ፀረ ህዳሴ ኃይሎችን እንታገል ሲባል… /ወንድይራድ ኃብተየስ/
ኢትዮጵያ ከወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ተላቃ በሠላም፣ በዴሞክራሲና በልማት ጎዳና መጓዝ ከጀመረች 27 ዓመታት ሊቆጠር ነው። በእነዚሀ ዓመታት በሁሉም የአገሪቱ ክልል አንጻራዊ ሠላም ሰፍኗል ማለት ይቻላል። በሁሉም ክልሎች ቀጣይነት ያለው ፈጣን ልማት እየተረጋገጠ ይገኛል ማለት ይቻላል። እየተመዘገበ ያለው ባለሁለት አኃዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እንደሚያመላክተው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አሁን በተያዘው ሁኔታ ተጠናክሮ ከቀጠለ አገሪቱ ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ መሸጋገሯ አይቀሬ ይሆናል።
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ የዳበረች አፍሪካዊት ኃያል አገር መሆኗም እንዲሁ አይቀሬ ነው። መላ ህዝቧም በአስተማማኝ መልኩ ይበለጽጋል። ይህንን እውነታ ዛሬ ላይ ቆመው የተነበዩ አንዳንድ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች የተጀመረውን ልማት ለማደናቀፍና ሠላሟን ለማደፍረስ በየጊዜው የተለያዩ ስትራቴጂዎችን እየቀየሱ መንቀሳቀሳቸውን አላቆሙም።
የስትራቴጂዎቹ መሠረታዊ ዓላማ የአገሪቱን ልማት ማደናቀፍና ህዝቦቿን በማበጣበጥ አገሪቱን ወደማያበራ የእርስ በርስ ግጭትና ውጥረት ውስጥ መክተት ነው። ዓላማውም አገሪቱን በብጥብጥና በሁከት ማዕበል ውስጥ በመዝፈቅ ኢትዮጵያዊያንን ወደ የእርስ በርስ ግጭትና ደም መፋሰስ በማስገባት አገሪቱ የተያያዘችውን የልማት እንቅስቃሴ ማስተጓጎል ነው።
ለዚህ ማስፈፀሚያ ከሚጠቀሙባቸው ሥልቶች አንዱ የኃይማኖት አክራሪነትን ማስፋፋትና በኃይማኖት ሽፋን የሽብር ተግባራትን መፈፀም ነው። በተለይም ዜጎች እየተገደዱ ከፍላጎታቸው ውጭ ያልፈለጉትንና የማያምኑበትን እምነት እንዲቀበሉ የማድረግ ሥልት ነው።
የቅርብም ሆነ የሩቅ የኢትዮጵያ ጠላቶች የአገሪቱን ልማት ለማደናቀፍ የሚጠቀሙበት አንዱ ሥልታቸው ሲከሽፍ ሌላ በመቀየስ እንቅስቃሴያቸውን ይቀጥላሉ። አንዱ ሥልታቸው ኃይማኖትን ሽፋን አድርጎ መንቀሳቀስ ሌላው ደግሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን በመሣሪያነት መጠቀም ነው።
በውጭ ያሉ ፅንፈኛ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገ ወጥ መንገድ፣ በአመጽና በጦርነት የመናድ ግብን ይዘው እየሰሩ ያሉ ናቸው። አንዳንዶቹም ቡድኖች በአገሪቱ ሕግ መሠረት በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅትነት ለመንቀሳቀስ እውቅና አግኝተው በሽፋን የሚሰሩ ኃይሎች ናቸው። እነዚህም በአገሪቱ በተለያየ ጊዜ በፈፀሟቸው ተግባራት ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት በአሸባሪነት ሰይሟቸዋል። እዚህ ላይ ብዙዎቹ በአገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች በአገሪቱ ሕግ መሠረት የተመዘገቡና በሕጋዊ መንገድ እንቀሳቀሳለን በሚል መንግሥትና ሕዝብ የሚያውቃቸው ናቸው።
እነዚህም ፓርቲዎች በአገሪቱ በተካሄዱ የተለያዩ ምርጫዎች አጀንዳቸውን በነጻነት በማራመድ የሚሳተፉና የፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸውን ለሕዝብ በማቅረብ በሠላማዊ የፖለቲካ ውድድር ውስጥ የሚሳተፉ ናቸው። ከእነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ውጪ አንዳንዶቹ በሕጋዊነት ስም ሕገ ወጥ ተግባራትን የሚያከናውኑ መሆናቸውም የአደባባይ ሚስጥር ነው። ሲፈልጉ አመጽና ብጥብጥን በመፍጠር የአገሪቱን ሠላም ለማደፍረስ ይሰራሉ፤ ሲያሻቸው ደግሞ ምርጫ በመጣ ቁጥር ለመመረጥ ይወዳደራሉ። ከየትኛው ወገን እንደሆኑ በግልጽ የለየለት አቋም አልያዙም። የየወቅቶቹን የአየር ሁኔታ እየገመገሙ ሁለቱን ተግባራት እያፈራረቁ በግላጭ ለመሥራት የሚንቀሳቀሱ ናቸው።
መቀመጫቸውን ባህር ማዶ ያደረጉ ፅንፈኞቹ ከአገር ቤት ቢጤዎቻቸው ጋር እጅጉን የተቆራኙ ናቸው። ባህር ማዶ ተቀምጠው አገር ውስጥ ብጥብና ሁከት እንዲፈጠር የማያደርጉት ነገር የለም። የአገር ቤቶቹ ሸሪኮቻቸው ጋር በህቡዕ በመንቀሳቀስ ለጥፋትና ለሽብር ተልዕኳቸው ግንባር ፈጥረው ሲሯሯጡም ይስተዋላሉ። ከመሰሎቻቸው ጋር ጋብቻ ፈፅመው የገንዘብ፣ የሥልጠናና ሌሎች ድጋፎችን ሲጋሩም ታይተዋል። ዓላማቸው አንድና አንድ ነው። የአገርን ልማት ማደናደቀፍና የህዝባቸውን ድህነት ማባባስ፣ ነው።
ከዓለም አቀፍ አሸባሪዎችና እነሱን ከሚደግፉ መንግሥታት በሚያገኙት በዚህ ገንዘብ የአገሪቱን ሠላም ለማደፍረስማ ንጹኃን ዘጎችን ለህልፈተ ህይወት ለመዳረግ ሲንቀሳቀሱ ተንሽም ሀፍረት አይሰማቸውም። በአገራቸውና በህዝባቸው ላይ ክህደትንና ጥፋትን ሲፈጽሙም ትንሽ አይቀፋቸውም። እነሱ ምን ጉዳያቸው፤ ባህር ማዶ ሆነው ሲያሻቸው ፖለቲካንና ኃይማኖትን በማደበላለቅ በዚህች አገር ደም መፋሰስ እንዳይቆም የቻሉትን ያህል ይራወጣሉ።
የፖለቲካ ሥልጣን በህዝብ ድምጽ ከሚገኝ ካርድ መሆኑ ጠፍቷቸው ሳይሆን በአቋራጭ የመንግሥት ሥልጣንን መያዝ አቋራጭ መንገድ አድርገው መምረጥ በመፈለጋቸው ነው። ለዚህም ነው በተለይ የፖለቲካ አጀንዳን በኃይማኖት ሽፋን በመደበላለቅ አንዱን ይዘው ሌላውን ሲጥሉ እሱም ካልተሳካ ሌላ ሥልትን በመቀየስ ሁከትና ሽብር የአገሪቱ መገለጫ እንዲሆን ለመሥራት የማይቦዝኑት። በቅርብ ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ የእምነት ተቋማት ውስጥ በአማኞች መካከል የእምነቱ ተከታይ መስሎ ሰርጎ በመግባት ቀላል የማይባል የጥፋት ድርጊቶች ሲፈፀሙ ተመልክተናል።
ዓላማቸው አንድና አንድ ነው። በአገሪቱ ብጥብጥና ደም መፋሰስን መፍጠርና ሠላምን ማደፍረስ ነው። ሠላምን በማደፍረስና ሁከትን በመፍጠር በግርግር ያሰቡትን የፖለቲካ አጀንዳ ማሳካት ያስችለናል ብለውም ያምናሉ። በዚህ መልክ ካደረጓቸው እንቅስቃሴዎች አንዱ በተለያዩ ኃይማኖት አማኞች መካከል ግጭትን መፍጠር ነው።
የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹና ሽብርተኞቹ ይህንን ስትራቴጂ ሲነድፉ አንድም ህዝቡ ለኃይማኖቱ ቀናኢ በመሆኑ በኃይማኖት ስም ከተንቀሳቀስን ሊበርድ ወደማይችል ግጭትና ደም መፋሰስ እናስገባዋለን በሚል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት በኃይማኖቶች መካከል የሚፈጠረውን ግጭት ለማርገብ፣ ሥርዓት ለማስያዝ፣ ለማረጋጋትና ሠላምን ለመፍጠር ሲል ሊወስድ የሚችለውን ሕጋዊ ርምጃ በማጋነን ይኸው በኃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ገብቷል በሚል ክስ በመመሥረት በአማኞች መካከል ልዩነት የመፍጠር እድል ይኖረናል በሚል ተስፋ ነው። መለስ ብለን የዚያን ሰሞኑን ድርጊት ብንመለከት በቤተክርስቲያን ኃይማኖታዊ ተልዕኳቸውን ለመወጣት በተሰባሰቡ ምዕመናን ፊት በመሄድ የእስልምና ኃይማኖት ፀሎት በማድረግ ህዝቡ እንዲቆጣና አምርሮ በሌላ ኃይማኖት ተከታዮች ላይ እንዲነሳሳ ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። በተገላቢጦሹም እንዲሁ በመፈፀም ብዙ ርቀት ተጉዘዋል።
በዚህ መልክ ባደረጉት ሰፊ እንቅስቃሴ ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሷል። በኃይማኖት ሽፋንም በርካታ ለኃይማኖታቸው ቀናኢ የሆኑ ንጹኃን አማኞችን አሳስተዋል። እዚህ ላይ በአገር ውስጥ ያሉ አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ለችግሩ መባባስ ቀላል የማይባል ድርሻ እንደነበራቸው የሚታወስ ነው።
መቀመጫቸውን ባህር ማዶ ባሉ አገራት ያደረጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ነን ባይ አሸባሪዎች እነሱ በሞቀ ቤት ተቀምጠው ጨቅላ ወጣቶችን በገንዘብ እየደለሉ አገር ውስጥ በሕገ ወጥ ተግባር እንዲሰማሩ የማድረግ አቅጣጫን ይከተላሉ። በዚህ መልክ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ አመራር ነይ ባዮችን አስመልክተው ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ያሉት ነገር ነበር።
“አንድ ሕዝብን አስተዳድራለሁ፤ ለህዝብ ቆሚያለሁ” የሚል ፖለቲከኛ ወይም የፖለቲካ አመራር ራሱ ሊገባበት የማይፈልገውንና በራሱ እንዲደርስ የማይሻውን ምንም የማያውቁ ለጋ ወጣቶችን በገንዘብ እያታለለ መማገድ ከተጠያቂነት አያድንም፤ ሞራላዊም ህልናዊም አይደለም።” ነበር ያሉት።
እርግጥ ነው፤ ራሳቸውን ከችግር አርቀው በአገሪቱ የሚገኙ ወጣቶችን በሕገ ወጥ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ እያደረጉ ያሉ ወገኖች በሌሎች ደም መጫወት እንደሆነ በመገንዘብ መለስ ብለው ደጋግመው ቢያጤኑ የተሻለ ነበር። ይህንን በመከወን የበደሉትን ህዝብ መካስ ብሎም በተጀመረው የህዳሴ ጉዟ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ በማኖር በጎ ሚና መጫወት ቢችሉ ዛሬም እድሉን አላቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ የህዳሴ ጉዞውን ተያይዞታል። ከዚህ ማዕድ ላይ የሚያፈናቅለውን ሊቀበል ከማይችልበት ደረጃ ላይ ነውና በቸልታ የማለፍ ትዕግሥቱን የለውም – ምክሬ ነው።