Artcles

ያልሠራናቸውን ሠርተን ስንወቃቀስ ሀገር ይገነባል !!

By Admin

April 24, 2017

ያልሠራናቸውን ሠርተን ስንወቃቀስ ሀገር ይገነባል !!

ስሜነህ

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት የዴሞክራሲ ተቋማትን ዓቅም መገንባት ግድ እና ምናልባትም ቅድመ ሁኔታ መሆኑ አያከራክርም። በእርግጥ የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት  በጣም በርካታ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ግን ከነዚህ ተቋማት መካከል አንድ ሦስቱ መሠረታዊ ስለመሆናቸው ብዙዎች ይናገራሉ። የብዙሃን ሙያ ማኅበራት ሚዲያ እና በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች። የፖሊሲ ጥናት ማዕከል እነዚህን መነሻ ያደረገ ጥናት ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል። ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በበኩሉ የብዙሃን ሙያ ማኅበራትን የተመለከተ ሰፊ መድረክ አዘጋጅቶ አሣታፊ ውይይት ማድረጉንም አይተናል። ባሳለፍነው ሰሞን ደግሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ሚዲያውን የተመለከተ መድረክ አዘጋጅቶ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ባለድርሻ አካላቱን አወያይቷል። ስለሆነም ወቅቱ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምንተጋበት ስለሆነ እና የዓለም የፕሬስ ቀን ሰሞን ላይ የምንገኝ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ይህ ተረክ ሚዲያውን በጥልቀት፤ የብዙሃን ማኅበራትን ደግሞ በመጠኑ የሚፈትሽ እና በጎደለው ለመሙላት የሚሞክር ይሆናል።

በአዋጅ ቁጥር 533/1999 መሠረት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በሀገሪቱ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ተቋማትን ፈቃድ ክትትል እና ቁጥጥር የሚያከናውንበት ሥልጣን ተሰጥቶታል። ይህ ተቋም  ከላይ ስለተመለከተው አጀንዳ “ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነትን በመወጣት እና የዴሞክራሲ ሥርዓትን በመገንባት ረገድ የንግድ ብሮድካሰት ሚዲያው የሚገኝበት ሁኔታ” በሚል ርዕስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።  በዚህ መድረክ የቀረበው እና የግል ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ባለፉት 12 ወራት አካባቢ ያሠራጯቸውን 150 ዜናዎች እና 800 ፕሮግራሞች መሠረት አድርጎ የተሠራ መሆኑ የተነገረለት ጥናት እንዳመለከተው፤ የግል ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ ለብሔራዊ መግባባት እዚህ ግባ የሚባል ሥራ አለመሥራታቸውን ነው። በግል ሚዲያው በኩል ማራገብ ዋና ሥራው እንደሆነ በተነገረበት በዚህ መድረክ ስለአራጋቢነት ሚናውም የቅርብ ማሳያ ተጠቅሷል። እንደማሳያነት የቀረበው ደግሞ በቆሼ የደረሰው አደጋ ነው። በቻይና በየወሩ ተመሳሳይ ችግር ያለ መሆኑ በሚታወቅበት አግባብ እና በቅርቡም ኮሎምቢያን የወሰዳትን ጎርፍ በመጥቀስ ይልቁንም ተመሳሳይ አደጋዎች በየትኛውም ዓለም የሚገጥሙ ስለመሆናቸው በማስመር በኛ ሚዲያዎች በኩል ቆሼ የተዘገበበት መንገድ ገንቢ እንዳልነበር እና ይልቁንም የማራገብ ዘመቻ እንደሆነ በማመላከት ሚዲያዎቻችን በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ግንባር ቀደም ሚና ቢኖርባቸውም ሆነው ያልተገኙ መሆናቸው ተመላክቷል። በመፍትሔዎች እና በመንስዔዎች ላይ በቂ ትንታኔ ማቅረብን መርሕ ያደረገ ሚዲያ በሌለበት ሀገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት የማይቻል ሲሆን፤ የሚከፋው ደግሞ ሚዲያው በግልባጭ አራጋቢ ሆኖ ሲገኝ ነው  ።

እንደሚዲያ ሰው የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ  እዚህ ጋር አንድ እና መሠረታዊ የሆነ ችግር መኖሩን ግን ይገነዘባል። የመንግስት ስራ አስፈጻሚዎች መረጃን የሚከለክሉ መሆኑ አንዱ ነው።ችግሩ ደግሞ በዚህ አያበቃም። አስፈጻሚዎቹን ያላስደሰታቸውን ፕሮገራም ሚዲያው ባቀረበ ጊዜ ደግሞ ከብርሃን ፈጥነው የደብዳቤ ጋጋታ መላካቸው ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ስለሀገሪቱ ልማት እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ እና ግንባር ቀደም ሚና እንዳለው ከሚታወቅ ምናልባትም ያለሚዲያው ተሳትፎ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት በማይቻልበት እውነታ ላይ ሆኖ አንድ ሥራ አስፈጻሚ መረጃ ስለከለከለ በማራገብ ሥራ መጠመድ ወይም ለማራገባችን ምክንያቱ የመረጃ ማጣት ነው ማለት ምክንያታዊ አያደርግም፤ ውኃ የማይቋጥር  መከራከሪያም ነው። ስለምን ቢባል አንዳንድ ሚዲያዎች በማራገብ  ተወዳጅ ለመሆን የሚጥሩ መሆኑ ይታወቃልና!።  

በንግድ መገናኛ ብዙሃን በኩል በተለይ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት እና የሥራ ኃላፊዎች መረጃ ሲጠየቁ አለመስጠት የተለመደ እና መንግሥትም ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ይህን ችግር በመሠረታዊነት አይቶ ከወቀሳው እኩል በኩል መፍትሔ ለመስጠት ካልቻለ ከአራጋቢዎቹ ተለይቶ የሚታይበት ምክንያት አይኖርም። ሚዲያውም ሆነ መንግሥት ያላቸውን ዕድል ሳይጠቀሙ አንዱ ሌላውን በመፈረጅ መወቃቀስ የትም አያደርስም። ባለሥልጣን መረጃ ተጠይቆ አልመልስም ካለ እገሌ የተባሉት ኃላፊ በአካል ተገኝተን አሊያም ደውለን በእንደዚህ ያለ ጉዳይ ላይ ላቀረብንላቸው ጥያቄ መልሰ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም ብሎ በማጋለጥ  (ለአንባቢ እና አድማጭ ተመልካች) ባለሥልጣኑን ማሳጣት የሚያስችለውን ዕድል ሳይጠቀም ማራገብ ተገቢ ያለመሆኑን ያክል፤ መረጃ የሚከለክሉ አስፈጻሚዎችን ሳይቀጡ እና መቅጣት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ሳያወጡ ስለምን ታራግባላችሁ ብሎ ወቀሳም ችግር የማሻገር ጉዳይ ካልሆነ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው የሚፈይድልን አንዳች ነገር የለም። ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሚናቸው የጎላ መሆኑ የሚታወቁ ተቋማት ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስችል መደላድል መፍጠር የመንግሥት ቁልፍ ተግባር መሆን እንዳለበት ሁሉ፤ በአራቱ የዴሞክራሲ እሴቶች መገንቢያ (የሕግ የበላይነት፣ ምክንያታዊነት፣ መቻቻል መፍጠር እና ሰጥቶ መቀበል) ተጠቅሞ ችግሮችን ፈልፍሎ ማውጣት እና ማቅረብ ደግሞ ከሚዲያው እና ከጋዜጠኞች የሚጠበቅ ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባዋል።

በዚህም ተባለ በዚያ ግን አሳማኝ ምክንያት የማይኖረው የመገናኛ ብዙሃኖቻችን ችግር  አጀንዳ ቀርጸው በአበይት ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን የሚያጎለብቱ ፕሮገራሞችን ከማሠራጨት እና በብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እኩልነት እና መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያጠናክር ተከታታይነት ያላቸው ፕሮግራሞችን ከማቅረብ አኳያ እጥረት ያለባቸው መሆኑ ነው። ለዚህ ሁነኛ ማሳያ የሚሆነን የብሮድካስት ፈቃድ ሲሰጣቸው ከገቡት ውል ውጪ በመሆን አብዛኛውን ጊዜያቸውን በስፖርት እና በመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ የሚያሳልፉ መገናኛ ብዙሃኖች መበርከታቸው ነው። የብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃዎችን በእኩልነት አለማስተናገድንም የተመለከተው ሌላኛው ማሳያ የሚሆን የአደባባይ ሐቅ ነው።

በእርግጥ እዚህም ጋር አንድ ችግር አለ። የመንግሥትን ሕግ እና ሥርዓትን አክብረው ፈቃድ ወስደው የሚጠበቅባቸውን ግብር እየከፈሉ እና ሀገራዊ ግዴታቸውን የሚወጡ መገናኛ ብዙሃኖች መኖራቸው በግልጽ በሚታወቅበት ሁኔታ የመንግሥት ድርጅቶችን ማስታወቂያዎች ግን በመመሪያ ለተወሰኑ የግል መገናኛ ብዙሃን እና ለመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ብቻ እየሰጡ ወሬ አራጋቢ ብሎ ወቀሳ ውኃ አያነሳም። የሚገርመው ደግሞ የመንግሥት ማስታወቂያዎችን ለሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የማዳረስ ሕግ በወጣበት አግባብ ይህ ልዩነት መፈጠሩ ነው ። ይህ ደንብ በሥራ ላይ ሳይውል የቆየው ባለመጽደቁ ነው። ስለሆነም ተጠያቂው አራጋቢ ባዩ መሆኑንም ማጤን እና በቶሎ ወደ ሕጋዊዩ አሠራር መግባት አስፈላጊ ይሆናል ።  

ሌላው ነገር ሚዲያውም ሆነ አስፈጻሚው ለሕዝብ ሊሰጥ የሚገባውን ያህል ትኩረት ባለመስጠት ችግር ተተብትቦ መያዙ ነው፡፡ ይህም የሕዝብን ኃይል፣ የሕዝብን ጉልበት፣ የሕዝብን ዓቅም በሚገባው ደረጃ አለመረዳት ነው፡፡  

በአስፈጻሚው በኩል ሚዲያ ላይ ያለው አመለካከት በሚፈለገው ደረጃ የዳበረ አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ አሳንሶ ማየት፣ ተፅዕኖ ማሳደር፣ የሚባለውን ብቻ ነው መዘገብ ያለበት ብሎ ማመን በአስፈጻሚው በኩል ከሚታዩ ችግሮች ተጠቃሾች እና አስቸኳይ መፍትሔ የሚሹ መሰናክሎች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስም የመገንባት ዓይነት እንጂ ሚዲያው የሕዝብ እና የመንግሥት ነው፣ ሕዝብን እና መንግሥትን የሚያገናኝ ድልድይ ነው ብሎ ያለመውሰድ ነገር በብዙ አስፈጻሚዎች ዘንድ ይታያል፡፡ ይኼም በመሆኑ ዝም ብለህ የተሰጠህን ሥራ፣ ጥሩ ነገሬን ብቻ አቅርብልኝ የማለት ሁኔታ በአስፈጻሚው ዘንድ ጎልቶ የሚታይ እና ስለምን መፍትሔ እንዳልተበጀለት የሚያጠያይቅ ነው፡፡ አልፎ ተርፎም ሚዲያውን የራሳቸው የሕዝብ ግንኙነት አድርገው መውሰድ፣ የተቋማቸውን ገጽታ መገንቢያ መሣሪያ አድርገው የመውሰድ ችግሮች የሚታዩ መሆኑንም የፖሊሲ ጥናት ማዕከል ሰሞንኛ ጥናት አረጋግጧል፡፡

ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሕዝብን ተሳትፎ ለማሳደግ ትልቅ ሚና ያላቸው  አካላት የሚፈለገውን ያህል ዓቅማቸው አልተገነባም፡፡ በዚሁ ላይ ደግሞ ሚዲያው ላይ እና የብዙሃን ማኅበራቱ ላይ አስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ ያሳድርባቸዋል፡፡ ስለሆነም ብቃታቸው ያልተገነባ እና መብታቸውን በማስከበር ሊሠሩ የሚገባቸውን ያህል ደፍረው እየሠሩ አይደለም፡፡  

ከላይ በተመለከቱ አስረጂዎች አግባብ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሚዲያውም ጋር ሆነ አስፈጻሚውም ላይ ችግሮች እንዳሉ ሁለቱንም ወገኖች የሚያስማማ ነው፡፡ ስለሆነም ልዩነቱ ያለው ይኼንን ችግር ወስዶ ምላሽ የመስጠት እና ያለመስጠት ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ችግር ደግሞ ሁሉም ጋ የሚታይ ነው፡፡ ከሕዝብ ምክር ቤትም ጋር ተያይዞ ሕዝብ የወከለኝ ነኝ፣ ከጀርባዬ ብዙ ሕዝብ አለ፣ ስለዚህ የእነሱን ሐሳብ እና ጥያቄ ይዤ መሄድ አለብኝ ብሎ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት የማሳየት ችግር ይታያል፡፡ በተለይ ማኅበራት ጋ ችግሩ የጎላ ነው፡፡ ብዙዎቹ የሙያ ማኅበራት የምንላቸው የተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ችግር አለባቸው፡፡

ሚዲውም ላይ እንደዚሁ ይታያል፡፡ ጋዜጠኛው የሕዝብ ጉዳይ ጉዳዬ ነው ብሎ ያለመሥራት፣ እዚያ ውስጥ የወጣ ነገር አለ ብሎ በተነሳሽነት እና በቁርጠኝነት የመሥራት ችግር አለ፡፡ የደመወዝ ማግኛ ብቻ አድርጎ የመውሰድ ነገር አለ፡፡ ይኼንን የሕዝብ ችግር በመሥራቴ ደስተኛ ያደርገኛል ብሎ ያለመንቀሳቀስ ነገር በጣም የሚታይ እና ጎልቶ የወጣ የሚዲያው ችግር ነው ፡፡ በመንግሥትም በኩል መረጃ ወሳኝ ጉዳይ ይነገራል እንጂ ስለወሳኝነቱ አንዳች የተሠራ ነገር የለም፡፡ እንደ ሀገር ቋሚ የመረጃ ቋት የሌለ መሆኑ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ለሁሉም ተደራሽ የሆኑ መረጃዎችን የመያዝ ነገር ገና ያልዳበረ መሆኑ የሚያስጠይቀው መንግሥትን ነው፡፡ ከሚዲያዎች አካባቢ የሚነሳው ነገር ደግሞ መረጃ ለማግኘት ውጣ ውረድ የበዛበት መሆኑ ነው፡፡ አድሏዊነት መኖር፣ አንዳንድ ጊዜ ለተወሰኑ ሰዎች ይሰጣል፣ ለተወሰኑት ደግሞ የሚከለከል መሆኑ፡፡ ስለሆነም ማንም አራጋቢ ማንም ደግሞ ወቃሽ የማይሆንበትን ዕድል መፍጠር እና ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ያልሠራናቸውን ሠርተን መወቃቀሱ  ተገቢ ይሆናል። ይህ ሲሆን፤ ለሀገር ልማት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሰብዓዊ መብት መከበር የበኩላችን ተወጣን ማለት ይሆናል። ሀገር የምትለማበት የተሻለው አጫራጭም ይኸው ነው።