CURRENT

ግጭቶችን በወቅቱ አለመፍታት እዳው ገብስ አይደለም

By Admin

April 27, 2017

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በዓለም ላይ ካሉ ወጣትና ዘመናዊ ሕገ መንግሥቶች መካከል የሚመደብ የእዚህ ዘመን ወርቃማ ሰነድ ነው፡፡ ይህ በሕዝብ ላብና ደም የተጻፈ የሕዝብ ሰነድ የትናንቱንም ብቻ ሳይሆን የዛሬውንና የነገውንም ጥያቄዎቻችንን ሁሉ በማያሻማ መልኩ የመለሰ የኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብት ነው፡፡ ዛሬ እንደ አገር እየተመዘገበ ላለው ዕድገት ምንጩ ሕገ መንግሥቱን በአግባቡ ሥራ ላይ የማዋላችን እውነታ ነው፡፡ በተቃራኒው አልፎ አልፎም ቢሆን እዚህም እዚያም ለሚከሰቱ ችግሮች አሁንም ምንጩ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ ለሙሉ በአግባቡ ባለመተግበራችን የተነሳ የሚከሰት ነው፡፡ ስለሆነም ለስኬታችንም ሆነ ለውድቀታችን አብዩ ጉዳይ ሕገ መንግሥቱን ተረድተን በምን ያህል ወሰን ፈጽመነዋል የሚለው ጥያቄ ላይ የሚወድቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ከሚመዘገቡ የልማት ድሎች ጀርባ «እኛ አለን» ብለን በድፍረት የምንናገረውንና የምንፎክረውን ያህል ከውድቀታችንም ጀርባ እኛው ራሳችን መኖራችንን በማያወላውል መንገድ መናገር አለብን፡፡ እውነታው ይሄ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ግን ሲሆን አይታይም፡፡ ወይንም እውነታውን ለመቀበል ብዙ ማገዶ እንፈጃለን፡፡ ይህ በመሆኑም ጭምር ነው ከአንዴም ሁለት ጊዜ ወደ ተሀድሶ ልንገባ የቻልነው፡፡

ሕዝቡ ምትክና አምሳያ የሌለውን አንድ ልጁን ሳይቀር እየመረቀ ሸኝቶ ይሄንን ሥርዓትና ሕገ መንግሥት ፈጥሯል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ያስፈጽሙ ዘንድ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ያስቀመጣቸው፣ ጊዜያቸውን ከመበጀትና ሀቀኛ ከመሆን የዘለለ መስዋዕትነት መክፈል የማይጠበቅባቸው በየደረጃው ያሉ የእዚህ ዘመን ልጆቹ ግን የግል ጥቅማቸውንና አጀንዳቸውን በማስቀደም እርስ በእርስ ሲያጋጩት ይታያል፡፡ ነገሩ «የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ፤ ኀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ» እንደሚባለው ተረት አይነት ሆኗል፡፡ እንኳንስ ኢትዮጵያውያን ይቅርና የሌላም አገር ሕዝብ ቢሆን አብሮ በሰላም ከመኖር የዘለለ አጀንዳ የለውም፡፡ ነገር ግን ከሕዝብ የወጡ የፖለቲካ ልሂቃን በግልና በተለያየ አጀንዳዎቻቸው ምክንያት ኢ ሕገ– መንግሥታዊ በሆነ መልኩ በወሠን እርስ በእርስ ሲያጋጩት ይታያል፡፡

ከዚህ አንጻር የሚነሳው የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ከወሰን ማካለል ጋር በተያያዘ በሁለቱ ክልሎች ግጭቶች ሲፈጠሩ ኖረዋል፡፡ በተለይም የዘንድሮው በአይነትም በስፋትም እጅግ የከፋ ነበር፡፡ በጣም የሚገርመው እንደእነዚህ ክልል ነዋሪዎች የበለጸገና የተከበረ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ያለው አለመኖሩ ነው። በዚህም ጭምር ነው የሁለቱ ክልል ተዋሳኝ ሕዝብ የወሰን ማካለሉን በተመለከተ በ1997 ዓ.ም በሕዝበ ውሳኔ የመጨረሻ ውሳኔውን አስታውቆ የነበረው፡፡ ይሄንን ሕዝበ ውሳኔ አክብሮና ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ የሚጠበቅባቸው የሁለቱ ክልሎች የአመራር አባላት ግን ጉዳዩን በራሳቸው አጀንዳና ፍላጎት የተነሳ ተግባራዊ ሳያደርጉት በመቅረታቸው የደረሰው ጥፋት ሁሉ ሊደርስ ችሏል፡፡

ከዚህ ጥፋት በስተጀርባ እጃቸው ያለበት የአመራር አባላት አንድ ሁለት ተብለው ተለይተው የእጃቸው ሊሰጣቸው፤ በዘሩት ልክም ሊያጭዱ ይገባል፡፡ ይሄ ካልሆነና ከቦታ ብቻ ዞር አድርጎ ለመተው ታስቦ ከሆነ እነዚህ ሰዎች ተመልሰው በሕዝቡ ውስጥ የሚገቡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ አርፈው ይቀመጣሉ ማለት ዘበት ነው፡፡

ከ12 ዓመታት በፊት ሕዝቡ ወስኖ የጨረሰውን ጉዳይ ዛሬም ድረስ ሳያስፈጽሙ መጓዝ በእውነት ቀልድ ነው፡፡ ያውም የወሰን ጉዳይ፡፡ በእዚህም ተባለ በእዚያ ይሄንን የሕዝብ ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ዘግይተውም ቢሆን ተስማምተዋል፡፡ አሁን ጥያቄው ይሄንን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግስ ምን ያህል ጊዜ ይወስድባቸዋል? የሚለው ነው፡፡ በሰነዱ ላይ እንደተገለጸው ከሦስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የወሰን ማካለሉን ሥራ ማጠናቀቅ ይገባል፡፡ አመራሩ በዚህ ልክ ቁርጠኛ መሆኑ የሚታየው ወደፊት ነው፡፡ ምክንያቱም ከ12 ዓመታት በፊት የነበረው አመራርም ተመሳሳይ ቃል ገብቶ እንደነበር አይዘነጋምና ነው፡፡ ስለሆነም ታሪካዊውን ስምምነት የፈረሙት የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ቃል በገቡት ልክ ቃላቸውን ተግባራዊ ሊያደርጉና የትናንቱን ጥቁር የመገዳደል ታሪክ በልማት ሊሽሩት ይገባቸዋል፡፡

የፌዴራልና የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት ስምምነቱን ወደ መሬት በሚያወርዱበት ጊዜ አንዳንድ የግል ጥቅም የሚነካባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አተገባበሩን ለማደናቀፍ መንቀሳቀሳቸው አይቀሬ ነው ተብሏል፡፡ ይሄንን ጉዳይ አስቀድሞ በመለየት ከወዲሁ መፍትሔ ማስቀመጥና እልባት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ችግርን አስቀድሞ መለየት አንድ መልካም ነገር ነው፤ በለዩት ልክ እርምጃ መውሰድ ደግሞ ብልህነት ነውና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራልም ይሁን የክልል ባለሥልጣናት ከወዲሁ የቤት ሥራቸውን ይሥሩ፡፡

በስምምነቱ ላይ እንደተገለጸውም የስምምነት ሰነዱ በግጭቱ ወቅት በተገደሉ ንጹሀን ዜጎች ደም የተጻፈ ሰነድ ነው፡፡ ይህንን ሰነድ ከነክብሩ ተግባራዊ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ከዚህ መለስ ግን ዛሬም ድረስ ተመሳሳይ የሆኑ ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች ተመሳሳይ ቁርጠኛ አቋም መወሰድና መሬት ላይ ማውረድ የሚጠይቁ የተዳፈኑ ችግሮች እንዳሉ መታወቅ አለበት፡፡ በሶማሌና በአፋር፣ በደቡብ ሕዝቦችና በኦሮሚያ እንዲሁም በሌሎችም መሰል አካባቢዎች ተመሳሳይ ግጭት በተለያዩ ጊዜያት ያጋጥማል፡፡ እነዚህ ግጭቶች ጊዜያዊ በሆነ መፍትሄ እየተሸነገሉ ዛሬም ድረስ ተጉዘዋል፡፡ መታወቅ ያለበት ግጭት ቆሟል ማለት ዘላቂ መፍትሔ መጥቷል ማለት እንዳልሆነ ነው፡፡ ስለሆነም ከእሳት ማጥፋት የዘለለ ሥራን በተቀሩት ክልሎች ላይም መሥራት የግድ ይላል፡፡

 ethpress