Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዴሞክራሲን ማጎልበት የመንግሥት ብቻ ድርሻ አይደለም

0 308

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዴሞክራሲን  ማጎልበት የመንግሥት ብቻ ድርሻ አይደለም    ብ. ነጋሽ

የዳበረ ዴሞክራሲን በመገንባት የሚጠቀሱት የምዕራባውያን ዴሞክራሲ በመቶዎች የሚለኩ ዓመታትን ተጉዟል። ኢትዮጵያ ከዴሞክራሲያዊ  የመንግሠት ሥርዓት ጋር ከተዋወቀች ገና ሩብ ክፍለ ዘመን ያህል እድሜ ብቻ ነው ያስቆጠረችው። አሁን ኢትዮጵያ በምትባለው ምድር ውስጥ የሚኖሩ አንዳንድ ማህበረሰቦች የዴሞክራሲ ባህሪ ያለው የአስተዳዳር ሥርዓት የነበራቸው መሆኑ ባይካድም፣ ዘመናዊ ዴሞክራሲ ግን ለኢትዮጵያ አዲስ ነው፤ ገና ሁለት አሥርት ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ ዴሞክራሲ።

ኢትዮጵያ ረጅሙን ታሪኳን  በፈላጭ ቆራጭ ንጉሣዊ (absolute monarchy) ሥርዓት ነው ያሳለፈችው። ማዕከላዊ ንጉሠ ነገሥታቱ ሲዳከሙ አገሪቱ በመሣፍንቶች ተከፋፍላ የነበረችበት ዘመናትም ነበሩ። ወደደቡብ ኢትዮጵያ ስንመጣ ደግሞ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የኦሮሞዎች ገዳ ሥርዓትና ሌሎች መሰል የአስተዳደር ሥርዓቶች የመኖራቸውን ያህል፣ ከሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ የነገስታት ሥርዓቶችም ነበሩ። የአሁኗ ኢትዮጵያ በአሃዳዊ ንጉሰ ነገሥታዊ ሥርዓት መተዳደር የጀመረችው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ገደማ መሆኑነ ልብ ይሏል። ይህ አሃዳዊ የንጉሠ ነገሥቱ ስርአት ያበቃው ከአራት አስርት ዓመታት በፊት ነበር። የዘውዳዊው ሥርዓት የታሪክ ምዕራፍ የተዘጋው በህዝባዊ አመጽ ነበር። ከኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጭቆና ነጻ የሆነች የህዝቦች የበላይነት የተረጋገጠባት ዴሞክራሲያዊ አገር የመመሥረት ተስፋ በሰነቀ ህዝባዊ ትግል።

ይሁን እንጂ ይህ ህዝባዊ ትግል የወለደው አብዮት ወደተፈለገው የህዝብ የበላይነት ወደተረጋገጠበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማሸጋጋር አልቻለም። ይህ እንዲሆን ያደረገው ቀዳሚው ምክንያት ዘውዳዊውን ሥርዓት የገረሰሰው ትግል ያልተደራጀ መሆኑ ነበር። እናም በወቀቱ ተደራጅቶ የነበረው ያንኑ ዘውዳዊ ሥርዓት ሲያገለግል የነበረው ወታደራዊ ኃይል፣ አባት አጥቶ ሲንሳፈፍ የነበረውን ሥልጣን በእጁ አስገባ። ወታደራዊው አካል ደርግ የተሰኘ ቡድን አደራጅቶ ነበር ሥልጣኑን በእጁ ያስገባው። ይህ ደርግ የተሰኘ ወታደራዊ ቡድን ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት መሠረተ። ይህ የመንግሥት ሥርዓት የቡድን ፈላጭ ቆራጭ (oligarchy) ሆነ።

ይህ የቡድን ፈላጭ ቆራጭ አምባገነናዊ ሥርዓት በተመሠረተ ማግሥት ነበር ህዝባዊ መንግሥት የመመሥረት ህዝባዊ የነጻነት ትግል የተቀሰቀሰው። በአመለካካት እንዲሁም በብሄራዊ ማንነት የተደራጁ የተለያዩ የነጻነት ቡድኖች አምባገነኑን ሥርዓት ለማስወገድ በየአቅጣጫው ትግል ማካሄድ ጀመሩ። ገሚሱ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ፣ ሌሎች ደግሞ በውጭ አገራት በተለያየ መንገድ ሥርዓቱን ለመታገል ሞክረዋል። ይህ በየአቅጣጫው የተካሄደ ህዝባዊ ትግል አምባገነኑን ሥርዓት ዳግም ላይመለስ አሰናበተው። እነሆ ይህ አምባገነን ሥርዓት ከተወገደ ሃያ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል። እንግዲህ አገሪቱ ከዴሞክራሲ ጋር የተዋወቀችው ከዚህ በኋላ ነበር። ከሽግግር መንግስሥ ጀምሮ የኢፌዴሪን የመንግሥት ሥርዓት እስከመመሥረት ያለው ሂደት አሁን በህይወት ያለን ጎልማሳ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የተሳተፍንበት የቅርብ ጊዜ ታሪካችን በመሆኑ ትቼው፣ የአገሪቱ ዴሞክራሲ አሁን የደረሰበትን ደረጃ ለመመለከት እሞክራለሁ።

ዴሞክራሲ አራት መሠረታዊ ነገሮችን ይይዛል። እነዚህም፤ ህዝብ መንግሥቱን የሚመርጥና የሚለውጥበት ሥርዓት መኖር፣ ሕዝብ በአገሩ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ የሚችል መሆኑ፣ የሁሉም ዜጎች ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች የተረጋገጠበት መሆኑ፤ ሁሉም ዜጎች በህግ ፊት እኩል መሆንና የህግ የበላይነት የሰፈነበት መሆኑ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ለዚሀ ጽሁፍ ዓላማ ህዝብ መንግሥቱን የመምረጥና የመለወጥ ሥርዓት ላይ አተኩራለሁ።

የመምረጥና የመመረጥ መብት የአመለካከት ነጻነት – የዜጎች የፈቀዱትን አመለካከትና አቋም የመያዝ፣ የመግለጽ፣ የሌሎችን ሃሳብና አመለካከት የመቀበል፣ በአመለካከት የመደራጀት ወዘተ…መብቶችና ነጻነቶች ባልተከበሩበት ሁኔታ እውን ሊሆን አይችልም። ምርጫና የአመለካካት ነጻነት ሊነጣጠሉ የማይችሉ የዴሞክራሲ ባህሪያት ናቸው። ከ26 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የነበሩት ንጉሣዊና የወታደራዊ ቡድን ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓቶች የአመለካከት ነጻነትን አላከበሩም። በመሆኑም ዘውዳዊው ሥርዓት ምንም እንኳን የፓርላማ ምርጫ የሚያካሂድ ቢሆንም፣ ወታደራዊው ቡድንም በመጨረሻዎቹ ዓመታት የኢህዴሪን መንግሥት መሥርቶ የሸንጎ ምርጫ አካሂጃለሁ ቢልም ምርጫው የዴሞክራሲን መሥፈርት አያሟላም፤ የአመለካካት ነጻነት ባልተከበረበት ሁኔታ ስለተካሄደ። ዜጎች አማራጭ ሃሳቦችን የሚያገኙበት፣ ተፎካካሪዎችም በነጻነት በያዙት አቋም ወይም በአመለካከት ላይ ተመሥርተው ባደራጁት ፓርቲ አማራጫቸውን የሚገልጹበት እድል ስላልነበረ ምርጫ ተካሂዷል ማለት አይቻልም።

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት በአንቀጽ 29፣ የአመለካከትና ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብት አረጋግጧል። የህገ መንግሥቱ አንቀፅ 31 የመደራጀት መብትን አረጋግጧል። አንቀጽ 38 ደግሞ የመምረጥና የመመረጥ መብትን አረጋግጧል። የህ አንቀጽ፤ ማንኛውም ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሄር፣ በብሄረሰብ፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለካከት ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሠረተ ልዩነት ሳይደረግበት፤ በቀጥታና በነጻነት በመረጣቸው ተወካዮቹ አማካይነት በህዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ፤ በማንኛውም የመንግሥት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት አለው ይላል። እነዚህ እውነታዎች በኢፌዴሪ የመንግሥት ሥርዓት ህዝብ በምርጫ መንግሥቱን የመወከልና ውክልናውን ማንሳት የሚያስችለው መሠረታዊ የዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መሟላቱን ያረጋግጣል።

አመለካከትን በነጻ የመያዝ፣ የመግለጽ፣ በአመለካከት የመደራጀት መብት በመረጋገጡ የተለያየ አቋምና አመለካከት እንዲሁም ፖሊሲዎች ያሏቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው በይፋ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። ህዝብ ደግሞ እነዚህ ፓርቲዎች ከሚያቀርቡለት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፖሊሲዎች መካከል ያዛልቀኛል ብሎ ያመነበትን ይመርጣል። የአብላጫውን ድምጽ ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ በውክልና ሥልጣን ይረከባል። በአጭሩ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይህ ነው። ይሀ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግን ገና መጎልበት ይቀረዋል። ዴሞክራሲው እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ ከባለድርሻ አካላት በተለይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማህበራትና ሚዲያ ብዙ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት ሁለት ተኩል አሥርት ዓመታት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለምንም የአመለካካት ገደብ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በግል እጩዎች ካቀረቡለት አማራጮች መካከል ይበጀኛል የሚለውን እየመረጠ አብላጫ ድምጽና ያገኘው ሥልጣን በውክልና የተረከበባቸው አምስት አገራዊና ክልላዊ ምርጫዎች አካሂዷል። በእነዚህ ምርጫዎች ላይ ከሃምሳ በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል። እስካሁን የተካሄዱት ምርጫዎች አሳታፊ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ አለመሆናቸውን በተጨባጭ አስረጂ የሚያረጋግጥ ቅሬታ አልቀረበባቸውም። ይሁን እንጂ ማስረጃ የሌላቸው የፍትሃዊነትና የተአማኒነተ ቅሬታዎች በየምርጫው ላይ ሲቀርቡ መቆየታቸው አይካድም። በመሆኑም ምርጫዎቹን አሳታፊ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ የመሆናቸው እውነት ሚዛን ይደፋል።

ይህ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ባለፉ ሁለት አሥርት ዓመታት እርከኖችን ተሸጋግሮ የማይቀለበስበት ደረጃ መድረስ የቻለ ቢሆንም፣ የጎለበተ ምሉዕ ዴሞክራሲ ለመሆን አሁንም ብዙ ይቀረዋል። ዴሞክራሲው ምሉዕእንዲሆን በማድረግ ረገድ በተለይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ላይ ከመሳተፍ ያለፈ ዴሞክራሲውን ለማጎልበት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብዙም ጎልቶ አይታይም። አብዛኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ ሲቃረብ ብቅ ይሉና ከምርጫው በኋላ ይሰወራሉ። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መኖራቸው የሚታወቀው በምርጫ ላይ ብቻ ነው። ፓርቲዎቹ ከምርጫ ውጭም በመሠረታዊ አገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳቦችን በማቅረብና በመተቸት፣ ህዝቡ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የሰፋ እይታ እንዲኖረው በማድረግ መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል። ይህን ገንቢ በሆነ መልኩ የሚያከናውኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ጥቂቶች ናቸው።

እርግጥ አዲስ አበባን ጨምሮ በየክልሉ ያሉ የመንግሥት አስፈጻሚዎች፣ የፌዴራል መንግሥቱን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ውጭ ባሉ ወቅቶች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የሚያደናቅፉበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ለምሣሌ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚያዘጋጇቸው የህዝባዊ ስብሰባዎችና ሠላማዊ ሰልፎች ጥያቄዎች ያለበቂ ምክንያት ፍቃድ መከልከል የመሳሰሉ መሰናክሎች ያጋጠመበት ሁኔታ መኖሩ አይካድም። ይሁን እንጂ ፍጹም ህጋዊና ሠላማዊ በሆነ መንገድ እነዚህን መሰናክሎች መታገል ከፓርቲዎቹ ይጠበቃል። ዴሞክራሲ የሚጎለብተው በዚህ መንገድ ብቻ ነውና።

እርግጥ የመንግሥት አስፈፃሚዎች የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ የሚያደናቅፉ ተግባራት የሚፈፅሙት ዴሞክራሲው እንዳያድግ ለማገድ ባለ ፍላጎት አይደለም። ከግንዛቤ ጉድለት ብቻም አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አመቺ አጋጣሚ ያገኙ ሲመስላቸው፣ በሠላማዊና ህጋዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሽፋን ዴሞክራሲያዊ መብት ያጎናፀፋቸውን ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመናድ የሚሞክሩበት ሁኔታ የተለመደ መሆኑ ባሳደረባቸው ሥጋት ምክንያትም ነው። ለምሣሌ በ2004 እና በ2005 ዓ.ም  ኃይማኖታዊ የአክራሪነት  እንቅስቃሴ ይፋ ወጥቶ በነበረበት ወቅት፣ አንድ ሁለት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን የሽብርተኝነት ምንጭ የሆነንና ዓለም ያወገዘውን የአክራሪነት እንቅስቃሴ በመደገፍ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት፣ ምናልባትም ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ የሞከሩበት ሁኔታ እንደነበረ ልብ ይሏል።  

አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ አገር ቤት ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ መብትና ነጻነት፤ ጥቅምና ፍላጎት ላይ አተኩሮ ከመሥራት ይልቅ፣ በውጭ አገራት አድፍጠው ለጋውን ዴሞክራሲ ለመቅጨት የሚራሯጡ ቀልባሾችን አጀንዳ ሲያራምዱና ህዝብ ሥርዓቱ ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ጥላቻ እንዲያድርበት በማደረግ ሥራ የተጠመዱበት ሁኔታ አለ። በማንኛውም አገራዊ ጉዳይ ላይ አቋም ከመያዛቸው በፊት በውጭ አገር የሚገኙ ገንዘብ እየደጎሙ ከሚመሯቸው ቡድኖች ይሁንታ የሚጠብቁ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። ያለእነዚህ ቡድኖች ፍቃድ አቋም መያዝ አይችሉም፤ አድርጉ ያሏቸውን ብቻ ነው የሚያደርጉት። ለምሳሌ መደረክና ሰማያዊ ፓርቲ በቅርቡ ከተካሄደውና የድርድር አሰራር ደንብ ላይ ስምምነት ላይ ከደረሰው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ራሳቸውን ያገለሉት የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎት መነሻ በማድረግ ነው ማለት ስህተትነቱ ያይላል። ከዚህ ይልቅ በድርድሩን እንዲቀጠሉ የውጭ ደጋፊዎቻቻው ይለፍ ስላልሰጧቸው የመሆን እድሉ ሰፊ ነው። በዚህ የተነሳ የመንግስት አስፈጻሚው አካል የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አካሄድ በጥርጣሬ እንዲመለከት ያደረጉበት ሁኔታ መኖሩ እርግጥ ነው።

ከዚህ በተረፈ በተለይ የምርጫ ሥነ ምግባር ደንቡን ያፀደቁትና በደንቡ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የመሠረቱ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤቱ አማካይነት በተለያዩ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ገዢው ፓርቲ ማብራሪያ እንዲሰጥ የጠየቁበት፣ አቋማቸውን የገለጹበትና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የተሳተፉበት ሁኔታ አለ። ይህ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤቱ አማካይነት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ በቅርቡ የተጀመረው የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር እንዲካሄድ ማድረግ ያስቻለ መሆኑም መታወቅ አለበት። ይህ የድርድር ጥያቄ በዚህ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በተወያዩበት ወቅት ተነስቶ ተቀባይነት በማግኘቱ በመንግሥት የሥራ እቅድ ውስጥ መካተቱ ይታወቃል።

ያም ሆነ ይህ የአገሪቱ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ውጭ ባሉ ጊዜዎችም በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ በንቃት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል። የፌዴራልና የክልል መንግሥታት እንዲሁም የከተማ አስተዳደር አስፈጻሚዎችም ይህን ህገ መንግሥታዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለባቸው። አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች “አውቆ የተኛ ቢጠሩት አይሰማም” እንዲሉ የሚያጠፉት ሆነ ብለው ሰለሆነ ምክር ይመልሳቸዋል ብሎ መጠበቅ የማይመስል ነው ሊባል ቢችልም፣ ከዚህ አካሄዳቸው ተቆጥበው በአገር ቤት የሚኖረውን የኢትዮጵያ ህዝብ መብትና ነጻነት፤ ጥቅምና ፍላጎት ማስጠበቅ ላይ ብቻ አተኩረው ቢንቀሳቀሱ የአገሪቱን ዴሞክራሲ የማሳደግ የሞራል ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚችሉ ማሳሰብ ተገቢ ነው። የአገሪቱን ዴሞክራሲ ማጎልበት የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ብቻ ኃላፊነት ሳይሆን የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ጭምር በመሆኑ፣ ባለው የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ሠላማዊና ህጋዊ እንቅስቃሴ በማድረግ የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy