CURRENT

የ2016 የሰብዓዊ ልማት ሪፖርት ይፋ ሆነ

By Admin

April 14, 2017

በሰብዓዊ ልማት ባለፉት 25 አመታት እድገት መታየቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድርጅት አስታወቀ።

የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም የ2016 የሰብዓዊ ልማት ሪፖርት ትናንት በአዲስ አበባ ይፋ ሆኗል።

በዚህ ወቅት እንደተገለጸው፥ በከፋ ድህነት ውስጥ ይገኝ የነበረው የምድራችን ነዋሪ አሁን ላይ ቅናሽ አሳይቷል።

በሪፖርቱ በሃገራት ሰዎች ረጅም እድሜ መኖራቸው፣ በርካታ ህጻናት የትምህርት እድል ማግኘታቸውና በማህበራዊ አገልግሎቶች እምርታ መታየቱም ተጠቅሷል።

በአጠቃላይም በሰው ልጆች የኑሮ ሁኔታ መሻሻሎች እንደታዩም ነው የተጠቀሰው።

ከዚህ ባለፈ ግን አሁንም በበርካታ ሃገራት ዘንድ ተግዳሮቶች መኖራቸው በሪፖርቱ ቀርቧል፤ በርካቶች አሁንም ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉም ተብሏል።

ባለፉት 25 አመታት ዜጎች የተሻለ የመኖሪያ አውድ አግኝተዋል ያለው ሪፖርቱ፥ በርካቶች ኑሮን ለማሸነፍ ከመታገላቸው አንጻር ግን በቂ አለመሆኑን ጠቅሷል።

አሁን ላይ ለአቅመ ስራ ከደረሱት መካከልም 200 ሚሊየን ስራ አጥ ሲሆኑ፥ የወጣቶች ድርሻም 73 ሚሊየን መሆኑ ተገልጿል።

ድርጀቱ በሪፖርቱ አሁንም የጾታ እኩልነትን ማስፈን አልተቻለም ነው ያለው።

ሪፖርቱ ኢትዮጵያን ዝቅተኛ የሰብዓዊ ዕድገት ካላቸው ሃገራት ተርታ መድቧታል።

በኢትዮጵያ ባለፉት 15 አመታት የሰብዓዊ ልማት ከ58 በመቶ በላይ እድገት ቢያሳይም አሁንም ከመጨረሻዎቹ ሃገራት ተርታ ተሰልፋለች።

የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽነሩ ዶክተር ይናገር ደሴም፥ ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት እምርታ ማሳየቷን ገልጸዋል።

በሰብዓዊ ልማት ዘርፍ ያለውን ክፍተት ለመቅረፍም በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ኖርዌይ፣ አውስትራሊያ እና ስዊዘርላንድ በወጣው ደረጃ መሪዎች መሆን ችለዋል፤ አሜሪካ 10ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ ቻይና ደግሞ 90ኛ ሆናለች᎓᎓

ኢትዮጵያም 15 ሃገራትን ብቻ በመቅደም በድርጅቱ መለኪያ 174ኛ ደረጃን ይዛለች።