CURRENT

ደቡብ አፍሪካ የኒዩክሌር ሀይል ማመንጫዎችን ለመገንባት የደረሰችው ስምምነት ውድቅ ተደረገ

By Admin

April 26, 2017

የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀገሪቱ መንግስት የኒዩክሌር ሀይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ለመገንባት ከሶስት ሀገራት ጋር የደረሰውን ስምምነት ውድቅ አደረገ።

ደቡብ አፍሪካ ስምምነቱን ከሩስያ፣ አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ጋር ነበር የተፈራረመችው።

የኬፕ ታውን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ስምምነቱን ህግን የጣሰ ነው በሚል ውድቅ አድርጎታል።

መንግስት የኒዩክሌር እቅዱን ለህዝብ ውይይት አለማቅረቡ እና በፓርላማ ክርክር ሳይደረግበት መቅረቱንም ነው ፍርድ ቤቱ የጠቀሰው።

ኧርዝላይፍ አፍሪካ ኤንድ ሳውዝ አፍሪካን ፌዝ ኮሚዩኒቲስ ኢንቫይሮመንታል ኢንስቲትዩት ከሶስቱ ሀገራት ጋር የተደረሰውን የኒዩክሌር ስምምነት ወደ ፍርድ ቤት በመውሰዱ ነው ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው።

የሀገሪቱ መንግስት እስካሁን በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠም።

ደቡብ አፍሪካ ስምንት የኒዩክሌር ሀይል ማመንጫ ጣቢያዎችን በ1 ትሪሊየን ራንድ (76 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር) ለመገንባት ማቀዷ ይታወሳል።

ይህ የሀገሪቱ እቅድም በአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾች ሲተች የቆየ ቢሆንም፥ የሀገሪቱ መንግስት እያደገ የመጣውን የኤሌክትሪክ ሀይል ፍላጎት ለማሟላት ከድንጋይ ከሰል ይልቅ የኒዩክሌር ሀይል እንደሚያስፈልግ ይሞግታል።

ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ብቸኛዋ የኒዩክሌር ሀይል ማመንጫ ያላት ሀገር መሆኗን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።FBC