለስ ሁለንተናዊ ጥረት ይደረጋል ብለዋል 

ጌትነት ምህረቴ ethpress

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy