Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጤና እና ትምህርት በሁለተኛው

0 358

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መንግስት ለሀገራችን ማህበራዊ ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት ባለፉት 26 ዓመታት በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ለዘርፉ እጅግ ከፍተኛ በደት በመመደብ ውጤት ማምጣት ችሏል። በተለይም በጤና እና በትምህርት ዘርፎች የተገኙት ውጤቶች ሊወሱ የሚገባቸው ናቸው። አውታሮቹ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ “ዕትዕ” ወቅት ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግበዋል። ታዲያ እዚህ ላይ የመጀመሪያው ዕቅድ ከሁለተኛው “ዕትዕ” ጋር ተመጋጋቢ በመሆኑ፤ በጤና እና በትምህርት ዘርፎች ስናወሳ አብረን የመጀመሪያውን የልማት ዕቅድ በጨረፍታ መመልከታችን አይቀርም።

እንደሚታወቀው የሀገራችንን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ማሳደግ ብቻ በቂ አይደለም። ጥራቱን በማሳደግ ጤናማና ተወዳዳሪ የስራ ሃይል ለመፍጠር ይቻላል። በጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራም በመታገዝ በመሠረታዊ የጤና አጠባበቅና ቁጥጥር አገልግሎት ዙሪያ የህብረተሰቡን የተደራጀ ተሳትፎ ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች እንዲከናወኑ ማድረግ ካለፈው ዕቅድ የሚቀጥል ነው።

በተለይም ጥራቱ የተጠበቀ የሆስፒታል አገልግሎት መስጠቱን ማረጋገጥ፣ ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘም የአገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል፣ ተቋሞቹም በሰው ሃይልና በቁሳቁስ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት መጠናከራቸውን ማረጋገጥ በዕቅድ ዘመኑ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰራባቸው ናቸው። በተለይም የህክምና ባለሙያዎች ፍልሰትን ለመቀነስ እየተደረገ ካለው ጥረት ባሻገር፤ ፍልሰቱን ለማካካስ የህክምና ባለሙያዎችን የማሰልጠን ስራም በከፍተኛ መጠን እንዲያድግ እየተደረገ ነው። ይህ ተግባርም የጤናውን ዘርፍ አሁን ካለበት ደረጃ የሚያሳድገው ነው።

የግሉ ዘርፍ በጤና መስክ የሚኖረውን ሚና ይበልጥ ለማጠናከርና ለማስፋት የሚሰጡት የህክምና አገልግሎቶች ጥራታቸውን የጠበቁ ሁሉንም ወገኖች የሚያረኩ እንዲሆኑ የሌሎች ሀገሮችን ልምድ በመቀመር ተገቢ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት ተዘርግቶ እየተሰራ ነው። በግል ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች እንዲቋቋሙ መንግስት ልዩ ድጋፍ እያደረገ ነው። ለዚህም በቅርቡ ለምርቃት የበቃው ዋሽንግተን ስፒታልን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። እንዲህ ዓይነቱ የግሉ ባለሃብት የተሳተፈበት አሰራር ሀገር ውስጥ ላለውም ይሁን ከውጭ ለሚመጡ ዜጎች ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስለሆነ የውጭ ምንዛሬያችንን በማዳበር ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል። የጤናው ዘርፍ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት ቀደም ሲል የተቀረፀው የጤና መድን ሥርዓት ተሟልቶ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

ከጤና በተጓዳኝ የዜጐችን የስነ ምግብ ፍላጐት እንዲሟሉ በማድረግ ጤናማና ምርታማ ዜጋ ማፍራት በሚል የተዘጋጀው ብሔራዊ የሥነ ምግብ ስትራቴጂ በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ተሰጥቶት ተግባራዊ እየተደረገ ነው። በዚህም የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ የማረጋገጥ፣ የእናቶችና ህፃናት እንክብካቤ፣ የጤና አገልግሎት እንዲዳረስ የማድረግና ጤናማ ከባቢ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ ትኩረት ተሰጥቶት ገቢራዊ እየሆነ ነው።

የድህረ-2015 ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ የልማት ግቦች ከሀገሪቱ የጤና ዘርፍ ግቦች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ ተፈፃሚ ለማድረግም ከወዲሁ ስራው ተጀምሯል። ይህም ጥራቱ የተረጋገጠ የመሠረታዊ የጤና አገልግሎት ሽፋን ወደ 100 በመቶ እንዲደስር የሚያደርግ ነው። የሁለተኛው “ዕትዕ” መረጃች እንደሚያመለክቱት የእናቶች ሞት ምጣኔን በ2012 ዓ.ም ወደ 199/100000፣ ከ5 ዓመት በታች ያሉ የህጻናት ሞት ወደ 30/1000 እንዲሁም ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ሞት ምጣኔን ወደ 19/1000 በመቶ ለማውረድ ግብ ተይዞ እየተሰራበት ነው።

የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ምጣኔ በ2012 ወደ 55 በመቶ ለማሳደግ ግብ የተያዘ ሲሆን በሰለጠኑ ባለሙያዎች በመታገዝ የወሊድ አገልግሎት ያገኙ እናቶች ሽፋን ከ41 በመቶ ወደ 95 በመቶ ለማሳደግ ዕቅድ ተይዞ ተግባራዊ እየሆነ ነው።

በአጠቃላይ ጥራት ያለው ጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማሻሻልና በመከላከል ላይ መሠረት ያደረግ የጤና ፖሊሲን፣ የሥርዓተ-ምግብ ስትራቴጂን አጠናክሮ በመተግበር የመሠረታዊ የጤና አገልግሎት ሽፋንን ከ93 በመቶ ወደ 100 በመቶ ከፍ እንዲል ለማድረግ ግብ ተቀምጦ እየተሰራት ነው። ይህ ሁኔታም የህዝቡን የመኖር ዕድሜ በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 64 ነጥብ 6 በመቶ፣ በ2012 ዓ.ም ወደ 69 ዓመት ያደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። በመሆኑም በሁለተኛው “ዕትዕ” ይህን በህይወት የመኖር ዕድሜን ለማሳካት በአንደኛው የዕቅድ ዘመን የተገኙት ለውጦችን ከዚህ ጋር በማጣመር ማጠናከር ይገባል።

በትምህርት መስክም በመጀመሪያው የልማት ዕቅድ የተገኙትን ውጤቶች ከሁለተኛው “ዕትዕ” ጋር በማስተሳሰር ስራው እየተሳለጠ ነው። በሁለተኛው “ዕትዕ” የትምህርቱ ዘርፍ የህፃናትንና የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ የሚገድቡ ችግሮች ለመቅረፍ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው። ከሀገራችን የትምህርት ግቦች ጋር የሚጣጣሙ የድህረ 2015 ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ የልማት ግቦች የዕቅዱ አካል ተደርገው ተፈፃሚ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ነው።

ትምህርትን በተመለከተ ቁልፉ ጉዳይ ጥራት ቢሆንም፤ ቀጥሎ ትኩረት የሚያሻቸው ከሽፋን ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በመኖራቸው ይህንኑ ጉዳይ ለማሻሻል እየተሰራ ነው። የመጀመሪያው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን የማስፋፋት ጉዳይ ነው። በያዝነው የዕቅድ ዘመን ይህን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም ለቅድመ መደበኛና የጐልማሶች ትምህርት ትኩረት በመስጠት ስራው እየተሳለጠ ነው። እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የመምህራንና የትምህርት ቤቶችን ጥራትና ቁጥር ለማሳደግ የሚወሰዱ ርምጃዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

እርግጥ እቅዱ ከተጀመረ ገና አንድ ዓመት ከመንፈቅን እልፍ ያለ ቢሆንም መንግስት በየደረጃው የትምህርት ጥራትን የማሻሻል ፕሮግራም ዘርግቶ እየሰራ ነው። ለኢኮኖሚ እድገቱና ለማህበራዊ ልማቱ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ ብቁ ዜጋ ማፍራት ቁልፍ ተግባር እንደመሆኑ መጠን፤ መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ስራ በማጠናከር ተገቢውን ተግባር እየተወጣ ነው። ለዚህም የግል ባለሃብቶች በትምህርት ዘርፍ በሰፊው እንዲሳተፉ ማበረታታት፣ ድጋፍ መስጠትና ስታንዳርዱን የጠበቀ ለመሆኑ ተገቢው ክትትልን የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ ነው። በመንግስት የትምህርት ተቋማትም እንዲሁ።

ያም ሆኖ ግን በመንግስት ጥረት ብቻ የትምህርት ጥራት ሊጠበቅ አይችልም። በመሆኑም ህብረተሰቡ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በመደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን ይኖርበታል። በእስካሁኑ ሂደት ህብረተሰቡ የመማር ማስተማሩ አካል እንዲሆን በማድረግ ከጥራት አኳያ የሚነሱትን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት እየተደረገ ነው። ይህ ሁኔታም በቀሪዎቹ የዕቅዱ ዓመታት ተጠናክሮ ከቀጠለ በትምህርት ጥራት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት የሚቻል ይመስለኛል።

በልማት ዕቅዱ ላይ እንደተመለከተው ከተሳትፎ አኳያ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ጥቅል ተሳትፎን በ2ዐዐ7 ዓ.ም ካለበት 43 ነጥብ 2 በመቶ በ2012 ዓ.ም ወደ 80 በመቶ ለማድረስ፣ የአንደኛ ደረጃ (ከ1ኛ-8ኛ ክፍሎች) ንጥር ተሳትፎን አሁን ካለበት 92 በመቶ ወደ 100 በመቶ ከፍ ለማድረግ፣ የሴቶችንና የወንዶችን የትምህርት የተሳትፎ ልዩነትን  በሁሉም እርከኖች ወደ 1:1 (አንድ ለአንድ ምጣኔ) ለማድረስ፣ ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያላቸውን የ1ኛ ደረጃ (1-8) ትምህርት ህፃናት ጥቅል ተሳትፎን ካለበት 4 ነጥብ 4 በመቶ ወደ 15 በመቶ ከፍ ለማድረግ ታስቦ እየተሰራ ነው።

የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎን አሁን ካለበት 39 ነጥብ 3 በመቶ በ2012 ዓ.ም ወደ 74 ነጥብ 2 በመቶ ለማድረስ በማሰብ ስራው እየተከናወነ ሲሆን፤ በከተማ በገጠርና በክልሎች መካከል ያለውን የአጠቃላይ ትምህርት ተሳትፎ ምጣኔ ልዩነት ለማጥበብ እንዲሁም የተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ተሳትፎ ምጣኔን ወደ 95 በመቶ ለማድረስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ከዚህ በተጓዳኝም የቴክኒክና ሙያ ስልጠናን ለማስፋፋት በመንግስት፣ በግል ዘርፍና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ተቋማትን የማስፋፋት ስራ ገቢራዊ በመሆን ላይ ይገኛል። በዚህም የተቋማቱን ቁጥር አሁን ካለበት 1 ሺህ 329 ወደ 1 ሺህ 778 ለማሳደግና በዚህም በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ቢያንስ አንድ ተቋም እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ ነው። በውጤቱም የመደበኛ ሰልጣኞችን ቅበላ አሁን ካለበት 408 ሺህ 838 ወደ 598 ሺህ 729 ከፍ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ነው።

የከፍተኛ ትምህርትን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ቀደም ሲል ከነበሩት በተጨማሪ አስራ አንድ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን በመገንባት በቅድመ-ምረቃ መደበኛ ፕሮግራም 600 ሺህ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም እንዲኖራቸው ይደረጋል። የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ብዛትም ወደ 63ሺ ከፍ እንዲል ግብ ተጥሎ ስራው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወነ ነው። ይህም የሴት ተማሪዎች ተሳትፎን በቅድመ ምረቃ ፕሮግራም በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 32 በመቶ በ2012 ዓ.ም ወደ 45 በመቶ ከፍ እንዲል፣ በሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 22 በመቶ በ2012 ዓ.ም ወደ 35 በመቶ እንዲያድግ እንዲሁም በሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራም በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 11 በመቶ በ2012 ዓ.ም ወደ 20 በመቶ እንዲያሳድግ ታስቦ መሰረታዊ ስራዎች ገቢራዊ እየተደረጉ ነው።

በአጠቃላይ በሁለተኛው “ዕትዕ” የጤና እና የትምህርት ግብ በዚህ መልኩ እየተከናወኑ ናቸው። ሆኖም በአንድ ዓመት ከስድስት ወር አፈፃፀም ብቻ ከወዲሁ ሁኔታውን ለመገምገም ያስቸግራል። ያም ሆኖ ግን በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑት ስራዎች መጪውን ጊዜ የሚያመላክቱ ናቸው። ያም ሆኖ ግን በእነዚህ የማህበራዊ ዘርፎች በ“ዕትዕ” የተቀመጡት ግቦች በቀጣዩቹ የዕቅዱ ጊዜያት ውጤታማ እንደሚሆኑ የመኪያጠያይቅ አይመስለኝም። ታዲያ ማንኛውም የልማት ዕቅድ ያለ ህብረተሰቡ ተሳትፎ ግቡን ሊመታ ስለማይችል እያንዳንዱ ዜጋ ለዕቅዱ መሳካት በንቃት መበሳተፍ የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው እዚህ ላይ ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል።  

  • በማህበራዊ ልማት ዘርፍ ማለትም በትምህርትና ጤና ማስፋፋ  አገራችን ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሏ ፤አገራችን በእነዚህ ዘርፎች የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች በተለይ በአንደኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋንና በጤናው ረገድ ደግሞ በእናቶችና ህፃናት ሞት እንዲሁም  ተላላፊ በሽታዎችን ለ HIV AIDS እና  ወባ ያሉትን በመግታት ረገድ ተጠቃሽ መሆኗን ማሳየት፤
  • በተመሳሳይ የጤና ሴክተሩንም የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በቂ ባለሙያ በማሰልጠን ለሁሉም ጤና ተቋማት ለማዳረስ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ህብረተሰቡም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት በስራዎቻችን ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡
  • የትምህር ቤትና የጤና ተቋማትን በማስፋፋት ረገድ መንግስት ህብረተሰቡን በማሳተፍ  ከፍተኛ ርብርበ በማድረጉ በእያንዳንዱ ቀበሌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትና ጤና ኬላ እንዲቋቋም አድርጓል። በዚህም ህብረተሰቡ አገልግሎቱን በአቅራቢያው ማግኘት በመቻሉ አገራችን ለትምህርት የደረሱ  ሁሉም ህጻናት  ትምህርት እንዲያገኙ  ማድረግ ችላለች። ይህን  ትልቅ ስኬት የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ  ሊሰራበት ይገባል።
  • ህብረተሰቡ የትምህርት ሽፋንን ለማሳደግ ያደረገውን ትብብር  የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ የተጀመረው ዘመቻ ላይ በንቃት በመሳተፍ  ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን ይጠበቅበታል። ይህም የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ ሌላው ትኩረት መሆን መቻል አለበት።

 

 

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy