Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፊት ለፊት ከኢፌዴሪ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር

0 1,750

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፊት ለፊት ከኢፌዴሪ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር      /ዘአማን በላይ/

(ክፍል ሁለትና የመጨረሻው)

ክፍል አንድ ፅሑፌ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በህዳሴው ግድብ የተለያዩ ጉዳዩች ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ አስነብቤያችኋለሁ። ቀሪው ቆይታችን ደግሞ ይህን ይመስላል። መልካም ንባብ።…


በክፍል አንድ ላይ ከተነሳው የዲፕሎማሲ ተግባር አኳያ እዚህ ላይ አንድ እውነታን ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። እርሱም አንድ ሀገር ከሌላ ሀገር ጋር የሚኖረው ግንኙነት ነው። በዲፕሎማሲው ዓለም አንድ ሀገር ከሌላው ጋር ግንኙነት የሚፈጥረው ለራሱ ጥቅም ሲል ነው። ይህ ግንኙነትም የሀገራት መብት ነው። ‘እገሌ የሚባል ሀገር ከእንቶኔ ጋር ለምን ተገናኘ?’ ማለት አይቻልም። እንዲህ ዓይነቱ እሳቤ የሀገራትን ሉዓላዊ መብት እንደ መጋፋትም ይቆጠራል። ከዚህ አኳያ የግብፅ መንግስት የስራ ኃላፊዎች ለራሳቸው የዲፕሎማሲ ስራ ደቡብ ሱዳን ሊሄዱ ይችላሉ። የደቡብ ሱዳኖች ወደ ካይሮ ሊያቀኑ ይችላሉ። ደቡብ ሱዳኖች ሞቃዲሾም ሆነ ካርቱም መሄድ መብታቸው ነው። ወደ አስመራም ቢጓዙ ከልካይ ሊኖራቸው አይችልም። ሌሎችም ሀገራት እንዲሁ። እናም ‘ለምን?’ ተብለው ሊጠየቁ አይገባም።

በመሆኑም አንድ ሀገር ከሌላው ጋር ሲገናኝ ‘በእኛ ላይ ሊዶልቱ ነው’ የሚል እሳቤ መያዝ አይገባም። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩም “…እኛም ከመሰለን ጋር አንድ ግራም የሚጨምርልን እስከሆነ ድረስ የምናደርገው ግንኙነት አለ።…እኛ የያዝነው አቋምና መርህ ከእነዚህ ሀገራት ጋር ሊገነዘቡት፣ ሊከተሉትና ሊያከብሩት የሚገባ ድንበር አለን። ያንን እንዲያከብሩት የማስገንዘብ ተግባር እናከናውናለን። ከግንኙነቱ ጀርባ፣ ፊት ለፊት በጋራ ተፈጥሮ ሃብት በፍትሀዊነት እንጠቀም ብለን የያዝነውን መርህ፣ እየተግባባን የመጣንበትን ጉዞ፣ አሁንም ቢሆን በቀጣይ ልንሰራቸውና ልንግባባቸው ይገባል ብለን የያዝናቸውን የቤት ሥራዎች የምናይበትና የምንራመድበት መንገድ ተጠርጓል። ይህ ይቀጥላል። የእኛን መሰረታዊ መርህ አስቀምጠን ግድባችንን እየገነባን ነው። እናም  መብት ስለሆነ እንደ መንግስት እነዚያ ሀገሮች ለምን ተገናኙ ብለን ግን አናይም።…” በማለት ያስረዳሉ።

ይህ ማለት ግን መንግስት አንድ ሁኔታ ከመከሰቱ በፊትና ሲከሰትም ዝም ብሎ ይመለከታት ማለት አይደለም። እያንዳንዱን ተገቢ ያልሆነና አጥፊ አካሄድን በንቃት እየተከታተለ ምላሽ መስጠቱ የሚቀር አይመስለኝም። አቶ ደመቀም ይህን ዕውነታ “…እንዲህ ሊያደርጉን ነው፣ የሚለው ከኛ ፍላጎት አኳያ ከየትኛውም አቅጣጫ ለሚመጣው ሁልጊዜ ነቅቶ መጠበቅ ይገባል። ይህም ሆኖ ግን የኛን መጠንከር፣ የዚህን ግድብ ዳር መድረስ የማይፈልጉ ብዙ አካላት አሉ። እስከ ተቻለ ድረስ ይህን ክፍተት ለመጠቀም የሚፈልጉትን ነቅቶ ለመጠበቅ ትልቁ አቅም የሀገር ውስጥ ሁኔታ ነው። የህዝቡ አንድነትና ጥንካሬ ነው። መንግሥት ያሉበትን ችግሮች እያቃለለ ጠንክሮ መቆም አለበት። እንደዚህ ጠንክሮ መቆም ካለ፣ የውጭ ፖሊሲያችን በጠብ ጫሪነት ሳይሆን ከሁሉም ጋር ተስማምቶ የሚሰራ ስለሆነ የምናስበውን ጉዞ ወደፊት ከሚያራምድልን ጋር ጥቅምና መብትን አክብረን እንጓዛለን።…” ሲሉ ይገልፁታል። ኢትዮጵያ በቀጣናው ውስጥ የምትጫወተው ሚና ትናንት እንደነበር፤ ዛሬም መኖሩን፤ ነገና ከነገ ወዲያም እንደሚቀጥል የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣናው ውስጥ ጠንካራ ሀገር ሆነን እንዳንወጣ የሚደረግን የክፋትና የአጥፊነት ጥንስስ ሁልጊዜ ቆቅ ሆኖ መጠበቅና መቋቋም እንደሚገባ ያስረዳሉ። በቅርብ ጊዜ እንደተሞከረው በህዳሴ ግድብ ላይ ሻዕቢያ የተለያዩ ዕድሎችን እየተጠቀመ ጥቃት ለመፈጸም የማይፈነቅለው ድንጋይ አለመኖሩን በቅርብ ጊዜ ትውስታነት በማንሳት። እናም “ሁሌም ብልህ ሆነን፣ የውስጣዊ አቅምን አጠንክረን ሊመክትና ወደፊት ሊያራምድ የሚችል ትጥቅ ይዘን መጓዝ አሸናፊነትንና ሌሎችንም ማክበራችንን የሚያረጋግጥ ነው” በማለት ዲፕሎማሲው በሰከነና ከስሜት ውጪ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት ያስረዳሉ።

ርግጥ የህዳሴው ግድብ ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ እንዲሁም ከአርሶ አደር እስከ ምሁር፣ ያለ አንዳች ልዮነት በፍፁም ሀገራዊ ስሜት ተንቀሳቅሰው አሻራቸውን ለማሳረፍ የተንቀሳቀሳቀሱበት ፕሮጀክት ነው። የሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተለይ የሀገራችን ምሁራን ልማቱ የእነርሱው መሆኑን በውል ተገንዝበው ስለ ድግቡ ትክክለኛ ገፅታና ስላለው ጠቀሜታ በማስገንዘብ ረገድ የዜግነት ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም በዚህ ይህን ሃሳብ ይጋራሉ። እናም የምሁራኑን አኩሪ ተግባር “…’የፓናል ኦፍ ኤክስፐርት’ አካሄድ ሲቀየስ፤ አሉ የተባሉ ምሁራን ተሰባስበው የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅና የያዝነውን አቋም ትክክለኛነት ለማብራራት የተጫወቱት ሚና እጅግ በጣም እልህ አስጨራሽና አኩሪ ነው። ብዙ የባለሙያዎች ቡድን ሆነው፣ ከእነዚያ ውስጥ እየተወከሉ ፊት ለፊት እየቀረቡ እልህ አስጨራሽና አኩሪ ሥራ አከናውነዋል። ምናልባትም ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያውያን ብቃት ከዚህ አኳያ ምን ያህል እንደሆነ ሌሎችም ግምት እንዲወስዱ ያደረገ ነው ማለት ይቻላል።…” በማለት ነበር የገለፁት።

እንደሚታወቀው በትናንትናው ኋላ ቀር የዘመን አስተሳሰብ ቅመራ መኖር የሚሹ አንዳንድ የግብፅ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ሚዲያዎች የህዳሴውን ግድብ አስመልክተው የሚሰጡት የተለያዩ የተሳሳቱ አስተያየቶች በግድቡ ዙሪያ ያልተገባ ግንዛቤን የሚያስጨብጡ ናቸው። ማጠንጠኛቸውም ቅላፄያቸውም ‘በሀገራችሁ የተፈጥሮ ሃብት መጠቀም የለባችሁም፤ አንድ ጠብታ ውሃ…ምንትስ’ የሚሉና የሀገራችን ህዝቦች ድህነትን ድል ለመንሳት የሚያደርጉትን ጥረት የሚያኮሰምን ነው። በዚህ ፅሑፍ አቅራቢ እምነት፤ ምንም እንኳን እነዚህ የተዛቡና ኋላ ቀር አስተሳሰቦች የዚያች ሀገር መንግስትና ህዝብ  አቋም ናቸው ተብለው የሚወሰዱ ባይሆኑም፤ የሀገራችን ምሁራን እነዚህን የተዛቡና ከክፍለ ዘመኑ ስልጡን እሳቤ ጋር የማይሄዱ አስተያየቶችን በማረቅና ትክክለኛውን መንገድ በማሳየት የሚጫወቱት ሚና ‘አሌ’ የሚባል አይመስለኝም።

ለዚህም ይመስለኛል—ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ፤ ምሁራኑ ተጨባጭ ሳይንሳዊ ጥናቶችን እያካሄዱ ያንን የምናብራራበትና የምንከራከርበትን ጭብጥ የሚያጠናክሩ ስራዎችን በዩኒቨስርቲዎች ውስጥ እያከናወኑ መሆናቸውን እንዲሁም አጀንዳው ሰፋ ብሎና ህዝባዊ ሆኖ፣ የትውልድ ጉዳይ ሆኖ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ የሚያስረዱት። በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች በሚገርም ሁኔታ በትምህርት ቤት ደረጃ ‘የናይል ክለብ’ እየተደራጁ ዓባይ ልክ ግብፆች ለረጅም ዓመታት እየገነቡ እንደመጡት ሁሉ፤ በሀገራችንም ወጣቶች በክለብ ተደራጅተው ያለንን ሃብት በትክክል ለመረዳት እና ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት አጋዥና ገንቢ የሚሆን ምሁራዊ አቅም ለመፍጠር ዘር እየተዘራ መሆኑን በመግለፅ ጭምር።

ያም ሆኖ በዚህ ፅሑፍ አቅራቢ እምነት፤ በግድቡ ዙሪያ የሚነሱና ከሀገራችንና ከህዝቦቿ ፍላጎት ጋር ፈፅመው የማይዛመዱ ስንኩል እሳቤዎችን በመቀልበስና ትክክለኛውን የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብ አቋም እንዲሁም የግድቡን ትክክለኛ ገፅታ በማሳወቅ ብሎም መከራከሪያና ማንፀሪያ የሚሆኑ እሳቤዎች ከሀገራችን ህዝቦች ፍላጎት ጋር በማስተሳሰር፣ ምሁራኑ ባለፉት ስድስት ዓመታት እንደ ዜጋ ያደረጉትን ርብርብ እስከ ግድቡ ፍፃሜ ድረስም ይበልጥ አጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ይመስለኛል።

በተለይም የተግባቦት ስራን ለተፋሰሱ ሀገራት፣ ለአፍሪካዊ ወንድሞቻችንና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እያንዳንዱን ጉዳይ ዘርዝሮ ከተጨባጭ አመክንዮ ጋር በማዛመድ በማከናወን ሀገራችንና ህዝቦቿ ምን እያደረጉ መሆናቸውን በሚገባ ማስረዳት የግድ ይላል። ይህን በማድረግም በጉዳዩ ላይ ለየት ያለ አቋም ያላቸው ግብፆችም ቢሆኑ ቀደምት የሀገሪቱ ገዥዎች ለዘመናት የዓባይ ውሃን የስልጣናቸው ማራዘሚያ “መድሃኒት” አድርገው ሲጠቀሙበት የነበረውን ዕውነታ ማስረዳት፤ ያ ወንድምና እሀት ህዝብ ከዚያ የተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ ወጥቶ ሃቁን ሚዛናዊና ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዲገነዘበው የሚያደርግ ይመስለኛል።

ታዲያ ይህን ጉዳይ አስመልክተው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ሃሳባቸውን የሚጀምሩት “…የግብፅ ህዝብ ዕውነታውን አይክድም” በማለት ነው። ለጥቀውም “…የግብፅ ገዥዎቸ ሲሸፍኑት በቆዩትና በወረሰው አመለካከት የሚጠበቅ የተሳሳተ ግንዛቤ ይኖራል። በትክክለኛው ዕይታው ግን ወንድሞችና እህቶች በድርቅ እየተጎዱ፣ በድህነት ውስጥ ሆነው፣ ከጓሯቸውና በጉያቸው የተፈጥሮ ሃብት እያለ ይህንን በምንችለው እናልማ፣ እናንተም እንዳትጎዱ በፍትሃዊነት የእናንተም ድርሻ ይከበር በማለት ቢያቀርቡ ይህንን ሃቅ የግብፅ ህዝብ ወደ ጎን የሚገፋው አይደለም። ስለሆነም ህዝብን በትክክለኛ ደረጃ አክብሮ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል” ብለዋል።  

ርግጥም አቶ ደመቀ እንዳሉት የየትኛውም ሀገር ህዝብ ለሌኛው ሀገር ህዝብ ማሰቡና መጨነቁ ባህሪያዊ ነው። ‘እኔ እየበላሁ አንተ ጦም እደር’ የሚል ህዝብ የለም። ህዝብ ሁሌም ሚዛናዊና ፍትሐዊ ነው። እርሱ እየበላ፣ ሌላው እንዲራብ የሚሻ አስተሳሰብን ፈፅሞ አይቀበልም። እናም የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት እንዲሁም ህዝቡ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነቡት ያሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የሚያለሙበት ዋነኛ ምክንያት ድህነትን ለመቅረፍ፣ ድርቅን ለማስወገድና እንደ ሌሎች ህዝቦች በተፈጥሮ ሃብታቸው ተጠቅመው ለማደግ ብቻ ነው። ሌላ ምንም ዓይነት ዓላማ የላቸውም። ወንድምና እህት ለሆነው የግብፅ ህዝብ ይህን በተገቢው ሁኔታ ማስረዳት ከተቻለ፤ ሁሉም ወገን ተጠቃሚ፣ አሸናፊና ‘አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ’ ተባብሎ የተፈጥሮ ሃብትን በጋራና በእኔነት መንፈስ አልምቶ መጠቀም ይቻላል።

የግብፅ መንግስት በግልፅ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የሚናገረው እንዲሁም የሀገሪቱ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚገልጿቸው ጉዳዩች የተለያዩ መሆናቸውን በተመለከተ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጠይቀናቸው ነበር። እናም ለጥያቄያችን ምላሽ የሰጡት “…ያንን እንደ አመጣጡ መመከት ነው” የሚል ቅልብጭ ያለ ምላሽ በመስጠት ነው። አክለውም “…ማንኛውም ግብፃዊ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ የትኛውም አመለካከት ይኑረው በዓባይ ጉዳይ ላይ አምባሳደር ሆኖ እየሰራ ነው። ከዓለም ባንክ አለ እስከ ተባለ ድርጅት ድረስ በየትኛውም ስምሪት አምባሳደር ሆኖ እየሰራ ነው። እኛም ተመሳሳይ ስራ ማከናወን የሚችል አሁን እየወጣ ያለ ምሁር አለን።…ግብፆች ለእኛ መዳከም እንደሚጥሩ ግልፅ ነው። ሆኖም የትኛውም ዓይነት አመለካከት ቢኖር፤ ይህን ተፈጥሮ ሃብት ማልማት የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው። ሥራው ታሪካዊ ነው ብሎ መነሳትና እንደ አመጣጡ መመከት ይገባናል። እናም ለምሁራኑ ትችት እንደ አመጣጡ በምሁራን መመከትና መድረኩ የሚጠይቀውን መልስ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል።…” በማለት የፊት ለፊትና የበስተጀርባ ያሉ ጉዳዩችን በመለየት ዕውነታዎችን ማስተካከል የሚችል ትጥቅ መታጠቅ እንደሚገባ አስረድተዋል።

በዚህ ፅሑፍ አቅራቢ እምነት፤ የግብፅ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር በግድቡ ጉዳይ በጋራ ለመስራት ተስማምቶ ሲያበቃ፤ ወዲያውኑ የሀገሪቱ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃን ከስምምነቱ ጋር የሚፃረሩ ጉዳዩችን መሰንዘራቸው የተለመደ ነው። እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲህ ዓይነቱ አካሄዳቸው እንደ “ፋሽን” የያዙት ይመስላል። ያለፉትን ጊዜያት “ፋሽኖች” ትተን የቅርቡን ብንመለከት እንኳን፤ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ለመታደም የአህጉሪቱ መዲና ወደ ሆነችው አዲስ አበባ የመጡት የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ እግረ መንገዳቸውን ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝተው በሁለትዩሽ ጉዳዩች ዙሪያ ስምምነት ደርሰው በነበሩበት ወቅት በግብፅ ሚዲያ አማካኝነት የተነዛውን አሉባልታ ማየት ይህን አባባኬን የሚያጠናክረው ይመስለኛል።

በወቅቱ ፕሬዚዳንት አልሲሲ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ተሳትፈው ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ውይይትና ስምምነት አድርገው ወደ ካይሮ እንደተመለሱ፤ አንድ የግብፅ ሚዲያ ገና ምንም ዓይነት መግባባት ያልተደረሰበትን “የግድቡን የውሃ አያያዝ” አስመልክቶ ‘ኢትዮጵያ ግድቡ በ21 ዓመታት ውስጥ ውሃ እንዲይዝ ተስማማች’ የሚል አስቂኝ ዘገባን ማቅረቡን አስታውሳለሁ። ይህን “ከፈረሱ የቀደመ ጋሪ” ዓይነት ቅጥፈት ፅንፈኛው ሚዲያም አብሮ አራግቦታል—ሰሚ ባያገኝም።

ምንም እንኳን በግሌ ሁሉንም አሉባልታዊ ዲስኩሮች እየተከታተሉና ስንዴውን ከእንክርዳዱ ሳይለዩ ለአሰስ ገሰሱ ሁሉ ምላሽ መስጠት ይገባል የሚል እምነት ባይኖረኝም፤ እንዲህ ዓይነቱ የተሳሳተ ዘገባ ምናልባትም ያለፉት የግብፅ ገዥ መደቦች የዓባይን ጉዳይ እንደ ጭንቀት ማስተንፈሻ ይጠቀሙበት እንደነበር እየተገነዘበ የመጣውን የዚያን ሀገር ህዝብ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስደው ስለሚችል አቶ ደመቀ እንዳሉት “መድረኩ የሚጠይቀውን ምላሽ” ትክክለኛና ተደራሽ በሆነ መንገድ መስጠት የሚገባ ይመስለኛል። ይህ ደግሞ ከሀገራችን የግልም ይሁን የመንግስት ሚዲያ እንዲሁም ከጦማሪዎች የሚጠበቅ የዜግነት ግዴታ ይመስለኛል።

እንዲህ ዓይነቱ ምላሽ የህዳሴውን ግድብ የሃይድሮ ሜካኒካል ስራዎችን ወስዶ ተግባሩን በሀገራዊ ቅኝት እየከወነ በሚገኘው ሀገር በቀሉ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዙሪያ ለሚነሱና ከእውነታው ጋር የሚጣረሱ አሉባልታዎችን በመመከት መስጠት ይገባል። ከዚህ አኳያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን በዚህ ሀገር በቀል ተቋም ላይ ፅንፈኛ ዲያስፖራዎችና ሚዲያዎቻቸው ስለሚነዙት አሉባልታ ጠይቀናቸው ነበር። እርሳቸውም ምላሻቸውን የጀመሩት ሉዓላዊ ሀገርን በማብራራት ነው። “ሉዓላዊ ሀገር ማለት በሀገር ቤት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ‘ወርልድ ክላስ’ (ዓለም አቀፋዊ ደረጃ ያለው) ስራ ሊያከናውን የሚችል  ሀገራዊ አቅም መገንባት ነው።…” በማለት የስኬታማ ሀገሮችን ተሞክሮ የቃኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አኳያ ‘ሜቴክ’ በህዳሴው ግድብ አሊያም በስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ውስጥ ገባ ማለት ተቋሙ ሀገራዊ አቅም ገንብቶ እንዲወጣ አቅጣጫ መከተላችንን ያሳያል ይላሉ። ውሳኔውም የሀገራችን ዘላቂ ልማትና የሉዓላዊነታችን አንዱ መገለጫ መሆኑን በማስመር። ይህም ዋናው ስራ ስራ ሳይበደል “ሜቴክ”ን ንዑስ ተቋራጭ አድርጎ ወደ ስራው እንዲገባና አቅም እንዲገነባ መደረጉ፤ በአሁኑ ወቅት ሲገመገም ትክክለኛ መንገድ እንደነበር መረጋገጡንም ያስረዳሉ—በ“ሜቴክ” ተሳትፎ ውጤታማና አርኪ ስራዎች መሰራታቸውን በመጠቆም።

ርግጥ አቶ ደመቀ እንዳሉት፤ “ሜቴክ” በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ መሳተፉ በአንድ በኩል ከዋናው ተቋራጭ ከሳሊኒ ኢምፔርሎጆ ጋር እየተማረ፣ ሳሊኒም ከእርሱ ትምህርት እየወሰደ ሀገር በቀሉ ተቋም በስራው ላይ በመሳተፉ በግድቡ ኃይል የማመንጨት አቅም ላይ ብዙ ለውጦች ሊገኙ ችለዋል። አዎ! “ሜቴክ” በግንባታ ስራው ላይ ተሳታፊ በመሆኑ፤ ግድቡ ገና ሲወጠን 5 ሺህ 250 ሜጋ ዋት እንዲያመነጭ ተይዞ የነበረውን ዕቅድ በስድስት ዓመት ውስጥ የአንድ ሺህ ሁለት መቶ ሜጋ ዋት ጭማሪ በማስገኘት ወደ 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት ከፍ ማድረግ ተችሏል። ምናልባትም ነገ ደግሞ አዲስ ለውጥ ሊገኝ ይችላል። ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት የተገኘው ለውጥ የአንድ ትልቅ ግድብ የኃይል ማመንጫ አቅርቦትን የሚያህል ነው። እናም ይህ በተጨባጭ የሚታይ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ እመርታን በማንኳሰስ ጥላሸት ለመቀባት የሚደረግ ተግባርን በተገቢው መንገድ መመከት የግድ ይላል።

የ“ሜቴክ” ተሳትፎ ግድቡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ክብረ ወሰኖችን እንዲሰብር ያደረገ ነው። ከዚህ አኳያ እንደ አውሮፓውያኑ ቀመር አቆጣጠር ከጃንዋሪ 2015 እስከ ዲሴምበር 2015 ድረስ ባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ውሰጥ 2,906,283 ኪዩቢክ ሜትር ሮለር ኮምፓክትድ ኮንክሪት የመሙላት፣ በሁለት ወራቶች ውስጥ (ከኖቭመንበር እስከ ዲሴምበር 2015 ድረስ) 608,877 ኪዩቢክ ሜትር ሮለር ኮምፓክትድ ኮንክሪት የመሙላት፣ 331,276 ኪዩቢክ ሜትር ሮለር ኮምፓክትድ ኮንክሪት በአንድ ወር ውስጥ ብቻ (በዲሴምበር 2015) የመሙላት፣  እና በ24 ሰዓት (በዲሴምበር 28 ቀን 2014) 23,200 ኪዩቢክ ሜትር ሮለር ኮምፓክትድ ኮንክሪት በመሙላት ግድቡ የዓለም ክብረ ወሰንን እንዲሰብር ማድረጉን መገንዘብ የሚቻል ይመስለኛል። በክብረ ወሰን መስበር ረገድ ከምንታወቅበት የአትሌቲክሱ ዘርፍ ወሰ ቴክኖሎጂም እየተሸጋገርን ነው። ይህም በአንድም ይሁን በሌላ መልክ “ሜቴክ” እና በግድቡ ላይ የሚሳተፉ ሌሎች አካላት ውጤት መሆኑ አይዘነጋም።

በአጭሩ በዚህ ሀገር በቀልና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ ላይ በሚገኝ ተቋም ላይ ሆን ተብለው በፅንፈኛው ዲያስፖራና በመሰል ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች የሚሰነዘሩ ጥላሸት የመቀባት ተግባር ተገቢ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን፤ በየጊዜው ተገቢው የተግባቦት ስራ ሊከናወንበት ይገባል። ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎቹ ይህን የሚቃወሙት ሀገራችን በራሷ ሀገር በቀል ቴክኖሎጂ እንዳታድግና ሁም የውጭ ኩባንያዎችን አንጋጣ እንድትመለከት መሻት በመሆኑ ዕውነታውን ከዚህ አኳያ እየቃኙ ተገቢውን ምላሽ መስጠት የግድ ይላል—የፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎቹ የጥላቻ ዲስኩርና መሬት ላይ ያለው የተቋሙ ስኬታማ ተግባራት “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” እንዲሉት ዓይነት ነውና።

ከሀገራችን የልማት ትልም አኳያ የህዳሴው ግድብ ብቸኛው ሜጋ ፕሮጀክት አይደለም—አንዱና ዋነኛው እንጂ። ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ትላንትም ነበሩን፤ ዛሬም አሉን፤ ወደፊትም ይኖሩናል። ትልቁ ጉዳይ ከትናንቱ ዛሬ፣ ከዛሬው ነገና ከነገው ከነገ በስቲያ የምንቀምራቸው ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎች ናቸው። ያም ሆኖ ይህ ፕሮጀክት ላለፉት ስድስት ዓመታት የሀገራችን ህዝቦች ቃላቸውን ጠብቀው የገነቡት በመሆኑ በተለየ ሁኔታ ሊታይ የሚገባው ይመስለኛል። እናም ይህን ፅሑፍ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አባባል ልቋጨው ወደድኩ—“…የጀመርነውን ለመጨረስ ወደ ከፍታው ተቆናጠናል፤ ዳር ለመድረስ ግለታችን ተጠብቆ ሊቀጥል ይገባል፣ ሁሉም በዚህ ዙሪያ የድርሻውን ይወጣ፤ ቃላችንን እንጠብቅ።…” በሚለው። አዎ! ነገም እንደ ትናንቱና እንደ ዛሬው በሙሉ አቅማችን ግድቡን በመገንባት የ“ይቻላል” መንፈስን በተግባር አረጋግጠን ከማጋመስ ከፍ ያልንበትን ፕሮጀክት ከፍፃሜው እንደምናደርሰው ማንም ሊጠራጠር አይገባም—ሁሌም ቢሆን ህዝብ የያዘው ነገር በስኬት መጠናቀቁ አይቀርምና!  

                                                     

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy