Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግብፅ በዓባይ የትብብር ማዕቀፍ ላይ ያነሳችው ጥያቄ በድጋሚ ውድቅ ተደረገ

0 761

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዓባይ ተፋሰስ ተጋሪ አገሮች የሚኒስትሮች ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት በኡጋንዳ ባደረገው ጉባዔ፣ ግብፅ በዓባይ ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ላይ ያነሳችው ጥያቄ በድጋሚ ውድቅ ተደረገ፡፡

የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ኮሚቴ (Nile-Com) ሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2009 ዓ.ም. በኡጋንዳ ኢንቴቤ ባደረገው ጉባዔ፣ ግብፅ የኢንቴቤ ስምምነት በመባል የሚታወቀውን የናይል የትብብር ማዕቀፍ አንቀጽ 14(ለ) ሆኖ እንዲካተት ያቀረበችው ረቂቅ ሐሳብ ውድቅ ተደርጓል፡፡

የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ጽሕፈት ቤት ለሚዲያዎች በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ግብፅ የትብብር ማዕቀፍ ይዘት በተለይም አንቀጽ 14 ንዑስ አንቀጽ (ለ) የግብፅን ጥቅም በሚያስከብር ሁኔታ እንዲገባ ጥያቄ አቅርባለች፡፡

አንቀጽ 14 ከውኃ ክፍፍል ጋር የተያያዙ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2010 ኢትዮጵያ በአንቀጽ 14(ለ) ሆኖ እንዲካተት ያቀረበችው ሁሉም ተጋሪ አገሮች በታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት ሳያደርሱ ውኃውን መጠቀም ይችላሉ የሚል ነበር፡፡

ይህንን ረቂቅ ሐሳብ ግብፅና ሱዳን በወቅቱ እንዳልተቀበሉት ይታወሳል፡፡ በዚህም ምክንያት አንቀጽ 14(ለ) በይደር እንዲቆይና በውጭ ገለልተኛ ባለሙያዎች ወደፊት ተጠንቶ የሁሉንም ወገን ፍላጎት የሚያሟላ አንቀጽ እንዲካተት ተስማምተው የትብብር ማዕቀፉን እ.ኤ.አ. በ2010 በኢንቴቤ በፊርማቸው ማፅደቃቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳና ታንዛኒያ ይህንኑ ስምምነት በሕግ አውጪዎቻቸው በማፅደቅ ሕግ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡ በዚህ የተነሳ ግብፅ ላለፉት ስድስት ዓመታት ራሷን ከናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ አግልላ ቆይታለች፡፡

ባለፈው ሳምንት በተደረገው የተፋሰሱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባዔ ግብፅ በድጋሚ ናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭን ለመቀላቀል ፍላጎት ከማሳየቷም በላይ፣ በሌሎች የተፋሰሱ ተጋሪ አገሮችም ድጋፍ እየተደረገላት ነው፡፡

ይሁን እንጂ ግብፅ ኢኒሼቲቩን ለመቀላቀል በድጋሚ አንቀጽ 14(ለ) ውስጥ እንዲካተት ያቀረበችው ረቂቅ ሐሳብ፣ የራሷ ታሪካዊ የናይል የውኃ ድርሻ እንዲከበር ነው፡፡

የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ወቅታዊ ሰብሳቢ የሆኑት የኡጋንዳው የውኃና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ሳም ኬፕቶሪስ፣ ጥያቄውን ከሌሎች የተፋሰሱ ሚኒስትሮች ጋር ተነጋግረው ውድቅ ማድረጋቸውን መግለጫው ያመለክታል፡፡

‹‹የዓባይን ውኃ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር በግብፅ በኩል የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርገናል፡፡ ምክንያቱም ሌሎቹ የተፋሰሱ ተጋሪ አገሮችም የውኃ አጠቃቀሙን በተመለከተ ድምፅ አላቸው፡፡ የሕዝብ ብዛታቸውም እየጨመረ ነው፤›› ሲሉ ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ግብፅ የታሰበውን ምላሽ በከፍተኛ ደረጃ ለማጤን ጊዜ እንዲሰጣት በጠየቀችው መሠረት ጊዜ እንደተሰጣት ለማወቅ ተችሏል፡፡ reporter

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy