Artcles

የሀገራችን ፌዴራሊዝምና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት

By Admin

April 04, 2017

የሀገራችን ፌዴራሊዝምና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት /ታዬ ከበደ/

የፌዴራል ስርዓታችንን ልዩ የሚያደርገው አንደኛው ጉዳይ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸው ነው፡፡ ይህም የፌዴራሉ መንግስት ቅርፀ- መንግስትነት ከሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የመነጨ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ከዚህም እነዚህ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች የፌዴራሉን ስርዓት በራሳቸው ይሁንታና ስምምነት መፍጠራቸውን መገንዘብ እንችላለን፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ካላቸው ስልጣን ቆርሰው ለፌዴራል መንግስቱ በመስጠት የሀገሪቱ አስተዳደር በመረጧቸው ተወካዮች አማካኝነት እንዲንቀሳቀስ ፈቅደው ተስማምተዋል፡፡ ለዚህ አንዱና ዋነኛው ማስረጃ ህገ-መንግስቱ በመግቢያው ላይ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች …”  በሚል ሐረግ መጀመሩ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ሌላኛው ልዩ ባህሪ ህብረ – ብሔራዊ መሆኑ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የየትኛውም ዓይነት ፌዴራሊዝም ዋነኛ ዓላማ በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በልዩነታቸው ውስጥ ያለውን አንድነት አቻችሎ በጋራ እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ እናም በውስጧ ከ80 በላይ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የያዘችው ሀገራችን ከፌዴራሊዝም ውጭ ሌላ ምርጫ ሊኖራት አይችልም፡፡

ስለሆነም እነዚህ ህዝቦች በልዩነታቸው ውስጥ ያላቸውን አንድነት ለማጠናከር እንዲሁም ተፈቃቅደውና ተከባብረው በመኖር የጋራ ቤታቸው የሆነችውን ሀገራችንን ለማልማት ቃል ኪዳን ገብተዋል፡፡ እነዚህ ህዝቦች በራሳቸው ቋንቋ እየተጠቀሙና እየተዳኙ ብሎም ባህላቸውን እያሳደጉ ከፌዴራሉ አንድነት የሚገኘውን የጋራ ጥቅም በመቋደስ የአብሮነት ጉዟቸውን ምቹ አድርገዋል፤ ውጤታማም ሆነዋል፡፡

በአንቀጽ 39 ስር የተደነገገውና የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል መብትም የሀገራችንን ፌዴራሊዝምን ልዩ ገጽታ የሚያላብሰው የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡

ይህ አንቀፅ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድና በአንድነት መኖር የሚያስችላቸውን ዴሞክራሲያዊ የአንድነት ዕድልንም አብሮ ይሰጣል፡፡ ታዲያ ይህን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመፍጠር ህዝቦች የእኩልነት መብታቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

በመሆኑም በአንቀጹ አማካኝነት የእኩልነት መብት ማረጋገጫ የሆኑት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮች ወዘተ ተከብረዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በፖለቲካዊ አስተዳደር በኩል እኩል የመሳተፍ መብት ያገኙ ሲሆን፤ በልማት ስራው ላይም እኩል ዕድል እዲያገኙና በውጤታቸው መሰረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል፡፡

ታዲያ እነዚህን መብቶች ሁሉ ያረጋገጠ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በምን ምክንያት ሊገነጠሉ ይችላሉ? የመብቶቹ ባለቤት በመሆኑም ጥቅሞቹን እያጣጣመ የፌዴራል ስርዓቱን ያጠናክራሉ እንጂ በምን ዓይነት የሂሳብ ቀመር ሊበታተኑ ይችላሉ?

በመሆኑም አንዳንድ ወገኖች በአንቀጽ 39 ላይ ያላቸው የስጋት ምንጭ ቀዳሚዎቹን አሃዳዊ ስርዓቶች ከመናፈቅ የመጣ አሊያም ህገ -መንግስቱን ቀድዶ ለመጣል ከመፈለግ የመነጨ ከመሆኑ በስተቀር እስካሁን ድረስ ያለው ተጨባጭ እውነታ የመበታተን ስጋትን የሚያመላክት አይደለም፡፡

ይህ የሀገራችን ተጨባጭ ሃቅም በመስኩ ምሁራን የተረጋገጠ ነው፡፡ የፌዴራሊዝም ምሁሩ ጆርጅ አንድርሰን እንደሚናገሩት፤ ምንም እንኳን የመገንጠል ጥያቄ ሊኖር የሚችለው በፌዴራል ስርዓቱ ውስጥ ነው ተብሎ ቢታሰብም እስካሁን ድረስ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያመላክተው አብዛኛዎቹ አሃዳዊ መንግስታት መበታተናቸውን ነው፡፡ እግርጥም “አራምባና ቆቦ” ስጋት ይሏል እንዲህ ነው፡፡

ያም ሆነ ይህ፤ በፌዴራሊዝም ስርዓታችን ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኘው አንቀጽ 39 የአንድነታችን ዋስትና እንጂ የመለያየታችን ስጋት ሊሆን አይችልም፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙና ይህ አንቀጽ የሌላቸው ሀገራት በብጥብጥና በሁከት እየታመሱ ያሉትም በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን ማምጣት ባለመቻላቸው መሆኑን ካሉበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር መመልከታችንም የዚሁ ውጤት ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት፤ በግጭት ውስጥ እየታመሱ ያሉት እነዚያ ሀገራት ይህ አንቀጽ ቢኖራቸው ኖሮ እስካሁን ድረስ የተከሰተው ሰብዓዊና ማቴሪያላዊ ቀውስ ባልተፈጠረ ነበር፡፡

ታዲያ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ያለምንም ገደብ ያረጋገጠ ቢሆንም ዓላማው በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን በሀገሪቱ ላይ ለማምጣት እንደሆነ መገንዘብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡

የምንከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት አባሎቹ የሚናቆሩበትና የሚባሉበት ሳይሆን አብረው በፈቃዳቸው በጋራ የሚያድጉበት ስርዓት መሆኑ ሌላው ልዩ ባህሪው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ ተባብረውና ተጋግዘው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ተደርጎ የተቀረጸው የፌዴራሉ ስርዓት በህገ – መንግስቱ ላይ በግልጽ መንጸባረቁ የጥንካሬው መገለጫ ነው፡፡

የህገ- መንግስቱን መግቢያ ቆንጥረን ብንወስድ እንኳን “…ጥቅማችንን፣ መብታችንንና ነጻነታችንን በጋራና በተደጋጋፊ ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን…” የሚለው ሃሳብ የፌዴራላዊ ስርዓቱ መገለጫ ህብረ – ብሔራዊነት ብቻ ሳይሆን መተጋገዝም ጭምር መሆኑን አመላካች ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም “መንግስት በዕድገት ኋላ ለቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልዩ ድጋፍ ማድረግ አለበት” የሚለው የህገ – መንግስቱ አንቀጽ 89 (4) የዚህ የመተጋገዝ ፌዴራሊዝም መገለጫ ተደርግ የሚወሰድ መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በጥቅሉ በእነዚህ ጥቅሞች አማካኝነት በተፈጠረው የሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ምላሾቹም ዘላቂ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን እውን የሚያደርጉ ከመሆናቸውም በላይ፤ በርካታ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች፣ ባህሎችና ታሪኮች ያሏቸው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፌዴራሊዝም ስር በመሆን ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸው እንዲጎለብት አስችለዋቸዋል፡፡

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ልዩነታቸው የስጋት፣ የአደጋ ብሎም የጦርነት ምንጭ ሳይሆን በራሳቸው ፈቃድ በመሰረቱት ፌዴራላዊ ስርዓት ጥላ ስር ሆነው በአስተማማኝ የሰላም ጎዳና ላይ መጓዝ ከጀመሩ እነሆ 22 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በድላቸው ባረጋገጡት አስማማኝ ሰላምም፤ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በህገ – መንግስቱ ዓላማ ጥላ ስር ሆነው የልማት ተጠቃሚነታቸውን በየደረጃው ይበልጥ ዕውን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ውጤቶች በፌዴራል ሥርዓቱ አማካኝነት ያገኘናቸው ትሩፋቶች እንደመሆናቸው መጠን፤ ፌዴራሊዝም የጦርነት ደመናን ገፍፎ በሰላም መንደር ውስጥ እንድንኖር ብሎም እንዲሁም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ያረጋገጠልን ነው ማለት እንችላለን፡፡ በተለይም የህገ መንግስቱ አንቀፅ 39 ለህዝቦች ሁለንተናዊ መብቶችን ያጎናፀፈ በመሆኑ፤ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድ የጋራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ፈጥረው እንዲኖሩ በማድረግ ልዩነትን ያጠበበ ነው ማለት ይቻላል፡፡