ሁለቱ አገሮች አጠቃላይ የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር ይመክራሉ
በሱዳን ወደብ ለኢትዮጵያ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ተርሚናል ተሠርቶ ተጠናቋል
የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አህመድ አል በሽር፣ በኢትዮጵያ የሚከሰት ማንኛውም የደኀንነት ችግር የሱዳንም ሥጋት መሆኑን ተናገሩ፡፡ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር አጠቃላይ የኢኮኖሚ ውህደት እንድትፈጥር ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር እየመከሩ ነው፡፡
ከመጋቢት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ያለውን የሱዳን የልዑካን ቡድን መርተው የመጡት ፕሬዚዳንት አል በሽር፣ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር እስከ ዛሬ የተፈራረመቻቸውን ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ወህደት ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር በመምከር ላይ ናቸው፡፡
ጉብኝቱን በተመለከተ ሁለቱም መሪዎች በጋራ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ ፕሬዚዳንት አል በሽር በኢትዮጵያ ሊከሰት የሚችል ማናቸውም ዓይነት የደኅንነት ሥጋት የሱዳንም እኩል ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጭፈራችን እንኳን ሳይቀር የትኛው የማናችን እንደሆነ መለየት ያስቸግረኛል፤›› በማለት የሁለቱም አገሮች ግንኙነት ታሪካዊና ጥንታዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ የተገኙ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ጭብጨባ በታጀበው ንግግራቸው፣ ‹‹እኛ አንድ ነን፣ የአንዳችን ችግር የሌላችንም ሕመም ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ግንኙነታችን ገደብ አይኖረውም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቱ አባባል ከሆነ፣ የኢትዮጵያንና የሱዳንን ደኅንነት ነጣጥሎ ማየት አይቻልም፡፡ ‹‹የአንዳችን ችግር የአንዳችን ሕመም መሆኑን እኛ መሪዎች አምነን ተስማምተናል፡፡ ይህንን የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲፈጽሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይገፉበታል ብዬ አምናለሁ፤›› ብለዋል፡፡
የሁለቱ አገሮች ውህደት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ዘርፎችን ያጠቃለለ እንደሆነም በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ፕሬዚዳንቱ ግብዣቸውን አክብረው ‹‹ወደ ሁለተኛ ቤታቸው›› ኢትዮጵያ መምጣታቸውን አድንቀው፣ ሁለቱም መሪዎች አዲስ አበባና ካርቱም መመላለሳቸው የተለመደ ቢሆንም፣ የአሁኑ የተለየና ለሁለቱም ሕዝቦች ትልቅ ትርጉም ያለው ጉብኝት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይኼኛው ጉብኝት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት መሆኑን አስታውሰው፣ በቅርቡ ከአዲስ አበባ – ካርቱም የአውቶብስ ትራንስፖርት መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡ እንደ ፕሬዚዳንት በሽር የሁለቱም አገሮች ደኅንነት የማይነጣጠል መሆኑን አስምረውበታል፡፡
ሱዳንን ከኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በመንገድና በንግድ የማስተሳሰር ጉዳይ የቆየ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ በሁለቱ አገሮች ስምምነት የተደረሰባቸውን በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ፣ የሁለቱ አገሮችን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ውህደትና መስተጋብር ለመፍጠር እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባና ካርቱምን የሚያናኘቸው የባቡር መስመር ግንባታ ጥናት ተጠናቆ ሥራውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሱዳን ወደብ ለኢትዮጵያ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ነፃ ተርሚናል ማዘጋጀቱንም አመስግነዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱን ‹‹ወንድሜ›› በማለት ቅርበታቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ በሁለቱም አገሮች መካከል ለመፍጠር የታሰበው የኢኮኖሚ ውህደት በቀጣናው ላሉት የኢጋድ አባል አገሮች ብሎም ለአፍሪካ አገሮች ቁጥር አንድ አብነት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት አል በሽር ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ነፃ የሸቀጦች ልውውጥና ነፃ የሰዎች ዝውውር በመጀመር የሁለቱን አገሮች የኢኮኖሚ ውህደት ለማፋጠን እንደሚሠራ ገልጸው፣ እስካሁን በመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ የተከናወነው ሥራ ከፍተኛ መኖሩን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያና በሱዳን የታሰበው መጀመርያ የኢኮኖሚ ቀጥሎ ወደ ፖለቲካ ውህደት በማስፋት በአካባቢው አንድ የጋራ ማኅበረሰብ መፍጠር ያለመ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ በቀጣናው የሚታየውን ስደት፣ ድርቅና ረሃብ ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት እንደሚቻልም አክለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር ወደ አዲስ አበባ የሚመጡትን ያህል ወደ አስመራም የሚጓዙ ሲሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱት ወዳለው አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ኤርትራንም ለማምጣት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ዝርዝር ውስጥ ከመግባት ግን ተቆጥበዋል፡፡ በሁለቱም አገሮች ከፍተኛ የጋራ ኮሚሽን፣ የቴክኒክ ኮሚቴና ዓቢይ ኮሚቴ የተፈረሙ ስምምነቶችን ወደ መሬት ለማውረድ በቅርቡ ሥራ ይጀምራሉ ተብሏል፡፡
ሱዳን ከግብፅና ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን የምትሳተፍበት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር አባል ስትሆን፣ በግድቡ ላይ የተጀመረው ድርድር ፍሬያማ ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውጪ በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ውስጥ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስና የደኅንነት ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያና ሱዳን በጋራ እንደሚሠሩ ተገልጿል፡፡