Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግድቡ ቀጣናዊ ትስስርን ለማጎልበት የሚደረገው ጥረት አንዱ ማሳያ ነው!

0 297

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

  • ግድቡ ቀጣናዊ ትስስርን ለማጎልበት የሚደረገው ጥረት አንዱ ማሳያ ነው! /ታዬ ከበደ/

                                                   ሀገራችን ለመስኖና ለኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫነት ያሚያገለግሉ በርካታ ወንዞች ያላት በመሆኗ ሳቢያ የምስራቅ አፍሪካ “የውሃ ማማ” በሚል ስያሜ ብትታወቅም በተፈጥሯዊ የውሃ ሀብቷ የመጠቀም መብቷ ተገድቦ መቆየቱ ከማናችንም የተሰወረ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የሚጠቀሱት ሀገሪቱን ጨምድዶ ይዞ የነበረው የከፋ ድህነት እንዲሁም ያለፉት መንግስታት የአስተሳሰብ ውስንነት መሆናቸው እሙን ነው፡፡

    ታዲያ በህዝብ ተሳትፎና በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ራዕይን የሰነቀው የኢፌዴሪ መንግስት፤ የህዝቡን ልማታዊ ተጠቃሚነትን በየደረጃው የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ለውጤት በመብቃቱ ከላይ የተጠቀሱን ሁለት ተግዳሮቶች በአስተማማኝ ሁኔታ መፍታት ችሏል። በዚህም የዘመናት ቁጭታችን የሆነውንና የትኛውንመሜገን ሳንጎዳ በተፈጥራዊ የውኃ ሀብታችን የመጠቀም መብታችንን በበቂ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ታጅቦ በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡

    እርግጥ የግብጽ መንግስታት በናይል ውኃ የብቻ ተጠቃሚነትን እንደ ታሪካዊ መብት ባለቤትነት ሲያጣቅሱ መደመጣቸው የሚገርም ጉዳይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት መብትን በተለያዩ ዘዴዎች እያደናቅፉ ዘመናትን ሲቆጥሩ የኖሩ በመሆናቸው ነው፡፡ ለማንኛውም ትናንት ዛሬ አይደለምና ሀገራችን ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት እያስመዘገበች በመሆኑ፤ በተፈጥሯዊ የውሃ ሀብቷ በመጠቀም መብቷ በማትደራደርበት ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

    በአሁኑ ወቅት እየተጠናከረ የመጣው የህዝቧ የልማት ቁርጠኝነት እንዲሁም መንግስት የሚያከናውናቸው ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ዘላቂና ከባቢያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆን ችለዋል፡፡ ይህ ተግባሯም ከጋራ ተጠቃሚነት መርህ ውጭ አሮጌና ዘመን ያለፈባቸው አስተሳሰቦች ዋጋ ቢስ መሆናቸውን ያረጋገጠ ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ አሮጌው የቅኝ ገዥዎች ስምምነት የተፋሰሱ ሀገራትን በውሃው እኩል ተጠቃሚነት እንዲሆኑ በሚያደርገው የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ መተካት ለአማራጭና ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን በየጊዜው እየገለፀች የምትገኘው፡፡

    ታዲያ ሀገራችን ስምምነቱን ስትቀበል በምክንያታዊነት ላይ ተመስርታ መሆኑን ልብ ማለት ያሻል፡፡ ይኸውም በመጀመሪያ ደረጃ የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት የሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት መብት የሚያስጠበቅና እኩል ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ እንጂ ልክ እንደ ቅኝ ገዥዎቹ ስምምነት በጣት ለሚቆጠሩ ሀገሮች መብት የቆመ አለመሆኑን ስለምትገነዘብ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ስምምነቱ በዓለም አቀፉ የውሃ አጠቃቀም መሰረታዊ መርሆዎች ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀና ህጋዊ መሰረት ያለውና ህገ ወጥ ስምምነቶችን በተለይም የቅኝ ግዛት ውሎችን በጽኑ የምትቃወም ሀገር ስለሆነች ነው።

    እናም አሮጌው ስምምነት በአዲሱ የመተካቱ አስፈላጊነት ከፍተኛ እንደሆነ ሀገራችን ታምናለች፡፡ በመሆኑም ዕውቅና የምትሰጠው አብዛኛው የተፋሰሱ ሀገራት ለተስማሙበት የኢንቴቤው ስምምነትን እንጂ እንደ መከራከሪያ ነጥብ ለሚጠቀሰው የቅኝ ገዥዎች ሰነድ አይደለም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን የትኛውም ወገን ያሻውን ቢልም፤ ሀገራችን እንደ ማንኛውም ሀገር በውሃ ሃብቷ በመጠቀም ህዝቦቿን ከድህነት የማላቀቅ መብት እንዳላት ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

    እንደሚታወቀው ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉም የላይኛው የናይል ተፋሰስ ሀገራት ህዝቦቻቸውን ከድህነት የማውጣት የቤት ስራ ፊታቸው ላይ ተደቅኖ ይገኛል፡፡ ይህን የቤት ስራቸውን በብቃት ለመወጣት ደግሞ ሁሉንም የተፈጥሮ ሃብታቸውን በተገቢው ሁኔታ አልምተው መጠቀም ይኖርባቸዋል። እናም ነገሩ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ከተፈጥሮ ሃብታቸው አንዱ የሆነውን ውሃ ለልማት የማዋል ጉዳይ ጊዜ የሚሰጡት አይደለም።

    ሀገራቱ በውሃ ሀብታቸውን ተጠቅመው የምግብ ዋስትናቸውን እንዲሁም የሃይል አቅርቦትን በማሳደግ ለኢንዱስትሪው ኢኮኖሚ ምቹ ሁኔታ መፍጠርን ዋነኛውና ወሳኙ አማራጭ አድርገል፡፡ በዚህም የዘመናት በደላቸውን ወደ ጎን በመተው በሆደ ሰፊነት በውሃው እኩል ተጠቃሚነት ላይ ለሁለት አስርት ዓመታት ሲደራደሩ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡

    ታዲያ ይህ ሂደት አንድ ትልቅ ግንዛቤን ያስጨበጠናል፡፡ እርሱም የተፋሰሱ ሀገራት በውሃው የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ብቻ መመስረታቸውን እንዲሁም ይህ ሃሳባቸው ማንንም ለመጉዳት የታሰበ አለመሆኑን ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው አንዱን ተጠቃሚ ሌላውን ተጎጂ ያደረጉት ሁለቱም የቅኝ ገዥዎች ስምምነቶች ከግብጽና ከሱዳን በስተቀር ሌሎቹን የተፋሰሱ ሀገራት ያገለሉና በሃይል ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡

    ከዚህ አንጻር የተፋሰሱ ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተው የኢንቴቤው የስምምነት ማዕቀፍ፤ የውሃ ባለሀብቶቹን የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትንም ይሁን ዋነኛ ተጠቃሚ የነበሩትን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ያጠቃለለ ሰጥቶ መቀበል አካሄድን የተከተለ መሆኑ ከላይ ለገለፅኩት እውነታ ሁነኛ አስረጅ ነው፡፡

    የኢፌደሪ መንግስትና ህዝቡ በመገንባት ላይ የሚገኙት የህዳሴው ግድብ የትኛውንም ወገን አይጎዳም። ይልቁንም ግድቡ ሀገራችን ኤሌክትሪክ በመሸጥ የቀጣናውን ሀገራት በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት አንዱ ማሳያ ነው። ከግድቡ ኬንያ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ። ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራትም እንዲሁ ተጠቃሚ መሆናቸው አይቀርም።

    ከዚህ ቀጣናዊና የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚነትና በኢኮኖሚ የማስተሳሰር ፍላጎቷ በመነሳትም ሀገራችን ለዘመናት ተገድቦ የቆየውን ሀገሪቱ በተፈጥሯዊ ውኃ ሃብቷ የመጠቀም መብቷን አሳልፋ ልትሰጥ አትችልም። እናም የራሷን ፕሮጀክት በራሷ አቅም በመገንባት ላይ ያለች እንዲሁም ከድህነት ለመውጣት ስትል የምትገነባቸውን ማናቸውንም የልማት ግድቦችን ለአፍታም ቢሆን የማታቆም መሆኗን መገንዘብ ይገባል። ብሔራዊ ጥቅሟን ለማንም አሳልፋ የማትሰጥ መሆኑንም ጭምር እንዲሁ።

    እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን ለድርድር አቅርባ የማታውቅ የጥቁር ህዝቦች መኩሪያ ሀገር ናት። ከባርነት፣ ከጭቆና እና ከቅኝ ተገዢነት ለመላቀቅ ብርቱ ትግል ላደረጉ በርካታ የዓለማችን ህዝቦች አርአያና ምሳሌያቸው እስከ መሆንም ደርሳለች።

    ዛሬ የሀገራችን ህዝቦች የራሳቸውና የቀጣናው ሀገራት ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ረሃብና ጦርነት ማብቃት አለበት ብለው ቆርጠዋል። ‘ለዚህ ሁሉ ያደረሰን ዋነኛ ጠላታችን ማነው?’ ብለው ጠይቀው ትክክለኛውን ምላሽም አግኝተዋል። ድህነትንም ዋነኛው ጠላታችን ነው ብለው ደምድመዋል። ጎረቤቶቻቸውን፣ በተለይም የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ ለማድረግ በእኩልና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ የግንኙነት ፖሊሲን ቀርፀውም እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ‘ድህነትንም እንዴት እናስወግዳለን?’ ብለው መክረው መፍትሔ ካበጁም ቆይተዋል። በሁሉም መስክ ፈጣን ልማትን ሊያመጡላቸው የሚችሉ አቅጣጫዎችን መከተል ብቸኛ አማራጫቸውን ከማውጣትም ባሻገር፤ በትግበራ ሂደቱ ላይ የጋራ መግባባትን እየፈጠሩ ነው።

    በተለይም ደግሞ እንደ ማንኛውም ሉዓላዊ ሀገር የዕድገት ውጥኖችን የማሳካው ባለኝ የተፈጥሮ ፀጋ በመጠቀም ነው ብላ በአባይ ወንዝ ላይ ትኩረት አድርጋለች። በዚህ ወንዝ ላይ የሚገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፍላጎት የሟማላት አቅም ያለው ብቻ ሳይሆን ቀጣናውንም በኢኮኖሚ የማስተሳሰር አንዱ ማሳያ ነው። ይህም ጥረት የዚህን ወንዝ ቱርፋት ተቋዳሽ የሆኑና የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርገው መሆኑም የሀገሪቱንና የህዝቦቿን ከሌሎች ጋር ተባብሮ የማደግ ፍላጎትን በግልጽ የሚያሳይ ነው። ታዲያ ለዚህ በጋራ የመልማት ቀጣናዊ ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይኖርባቸዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy