Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግጭት መቼም ቢሆን የህዝቦች ፍላጎት ሆኖ አያውቅም!

0 313

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ግጭት መቼም ቢሆን የህዝቦች ፍላጎት ሆኖ አያውቅም!

                               ታዬ ከበደ

ግጭቶች በየትኛውም ሁኔታ ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ግጭት መፈጠር የለበትም ሊባል አይችልም፡፡ በየትኛውም ማህበረሰብ መስተጋብራዊ ግንኙነት ውስጥ  ግጭት መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ዋናው ጉዳይ እንዴት አድርገን ልናረጋጋቸው እንችላለን የሚለው ነው፡፡ ግጭቶች በራሳቸው መጥፎ አይደሉም፡፡ መጥፎ የሚያደርጋቸው አስተሳሰባችን ነው፡፡

ለውጥን መሰረት ባደረገ አስተሳሰብ ከተቃኘ፣ ግጭት የለውጥ መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ፌዴራሊዝም የግጭት መነሻ ነው የሚባለው አመለካከት መሰረት የሌለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት መቻቻልን ያመጣና በሂደትም በመጎልበት ላይ ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም የስርዓቱ አወቃቀር ብዝሃነትን እንደ ውበት አድርጎ የሚነሳ በመሆኑ ነው፡፡ በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነትን በማጠናከር የመቻቻል መንፈስ እንዲዳብር ተደርጎ በህዝቦች ስለተዋቀረ ነው፡፡

ያም ሆኖ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች መነሻውን ድንበር በማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት አሉ። እነዚህ ተግባራት መነሻቸው ህዝብ አይደለም። ህዝብ ለሰላም እንጂ ለግጭት ቦታ ሊኖረው አይችልም። ይሁንና አሁንም ቢሆን ለግጭት የሚሆን ምህዳርን በተቻለ መጠን ማጥበብ ይገባል።

እንደሚታወቀው የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ከመልካም አስተዳደር ችግር፣ ከሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ ህዝቡን በማወያየት ዕርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሱ ነው። በክልሎች በተካሄዱ ሰፋፊ የውይይት መድረኮች ከህዝቡ በተገኘው ግብዓት መሠረት ጥፋት በፈፀሙ አመራሮች ላይ ዕርምጃ መወሰድም ተጀምሯል፤ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ርምጃውን በጥልቀትና በስፋት በማስቀጠል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት መሥራት የግድ ነው። የህልውና ጉዳይም ነው። ምክንያቱም ችግሩ በቅርቡ በተወሰኑ የሃገራችን አካባቢዎች ለሰላም እና መረገጋት መጥፋት መንስኤ ሆኖ ተስተውሏልና። ሰላም ደግሞ የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።

እርግጥ ከማናቸውም ችግሮች በስተጀርባ ግጭቶችን ተገን አድርገው የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳከት የሚጥሩ ኃይሎች መኖራቸው የግድ ነው። እነዚህ የተጀመረውን የሠላም፣ የመልካም አስተዳደርና የህዳሴ ጉዞ ለመቀልበስ በመሯሯጥ ላይ የሚገኙ ኃይሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሰላማችንን ለማድፍረስ፣ የዕድገት ግስጋሴያችንን ለማደናቀፍ ደፋ ቀና ማለታቸው በቅርቡ በኦሮሚያና በጋምቤላ የተከሰቱት ድርጊቶች ሁነኛ አስረጅዎች ናቸው።  

ያም ሆኖ ምክንያቶችን መድፈን ይገባል። ቀዳዳዎችን ያለ አንዳች ሽንቁር መድፈን የግድ ይላል። ለግጭት ሃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት ወሳኝ ነው። ይህን ለመከወን የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎችን በቁርጠኝነት መታገል ይገባል።

በተለይም ግጭትን ቦታ ለማሳጣት የትምክህትንና የጥበት አራማጆችን መታገል የግድ ይላል። እንደሚታወቀው በትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብ የተጠመቁ ኃይሎች ከሁሉ በላይ የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ብዝሃነትን አጥብቀው ይጠላሉ፡፡ የትምክህት ኃይሉ የእኔ ብሄር ብቻ ልዕለ ኃያል የሆነ፣ ቋንቋዬ፣ ባህሌና ማንነቴ ከሌላው የሚበልጥና የተለየ፣ ሁሌም ለመግዛት የተፈጠ ርኩ ነኝ ብሎ ያምናል፡፡

ከዚህ ጐን ለጐንም ሌላውን ብሔርና ዜጋ ተራና ርካሽ፣ ለመመራት እንጂ ለመምራት ያልተፈጠረ ቋንቋው፣ ባህሉና ማንነቱ የወረደ አድርጐ ይቆጥረዋል፡፡ የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንም አይቀበልም። ስለሆነም ብዝሃነትን ደፍጥጦ የራሱን አስተሳ ሰብ፣ ቋንቋና ባህል በሌላው ላይ ለመጫን የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡

ይህ ካልሆነ ሀገር ትጥፋ ህዝብም ይለቅ የሚል ህሳቤም የተጠናወተው ነው። ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ብሔርተኝነትን የማይቀበል፣ የህዝቦች አንድነት ሳይሆን የግዛት አንድነት የሚያሳስበው ኃይል ነው። ከህዝብ ይልቅ ተራራና ወንዝ የሚናፍቅ ፀረ ህዝብ አመለካከት የተጠናወተውም ነው፡፡ የዚህ አስተሳሰብ ተቃራኒ የሆነው ጠባብነትን የተላበሰ ኃይል ደግሞ ሁሉንም ለእኔ እና ለእኔ ብቻ ብሎ የሚያስብ ነገሮችን ሁሉ በጠባብነት መነፅር የሚመዝን የዚህ ዓለም ዕውነታ የሆነውን ብዘሃነትን ተቀብሎና ተቻችሎ መኖር የእሬት ያህል የሚጎመዝዘው ኋላ ቀር አሳቢ ነው። በጠባብነት ድንበር የታጠረ እንደመሆኑ መጠንም ከሱ ብሔር ውጪ ያለ ህዝብ በአካባቢው እንዳይኖር ሌላ ቋንቋ እንዳይነገር ይሰብካል፡፡ ያስባል፡፡ ያልማል፡፡

ይህ የጥበት ሃይል በመስበክ ብቻ ራሱን አያቅብም፡፡ የብሔሩ አባል ሌላውን በጥላቻና በጥርጣሬ እንዲመለከተው ዕድሉ ሲመቻችለትም እንዲያጠቃና እንዲያጠፋው ተግቶ ይሠራል፡፡ በአኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን አይቀበልም። የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፀር በመሆንም ሌላውን ዜጋ ለመጨፍለቅ ይሞክራል—ቢሳካለትም ባይሳካለትም፡፡

ታዲያ የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፅኑ ጠላት የሆኑትና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የሃይማኖት፣ የብሔር፣ የቋንቋና የባህል ብዝሃነት ባለባቸው ሃገሮች ፈጽሞ ሊሠሩ የማይችሉት እነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች፤ በአሁኑ ወቅት በሰላማችንና በልማታችን ላይ የተደቀኑ እንቅፋትና ጋሬጣዎች መሆናችው ፍንትው ብሎ እየታየ ነው፡፡

የትምክህት ኃይሉ በግንቦት ሰባት፣ ጠባብ ኃይሉ ደግሞ በኦነግ ፊታውራሪነት ለራሱ እንኳ መሆን ባልቻለውና ማተራመስና ሽብርን የዕለት እንጀራው ባደረገው የኤርትራ መንግሥት አይዞህ ባይነት ኢትዮጵያን የማፈራረስና ከፈጣን ልማቷ የማደናቀፍ ተልዕኮ ተቀብለው ላለፉት ዓመታት የሽብርና የጥፋት ተግባርን ያለመታከት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳን በመላ ኢትዮጵያውያንና በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ጽናት የጥፋት ተልዕኳቸውን መፈፀም ባይችሉም፡፡

ራሱን ግንቦት ሰባት ብሎ የሚጠራው የሽብርና የብዝሃነት ጠላት የሆነ የትምክህት ኃይል በኢትዮጵያ የሰፈነው የብሄር ብሔረሰቦች የማንነት፣ የቋንቋና የሃይማኖት እኩልነትን ፈጽሞ የማይቀበል፣ በአንድን ብሔር ስም የሚነግድና በተግባር እንደታየው የሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች ደመኛ ጠላት ነው፡፡ የትምክህት ሱሱን መወጣትና የአስመራውን ከፍ ሲልም የአንዳንድ ኢትዮጵያ እንዳታድግ የሚሹ ሃይሎችን ተልዕኮ በመያዝ የቀን ቅዠት ሰንቆ ሽብርና ትርምስ ለመፍጠር አቅዶ ይሰራል—የቀቢፀ ተስፋው አለመሳካት እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡

ገደብ የሌለው የሥልጣን ጥሙን ለማርካት በህዝቦች መካከል ግጭትና መተላለቅን የሚፈጥሩ መርዘኛ መረጃዎችን የሚረጭ ከዚህም የፖለቲካ ትርፍ አትርፎ የአራት ኪሎውን ቤተመንግሥት እቆጣጠራለሁ ብሎ የሚያስብ ከንቱ ድርጅት ነው— ትምክህተኛው ግንቦት ሰባት፡፡  ፊት ለፊቱ የተገተረን እውነታ ለመካድ የሚውተረተር እብሪተኛ ቡድንም ጭምር መሆኑ ይታወቃል፡፡

ከዚህ ቡድን በዓላማም ሆነ በአስተሳሰብ ተቃራኒ የሆነው የጠባብ ኃይልም በኦሮሞ ህዝቦች ደም ሲነግድ በኖረው ኦነግ የተባለ አሸባሪ ድርጅት የሚመራና የኤርትራ መንግሥት የጡት አባቱ የሆነለት የጥፋት ቡድን ነው፡፡ ቡድኑ ‘የኦሮሞን ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ብሔር ገንጥዬ ኦሮሚያ የምትባል ሀገር እፈጥራለሁ’ በሚል የቀን ህልም ውስጥ የተዘፈቀ የሽብርተኞች ስብስብም ነው፡፡

የትላንት ገዥ መደቦች በህዝቦች ላይ የፈፀሙትን በደል ሁሉ የአንድ ብሔረሰብ አባላት እንደፈፀሙት አድርጐ የጥላቻ መርዝ መርጨትና አንዱ ብሔር በሌላኛው ላይ ተነሳስቶ እልቂት ሲፈጥር ማየትም የማይለወጥ ራዕዩ ነው፡፡ ለዚህም ነው— ‘እገሌ የተባለውን ብሔረሰብ አባል ከክልልህ አባረው ወይም አጥፋው’ በማለት የማያቋርጥ ስብከቱን ሲያሰማ የሚኖረው፡፡

በጥበት ሃይልነት የሚነሳው ሌላው አካል ጃዋር መሃመድ የተሰኘው የእነ ግብፅ መንግስት ተቋማት ተላላኪ ነው፡፡ የጃዋር የጥበት መጠን ‘አንገቱን በሜጫ’ እስከሚል አስገራሚ ዲስኩር የሚዘልቅ ነው፡፡ ይህ ግለሰብ በፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ዳረጎት ሰጪነት ያቋቋመውን “OMN” የተሰኘን ጣቢያ በማቋቋም ሀገራችን ውስጥ ብጥብጥ ለመፍጠር ተሯሩጧል። በርካታዎች ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ እንዲቀር አድርጓል። በድሃው የኦሮሞ ልጅ እጅ ፍም እሳትን በመያዝ ወጣቶችን ባልተገባ መንገድ መርቶ ብጥብጥ ፈጥሯል። “አኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የሚል ብሂልን በመከተል በሌላኛው ላይ እሳትን ለመለኮስ ጥረት ማድረጉን እናስታውሳለን፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩት በሶማሌና በኦሮሚያ የድንበር አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት ይኸው ትምክህትና ጥበት የወለደው ችግር ነው። በአጎራባች ክልሎቹ የድንበር አካባቢዎች የተፈጠረው ችግር በምንም መልኩ የየትኛውንም ክልል ህዝብ የሚመለከት አይደለም። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ግጭት የየትኛውም ህዝብ ፍላጎት ሆኖ አያውቅምና። እናም ለግጭት መንስኤ የሆኑትን ትምክህትንና ጥበትን በመታገል የህዝቡን ትክክለኛ የሰላም ፍላጎት መከተል ይገባል። አበቃሁ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy