Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዳሴው ግድብ ብሔራዊ ኩራታችን ነው!

0 391

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዳሴው ግድብ ብሔራዊ ኩራታችን ነው!    /ታዬ ከበደ/

 በዓባይ ውሃን የመጠቀሙ ጉዳይ ላንዱ የቤት፣ የሌላው የጎረቤት ሆኖ በመቆየቱ፤ ለዘመናት የድህነትና የኋላቀርነት መገለጫ ሆነን እንድንሻገር ተገደናል፡፡ በውሃ ሀብታችን እንዳንጠቀም በተጣለብን ገደብም ለተደጋጋሚ ጊዜ በርካታ ዜጎቻችንን በድርቅ ከጉያችን ተነጥቀናል። በዚህም ሀገራችን በውሃ እጥረት ሳቢያ ዜጎች ለሞት የሚዳረጉባት ብቸኛዋ የአለማችን የውሃ ሃብት ባለቤት ሆና ከመቆየቷ ባሻገር፤ የውሃ ሀብቷ የቁጭቷ ምንጭ ብቻ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ሆኖም እነዚህን ሁኔታዎች መቀየር ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግስት ሀገራዊው የፀረ – ድህነት ትግሉን በማቀጣጠል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራን ይፋ አድርጓል፡፡ በእርግጥም የግድብ ግንባታ ለዘመናት የዘለቀውን የድህነትና የኋላቀርነት ታሪካችንን የመቀየርና ያለመቀየር ጉዳይ አንዱ ምክንያት በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳነቱ አያጠያይቅም፡፡ በመሆኑም የግድቡን ግንባታ የማሳካቱ ጉዳይ የአሁኑን ትውልድ ህይወት የመለወጥና ያለ መለወጥ ጥያቄና ውሳኔ ብቻ አይሆንም— የቀጣዩን ትውልድ ህልውና የማረጋገጥና ያለማረጋገጥ ብሎም ሀገራዊ ህልውናን የማስቀጠል ታላቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው እንጂ፡፡

እናም ለሀገራዊ ህልውናችን ቀጣይነት፣ ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ኑሮ መሻሻልና ከድህነታቸው መውጫነት ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የህዳሴው ግድብ ብሔራዊ አጀንዳችንና ኩራታችን ነው። በተፈጥሮ ሃብታችን እንድንኮራም ያደረገን ነው። ይህን የተፈጥሮ ሃብታችንን ማልማት ድህነትን መታገል መሆኑ መንጋት የለበትም።

እንደሚታውቀው ሀገራችንን ጨምሮ ሁሉም የላይኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት በድህነት የሚማቅቁና በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቁና ናቸው። በዚህም ሳቢያ በአመዛኙ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ እርዳታ ለመጠበቅ ይገደዳሉ፡፡ ቀደም ሲል ያገኙት የነበረው የዝናብ መጠን ከመቀነሱና በአየር መዛባት ሳቢያ ዜጎቻቸው  በረሃብና በእርዛት ለመገረፍ ከመገደዳቸውም በላይ ለእልቂት ተዳርገዋል፡፡ ግድቡ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉትና ለሀገራችንም ሆነ ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚነት ጉልህ ድርሻ የሚያበረክት ነው፡፡

ከዚህ አኳያም ሀገራዊ ፋይዳውን ስንመለከት ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የፀረ – ድህነት ትግል ከግብ በማድረስ ለህዳሴው ጉዞ ስኬት የሚያበረክተው ሚና የላቀ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ የሀገራችንን የኤሌትሪክ ሽፋን የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ፤ ለዘመናት መብራት እንደ ገነት ለራቀው የገጠሩ ህዝባችን ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ይህም ለከፍተኛው የደንና የመሬት መራቆት ችግር እንዲሁም ሊከሰት የሚችለውን የአየር መዛባትና የሚያስከትለውን የድርቅ አደጋ የሚያስቀር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሃይል አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ለሚደርሰው የጤና ችግር እልባት ይሰጣል፤ መሳ ለመሳም ለህክምና የሚወጣውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ይህም ፋይዳውን ድርብ ድርብርብ ያደርገዋል፡፡

ግድቡ ከዚህም የላቀ ፋይዳ አለው፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅ የኤሌትሪክ ሃይልን ለጎረቤት ሀገሮች መሸጥ ይቻላል። ይህም በድህነት ለሚሰቃየው ህዝባችን ህይወትና ኑሮ መሻሻል የሚረዳ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ይሆናል፡፡ እናም ከሽያጩ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ የሀገሪቱን ዕድገት በማፋጠን ለዜጎች ኑሮ መለወጥ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም፡፡ በመሆኑም የግድቡ ግንባታ በድህነትና በኋላቀርነት የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ ስለሆነ የህልውናችን መሰረት መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላል፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ ሊዘነጋ የማይገባው ነገር ቢኖር፤ ሀገራችን ምንም እንኳን ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ የምትከተልና ውጤታማ መሆኗ የሚታወቅ ቢሆንም ቅሉ፤ ወደ ኢንዱስትሪው መር ኢኮኖሚ መሸጋገሯ የማይቀር ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የኤሌትሪክ ሃይልን የሚጠይቅ ነው፡፡ እናም በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየተስተዋለ ከሚታየው ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ጋር ተያይዞ ለቀጣይነቱ የህዳሴው ግድብ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ የሚሰጠው ምላሽ ምን ያህል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህልውና ጉዳይነቱ የዜጎችንና የሀገራችንን ዕድገት በማፋጠን ብቻ የተወሰነ አይደለም—የጎረቤቶቻችንን ተጠቃሚነት በማሳደግ የሰላማችን ዋስትናም ጭምር እንጂ፡፡ እናም ግድቡ ከከፍተኛ የኤሌትሪክ ሃይል እጥረት ለሚሰቃዩት እንደ እነ ኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ለመሳሰሉ ጎረቤቶቻችን ለችግራቸው ምላሽ የሚሰጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩተን የሚያሳድግ፣ ግንኙነታችንንም የማጠናከር ሚናው በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የግድቡ ግንባታ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር ለአካባቢው ሠላምና መረጋጋት የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት በግድቡ ግንባታ ስፍራ ላይ የመሰረት ድንጋይ ካኖረበት ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ጀምሮ፤ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለ አንዳች ልዩነት ስኬታማነቱን ዕውን ለማድረግና በራሳችን ተነሳሽነት ማናቸውንም ጉዳዮች ለመከወን ቃል ገብተናል፡፡ በዚህም ሁሉም የሀገራችን ህዝብ የዘመናት ቁጭትና ብሔራዊ ሀብቱ የሆነውን የዓባይ ወንዝን የመጠቀም ምኞትና ፍላጎት በአዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት ተደርጓል፡፡

በህዝቦች የማይነጥፈና ሙሉ ተሳትፎ የሚገነባው እንዲሁም የዜጎች ሀብት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሳችን ገንዘብና ተሳትፎ የሚገነባ ብቸኛው የዓለማችን ፕሮጀክት ለመሆን በቅቷል፡፡ ዜጎች ከዕለት ምግባቸው ቀንሰው የሚገነቡትና እንደ አይናቸው ብሌን የሚንከባከቡት ግድብ መሆኑም ታሪካዊነቱ የትየሌለ ነው፡፡

የናይል ተፋሰስ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ7 ነጥብ 10 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜትር ተጨማሪ ውሃን ማስገኘት እንደሚችል ጥናቶች አረጋግጠዋል። ሁሉንም ነገር በጥርጣሬ የሚመለከቱት አንዳንድ የውጭ ፖለቲከኞች የ“ይጎዳናል” ያረጀ አስተሳሰብን በማራመድ ጉዳዩን የፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረጉት ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብም እስካሁን ድረስ የጠፋ አይመስልም። በተለይም ግብፆች አስተሳሰቡን በተለያዩ መንገዶች ሲገልፁና እንደ ናይል ተፋሰስ ዓይነት የትብብር ማዕቀፍ ደጋግመው በጥያቄነት ሲያቀርቡት እየተስተዋሉ ነው።

ዳሩ ግን ሀገራችን ከምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አኳያ ሌሎችን የመጉዳት አስተሳሰብን ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ አታራምድም። ይልቁንም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የምታምንና ይህንንም በተግባር እያረጋገጠች የምትገኝ መሆኗን በተለያዩ መድረኮች ማስመስከር ችላለች፡፡ ከዚህም መካከል የአባይ ተፋሰስ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የኢንቴቤው ስምምነት በማሳያነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ ይህን ስምምነት ከዳር ለማድረስ ከአስራ ሶስት ዓመታት በላይ መፍጀቱ ምን ያህል ጥረት እንደጠየቀ ለመረዳት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በአባይ ተፋሰስ የጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ የነበረው አስተሳሰብን መቀየሩ ብቻ የሚጠይቀውን ጥረት መገመት አይከብድምና፡፡

ያም ሆነ ይህ ግን አሁን ስድስተኛ ዓመቱን የደፈነውና ፍፃሜውም 56 በመቶ የሆነው የህዳሴ ግድብ በፍትሐዊነት ሁላችንም ተጠቃሚ የምንሆንበት ሀገራዊ አጀንዳ ነው። የሀገራችን ህዝቦች ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ከዕለት ጉርሳቸውና ከዓመት ልብሳቸው እየቀነሱ ከሚገነቡት የህዳሴ ግድብ የበለጠ ብሔራዊ አጀንዳና ኩራት ሊኖር የሚችል አይመስለኝም፡፡ በመሆኑም የግድቡን ግንባታ ከፍፃሜው ለማድረስ ላለፉት ስድስት ዓመታት ያሳየነውን ብሔራዊ ኩራትና መግባባት ሰንቀን መቀጠል ይኖርብናል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy