POLITICS

የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነትን በሥርዓት የመምራት ጥያቄ

By Admin

April 01, 2017

ከወልቃይት የድንበርና የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዘው የተነሱ ውዝግቦች የበርካታ ዜጎችን ስሜት ቀስቅሰዋል፣ ትኩረትም ስበዋል፡፡ የትግራይና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት፣ የክልሎቹ ነዋሪዎች፣ የፌዴራል መንግሥቱና ሌሎች በጉዳዩ ላይ ፍላጎት ያሳዩ ግለሰቦችና አካላት የተነሳውን ጥያቄ ከታሪክ፣ ከፖለቲካ፣ ከሕግና ከባህል በመነሳት ተንትነዋል፡፡ በውዝግቡ ተሳታፊ ለሆኑ አካላት ከመወገን ተላቀው፣ ጉዳዩን ከመርህ አኳያ ለማየት የመረጡ በጣም ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ነበሩ፡፡

በዚህ ሁሉ መካከል የሁሉም ሰው ዓይን በፌዴራል መንግሥቱ ላይ በማረፉ ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጥና ተመሳሳይ ችግሮች ወደፊትም ሲፈጠሩ ለመቅረፍ የሚያስችል መርህና አሠራር እንዲዘረጋም ተጠብቆ ነበር፡፡ ይሁንና ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት በጉዳዩ ላይ የቀረበው የፌዴራል መንግሥቱ ግምገማና ትንተኔ ይበልጥ ጥርጣሬና ግራ መጋባትን የፈጠረ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የፌዴራል መንግሥቱ በሁለቱ ክልሎች ያሉ የፖለቲካ አመራሮች የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ ባይንቀሳቀሱ ኖሮ ወልቃይት የግጭት ምንጭ ሊሆን እንደማይችል ገልጿል፡፡ ከዚህ አቋም በመነሳት በግጭቱ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድልና ንብረት እንዲወድም በማድረግ ተሳትፎ ባላቸው አመራሮች ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድ መጠበቅ ተፈጥሯዊ ባህርይ ነው፡፡

ይሁንና ይህ ዕርምጃ ስለመወሰዱ ወይም እንደሚወሰድ ማረጋገጫ ሳይሰጥ፣ በኋላ ላይ የፌዴራል መንግሥት የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ተነጋግረው ችግሩን በጋራ እንደሚቀርፉት በይፋ ገለጸ፡፡ እርግጥ ነው ምክክር በራሱ የሚነቀፍ ድርጊት አይደለም፡፡ ነገር ግን ከተጠያቂነት ጋር ጎን ለጎን ካልፈተጸመ በሕዝብ ላይ ከደረሰው ጉዳትና ኃይል አንፃር እነዚህ ዕርምጃዎች በራሳቸው ተመጣጣኝ አይሆኑም፡፡ እንዲህም ሆኖ ውይይቶቹ የሚፈለገውን ውጤት እያስገኙ አይደለም፡፡ የወልቃይት ግጭት ከተከሰተ ዘጠኝ ወራት ቢሆንም የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጥያቄው የተነሳበት የወልቃት ክልል የሚገኘው በትግራይ ክልል በመሆኑ ጉዳዩ በትግራይ ክልል ይፈታል ብሎ የአማራ ክልል ይጠብቃል፡፡

በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል ያለው የድንበር ጥያቄ በእንጥልጥል ባለበት ወቅት፣ የኦሮሚያና የኢትዮ ሶማሌ ክልሎች በተመሳሳይ በድንበር የተነሳ ግጭት ውስጥ በመግባታቸው በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለውን የድንበር ማካለል ችግር ለመቅረፍ ሕዝበ ውሳኔ የተደረገው በ1998 ዓ.ም. ቢሆንም፣ ግጭቶቹ ግን ከነአውዳሚ ውጤታቸው ቀጥለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአስተዳደራቸውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት፣ ይህ ጉዳይ የፓርላማ አባላት ትኩረት ከሰጧቸው አጀንዳዎች አንዱ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለጉዳዩ ማብራሪያ የሰጡት ከወልቃይት ጥያቄ ጋር በማነፃፀር ነበር፡፡ ‹‹የድንበር ማካለል ችግሮች ለዓመታት እየተንከባለሉ የመጡ ናቸው፡፡ ሕዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች የነበረን ምላሽ አናሳ ነበር፡፡ ጥያቄዎቹ በወቅቱ ምላሽ ያላገኙት የነበረን አመለካከት የተበላሽ ስለነበር ነው፡፡ አመራራችን ውስጥ የጠባብነትና የትምክህተኝነት ችግር አለ፡፡ ሕዝቡ መጋጨት አይፈልግም፡፡ እየተጋጨ ያለው ሚሊሻ ከሚሊሻ ጋር፣ ልዩ ፖሊስ ከልዩ ፖሊስ ጋር ነው፡፡ ይኼን የሚያዘምተው ደግሞ ታች ያለው አመራራችን ነው፡፡ ደረጃው ቢለያይም ከዚህ ነፃ የሆነ ክልል ግን የለም፡፡ እነዚህ ግጭቶች ከብሔር ግጭት ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡

በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ካሉበት መሠረታዊና ሥር የሰደዱ ችግሮች አንዱ የግልጽነትና የተጠያቂነት አለመኖር መሆኑን ብዙዎቹ ይጠቅሱታል፡፡ ነገር ግን በፓርላማ ውሏቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደራቸው በሕገወጥ ተግባራት በተሳተፉ ግለሰቦች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሕዝቡን ያጋጩና ደም ያፋሰሱ አካላት በሕግ ይጠየቃሉ፡፡ በተፈጠሩት ግጭቶች ላይ በፌዴራል ደረጃ አንድም መረጃ አላመለጠንም፡፡ ማስረጃም አለን፤›› ሲሉም መፍትሔው በእጃቸው እንዳለ አመላክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቅርቡ በተካሄዱ የ‘ጥልቅ ተሃድሶ’ ስብሰባዎች ላይ በተፈጠረው መግባባት ችግሩ በዘላቂነት ይፈታል የሚል ፅኑ እምነት እንዳሳደረባቸውም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካና የደኅንነት ተንታኞች ስብሰባዎቹ ጉዳዩን በጥልቀት ከማየት ይልቅ፣ ከላይ ከላይ ገረፍ ገረፍ አድርገው በማለፍ ላይ ያተኮሩና ይልቁንም በመሬት ላይ ያለው ተጨባጭ እውነት ሥልት ባለው መንገድ እንዲደበቅና ክህደት በአደባባይ አክብሮት እንዲሰጠው እየተደረገ ነው ሲሉ ያማርራሉ፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የደኅንነት ተንታኝ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ የፖለቲካ አመራሮች ዕርምጃ ሳይወሰድባቸው በቃላት እየጫወቱ ቢሆንም፣ ሕዝቡ ግን ፍትሐዊ ባልሆኑ ውሳኔዎች እየተሰቃየ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የግጭቶቹ ተፈጥሮና ባህርይ እየተለዋወጠ ቢሆንም የአቶ ኃይለ ማርያም አስተዳደር ግን ለሁሉም ችግሮች የሚሰጠው መግለጫ ከአመራሮች ጠባብነትና ትምክህተኝነት ሊነፃ አልቻለም፡፡

‹‹የፌዴራል መንግሥት በሚያደርጋቸው ማንኛውም ዓይነት ጥረቶች ላይ የክልል መንግሥታት በበቂ ሁኔታ ካላመኑበት እንቅፋት መሆን ይችላሉ፤›› ያሉት ኤክስፐርቱ፣ ‹‹በሥራ ላይ ያለው ሥርዓት ለ20 ዓመታት ተሠርቶበት አሁንም ተመሳሳይ ችግሮች የሚታዩ ከሆነ ሥርዓቱ ሊከለስ ይገባል፡፡ ሥርዓቱ ችግሮችን በበቂ ሁኔታ እየቀረፈ ላለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ስለዚህ አዲስ መሣሪያዎችና አሠራሮች ያስፈልጉናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ከዚሁ ለአረጁና ላፈጁ ችግሮች መፍቻ አዲስ መንገዶችን ለመቀየስ ከሚደረገው ጥረት ጋር በተያያዘ የፌዴራሊዝም ኤክስፐርቶች የመንግሥታት የእርስ በርስ ግንኙነት ተቋማዊ እንዲሆንና ዝርዝር ሕግ እንዲወጣለት ለዓመታት ይጠይቁ ነበር፡፡ በቅርቡ የፌዴራሉ መንግሥት ይህንኑ የተመለከተ ረቂቅ ፖሊሲ እንዲዘጋጅና ለውይይት እንዲቀርብ አድርጓል፡፡

አሰፋ ፍስሐ (ዶ/ር) ተባባሪ ፕሮፌሰርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራል ጥናቶች ማዕከል ኃላፊ ናቸው፡፡ አሰፋ በረቂቅ ፖሊሲው ዝግጅት ተሳታፊ ናቸው፡፡ ‹‹ረቂቅ ፖሊሲው አሁንም ገና በሥራ ላይ ያለ ነው፡፡ የመጨረሻ ቅርፁን አልያዘም፡፡ ጉዳዩን ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅ እየሞከርን ነው፡፡ የመንግሥታት የእርስ በርስ ግንኙነት በሕገ መንግሥቱ በአግባቡ የተሸፈነ ጉዳይ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የመንግሥትን የእርስ በርስ ግንኙነት ተቋማዊ ማድረግ አዲስ ጥረት ነው፡፡ ይሁንና መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ ይኼው መርህ በተለያየ ደረጃ የተለያዩ ተዋናዮችን በማቀፍ ሲካሄድ ነበር፡፡ ዘመላክ አይተነው (ዶ/ር) የፌዴራሊዝም ኤክስፐርትና አካባቢያዊ አስተዳደሮች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩ ባለሙያ ናቸው፡፡ እንደ አሰፋ ሁሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራል ጥናቶች ማዕከል የሚሠሩት ዘመላክ፣ ‹‹የክልል መንግሥታት የጎንዮሽ ግንኙነት ያደርጉ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ለአብነት ያህል የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የአማራ ክልሎች የተለያዩ ተቋማት በተለይም የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ በቋሚነት በመገናኘት ይመክሩ ነበር፡፡ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ደቡብና ሐረሪም ተመሳሳይ መድረኮች ነበራቸው፡፡ እነዚህ መድረኮች የተካሄዱት የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶላቸው አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ይካሄዱ በነበሩ የመንግሥታት የእርስ በርስ ግንኙነቶች የፌዴራል መንግሥት ጉልህ ሚና ይዟል በማለት የክልል መንግሥታት ቅሬታ ያቀርቡ ነበር፡፡ የክልል መንግሥታት ድምፆች በአግባቡ አልተሰሙም የሚል ቅሬታ ነበር፡፡ ስለዚህ የክልል መንግሥታት የዚህ ፖሊሲ አካል እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረናል፡፡ በሒደቱ እኩል አጋሮች ሆነው ተወስደዋል፡፡ አጠቃላይ ሥርዓቱም በትብብር፣ በአጋርነትና በስምምነት በሚሰጥ የውሳኔ አሰጣጥ እንዲሆን አድርገናል፤›› ሲሉም አሰፋ አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ ዘመላክ ይህን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ የመንግሥታት የእርስ በርስ ግንኙነትን የሚመራ አንድ ሰነድ ክልሎቹ በሙሉ መተማመን የሚቀበሉት ሊሆን እንደሚገባ ይሞግታሉ፡፡ ለዘመላክ ይህ ሥርዓት በቁጥጥር አልያም በትብብር ይገለጻል፡፡ ‹‹ቁጥጥር አንዱን ከፍተኛ ሌላኛውን ዝቅተኛ በማድረግ ከፍተኛው ዝቅተኛውን እንዲከታተለውና ሲያስፈልግም በእንቅስቃሴዎቹ ጣልቃ እንዲገባ የሚያደርግ ነው፡፡ ትብብር በተቃራኒው በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ መንግሥታት መካከል በእኩልነት የሚደረግ ምክክር ነው፡፡ በዚህም መንግሥታትና ባለሥልጣናት ተገናኝተው በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ተነጋግረው ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሞክሩ መድረክ ይመቻቻል፤›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በቁጥጥር የሚገለጸውና ያልተፈለገ ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዘው አሠራር ክልሎች በአጠቃላይ ሥርዓቱን በጥርጣሬ እንዲያዩት አድርጓል፡፡ ይህ ሥጋት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የተገደበ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ የመንግሥታትን የእርስ በርስ ግንኙነት በሕግ የመግዛት ወይም ተቋማዊ ቅርፅ የመስጠት ጉዳይ አከራካሪ ነው፡፡ አንዳንዶች ሥርዓቱ ተፈጥሮአዊ ባህርይ ይዞ እንዲያድግ ከተፈለገ ከሕግ ማዕቀፍ ውጪ ቢካሄድ ይመረጣል ይላሉ፡፡ ዘመላክ፣ ‹‹እነዚህ ወገኖች ያላቸው አቋም የሕግ ማዕቀፍ ግንኙነቱን ግትር ያደርገዋል የሚል ነው፡፡ ይህም ተፈላጊውን ትብብር ሊከለክል ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው፤›› ብለዋል፡፡ ሌሎች ግን በተቃራኒ ለመንግሥት የእርስ በርስ ግንኙነት የሕግ ማዕቀፍ ማበጀት ሒደቱ ግልጽና ተገማች እንዲሆን፣ ዝርዝር ሥነ ሥርዓቶችም ሁሉም አካላት ድምፃቸው እንዲሰማ ስለሚያደርጉ አስፈላጊነቱን ያጎላሉ፡፡ ዘመላክ፣ ‹‹የሕግ ማዕቀፍ ቢዘጋጅም ሥርዓቱና ሒደቱ ግትር እንዳይሆን በማድረግ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

እንደ አሰፋ ገለጻ የመንግሥት የእርስ በርስ ግንኙነት ሥርዓት ለሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች አስፈላጊ ነው፡፡ የመጀመሪያው በሕገ መንግሥቱ የፌዴራል መንግሥቱና ክልሎች የሚጋሯቸው ሥልጣኖች በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተቀመጡ ከመሆናቸው ጋር ይያያዛል፡፡ ‹‹ሁለቱ የመንግሥት ተዋረዶች የሚሠሩት በራሳቸው ተቋማት አማካይነት ነው፡፡ ስለዚህ በጋራ ጉዳይ ላይ በጋራ ማቀድ፣ ማስተባበርና መፈጸም ይጠበቃል፤›› ሲሉ አመልክተዋል፡፡

‹‹ይህን በፓርቲ መስመር፣ መደበኛ ባልሆነ የሚኒስትሮች ግንኙነት፣ በፓርላማ አፈ ጉባዔዎች ፎረምና በተለያዩ የዘርፍ አካላት ስብሰባዎች ስንፈጽመው ቆይተናል፡፡ በሒደቱ የቀረው ነገር ቢኖር አመራር የሚሰጥና በጉዳዩ ላይ ፖሊሲ የሚቀርፅ አካል ነው፤›› ያሉት አሰፋ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የፌዴራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር ይህንኑ ጉዳይ የሚመለከት ክፍል ያላቸው ቢሆንም ወጥ የሆነ አገር አቀፍ አመራር እንደሌለ ግን አስገንዝበዋል፡፡

ለአሰፋ ሁለተኛው የመንግሥታት የእርስ በርስ ግንኙነት ጠቀሜታ ሕገ መንግሥታዊ ከለላ ካለው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ጋር የተያያዘ ነው፣ ‹‹በዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሒደት ውጤቶች ተገማች አይደሉም፡፡ በምርጫ 97 ቅንጅት አዲስ አበባንና በርካታ ወንበሮችን ደግሞ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልል አሸንፎ ነበር፡፡ ፈጠነም ዘገየ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ክልሎችን ወይም ፌዴራል መንግሥቱን ሊቆጣጠሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች እርስ በርስ የሚገናኙበትን ሥርዓት የሚመሩ መርሆዎች፣ ሕጎችና ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ አሁን አንድ ፓርቲ ብቻ ስላለ ጉዳዮችን በስልክ መጨረስ ይቻል ይሆናል፡፡ ለነገሩ በአንድ ፓርቲ ውስጥም ቢሆን ቀላል እንዳልሆነ በቅርቡ ከነበረው ቀውስ መረዳት ይቻላል፡፡ የተለያዩ በርካታ ፓርቲዎች ሲኖሩ ችግሩ ይበልጥ እንደሚወሳሰብ መገመት ይቻላል፡፡ በረቂቁ ፖሊሲ ዋናው ውሳኔ ሰጪ አካል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና የክልል ፕሬዚዳንቶች እንዲሆኑ አድርገናል፡፡ ከታች ደግሞ የፌዴራሉና የክልል መንግሥታት የዘርፍ አካላት አሉ፤›› በማለትም አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ የመንግሥታት የእርስ በርስ ግንኙነት ሥርዓት አገሪቱ በተለያየ ጊዜያት ካጋጠማት አውዳሚ ችግር ለመቅረፍ ምን ያህል አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ነው፡፡ ዘመላክ፣ ‹‹ሥርዓቱ ባለመኖሩ ችግሮች ተፈጥረዋል ብዬ አላስብም፡፡ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የነበረው ግንኙነትም ግጭቶች እንዲፈቱ አስተዋጽኦ አድርጓል የሚል ግምገማ የለኝም፡፡ ነገር ግን ግንኙነቱ በቋሚነት የሚካሄድ ከሆነ ችግሮችን ገና ማቆጥቆጥ ሲጀምሩ ለመግረዝ ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡ ዘመላክ ሥርዓቱ ከበርካታ ጠቀሜታዎቹ መካከል ለስብሰባ የሚቀመጠው ማን እንደሆነ፣ መቼ ስብሰባ እንደሚደረግ፣ በምን ጉዳዮች ላይ ውይይቱ እንደሚደረግና ውሳኔዎች ላይ እንዴት እንደሚደረስ የሚገዛ በመሆኑ ይበልጥ ግልጽነት እንደሚያሰፍን አመልክተዋል፡፡

ለደኅንነት ተንታኙ የመንግሥታት ግንኙነት ፖሊሲ ረቂቅ መዘጋጀቱ በራሱ ችግሮችን አሁን ባለው ሥርዓት መቅረፍ ላለመቻሉ ማሳያ ነው፡፡ ነገር ግን የመንግሥታት የእርስ በርስ ግንኙነት ሥርዓቱ በራሱ ችግሮችን ሊቀርፍ አይችልም፡፡ ቢሆንም በግልጽነትና በተጠያቂነት በተመሠረቱ የፖለቲካ ማሻሻያዎችና ተቋማዊ ባህል ከታገዘ ግን፣ የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ካሉበት በሽታዎች መካከል የተወሰኑትን የማዳን ኃይል እንደሚኖረው እምነታቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ reporter