Artcles

የሀገራችን ክፍለ አህጉራዊ ጥረት

By Admin

April 11, 2017

የሀገራችን ክፍለ አህጉራዊ ጥረት /ዳዊት ምትኩ/

            ኢትዮጵያ ቀጣናውን በልማት አውታሮች ለማስተሳሰር ከምታደርገው ጥረት ባሻገር የአካባቢው ሰላም እንዳይናጋ የበኩሏን ጥረት እያደረገች ነው። ይህ ተግባሯም ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዳይነጣጠሉ ያደረገ ነው ማለት ይቻላል። በአንድ በኩል በልማት እየተሳሰሩ፤ በሌላ ወገን ደግሞ ሰላምን በማምጣት ልማቱ ለዴሞክራሲው መጎልበት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ዕድል ይሰጣል።

በዚህም ፅሑፍ ሀገራችን የክፍለ አህጉሩን ሰላም በማረጋገጥ ልማትና ዴሞክራሲ እውን እንዲሆኑ በማከናወን ላይ ያለችውን ተግባር ለመጠቃቀስ ይቻላል። እንደሚታወቀው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ቀውስ የበዛበት ነው። ያለ ጦርነት ስጋት ውሎ ያደረበት ጊዜ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህ ሁኔታም የአካባቢው ሀገራት ሰላማቸውን አረጋግጠው ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማታቸውና ዴሞክራሲ ግንባታቸው እንዳያተኩሩ አድርጓል።

የኢፌዴሪ መንግስት አፍሪካውያንና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያደርግለትን የሰላም ማስከበር ጥሪ ተቀብሎ ያከናወናቸው ተግባራት እደተጠበቁ ሆነው፤ የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦችን ሰላም ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን ተወጥቷል። አንዱ በዳርፉር ሱዳን ያደረገው ነው። በሱዳን ዳርፉር ግዛት ከሌሎች ሀገሮች ጋር በመሆን ባሰማራችው ሠላም አስከባሪ ሃይልም የእርስ በርስ ግጭት እንዳይከሰት በማድረግ ላይ መሆኗም ይታወቃል። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በይገባኛል በሚከራከሩበት የአብዬ ግዛት ከዓለም ብቻውን የተሰማራ ሠላም አስከባሪ ኃይል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር በማሰማራት በዓለም- አቀፍ ደረጃ ተቀባይነቷን ያሳደገ ተግባር እያከናወነች ነው።

ሀገራችን በሁለቱም ሀገሮች መንግሥታትና ሕዝቦች ያላት አክብሮትም ከፍተኛ ነው። ሀገራችን በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ሠላም፣ ጸጥታና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ባለችው ሚና በሶማሊያ የነበረውን መንግሥት- አልባነትና አክራሪነት በመታገልም ውጤታማ መሆን ችላለች።

በተለይም የአፍሪካ ህበረትም ሆነ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚሰጣት ማናቸውም የኃላፊነት ቦታዎች በገለልተኝነት ተግባሯን በመወጣት አንቱታን ማትረፍ ችላለች። ለዚህም በአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ (አሚሶም) ጥላ ስር በመሆን የዓለም አቀፍ አሸባሪው አል-ቃዒዳ ክንፍ የሆነውን አል-ሸባብን ትርጉም ወደሌለው ደረጃ እንዲወርድ በማድረግ ቀጣናውን ከስጋት የመታደግ ስራዋን መጥቀስ ይቻላል።

በደቡብ ሱዳን የተከሰተውን ቀውስ ለመፍታትም ሀገራችን በአደራዳሪነትና ሰላም የሚያስጠብቁ ኃይሎቿን ጭምር በመላክ ወንድም የሆነውን የዚያች ሀገርን ህዝብ ሰቆቃ ለማስወገድ ችላለች፤ ስደተኞችን በመቀበል ጭምር። ተግባሯን በገለልተኝነት በመከወኗም በአፍሪካውያንም ይሁን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተቀባይነቷን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገች መጥታለች።

እርግጥ ሠላማቸው የተረጋገጠ፣ በኢኮኖሚያቸው የበለጸገና ዴሞክራሲ ያበበባቸው ጎረቤቶች የጋራ ጥቅም መሠረት መሆናቸው የማይታበይ ቢሆንም፤ ሀገራችን ከዚህ ባለፈ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች ሰላም ያለማሰለስ በመሥራት ላይ ትገኛለች። በሞሮኮና በአልጄሪያ፣ ናይጄሪያ ውስጥ የቢያፍራ የመገንጠል እንቅስቃሴን እንዲሁም በሱዳን የቤኛኛ እንቅስቃሴ ከማዕከላዊ መንግሥታት ጋር የነበራቸውን ግጭት በመፍታት ታሪካዊ አስተዋጽኦ ማበርከቷም የሚዘነጋ ሃቅ አይደለም።

ምን ይህ ብቻ። ሀገራችን እያስመዘገበችው ያለው ልማታዊ እመርታ ሌላኛው የተመራጭነቷ ምስጢር ነው ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ ያላት አህጉራዊ ትብብር ኮሜሳ በሚሰኘው በምሥራቅና የማዕከላዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ ትስሰር የተጠናከረ ውህደት ለመፍጠር ያላት ሚናም ከፍተኛ ነው።

በመሠረተ-ልማት ግንባታ መስክ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብም ጥረት እያደረገች ነው። የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግም በመሥራት ላይ ነች። ከጅቡቲ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ጋር የመንገድ ግንኙነት በመፍጠር ለጋራ ጥቅም በመትጋት ላይ ትገኛለች። ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኝ የባቡር መሥመር ግንባታው እየተገባደደ ሲሆን፤ ከኬንያ ጋር የሚያገናኘው መሥመርም ዝርጋታው ተጀምሯል።

ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ተጠቃሚ እንድትሆን ከማድረጓም በላይ፤ ኬንያንም በተመሳሳይ ሁኔታ እንድትጠቀም በመጣር ላይ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃዎች ያስረዳሉ። ሀገራችን በምትከተለው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መርህም ተቀባይነት ያላት ናት። በዚህ አስተሳሰቧም የአባይ ውኃ አጠቃቀም ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መጠቀም አስፈላጊነቱን አምናም እየሰራች ነው። የናይል የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮች የጋራ ማዕቀፍ ፈርማ ወደ ማጽደቅ ሂደት በመግባት ላይ ነች። ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት ማለት 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት በማመንጨት ዓላማዋ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ጎረቤት ሀገሮችንም መጥቀም ስለሆነ ነው።

በጐረቤት ሀገር ሱዳን የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋት እልባት ከመስጠት አኳያ የአንበሳውን ድርሻ ከተወጡት የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት። በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል የነበረውን አለመግባባት በመፍታት፣ በዳርፉርና በአብዬ የተከሰቱ ችግሮችን በመቅረፍና የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በማሰማራት ሀገራችን የተጫወተችው ሚና እጅግ የላቀ ነው።

የኢፌደሪ መንግስት በጎረቤት ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ያደረገው ጥረት የሚመነጨው ሌሎች ሃይሎች እንደሚሉት ሳይሆን የጐረቤቶቻችን ሰላም ለሀገራቸን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን መፋጠን ካለው ፋይዳ አኳያ መሆኑ ለማንም የሚሰወር አይመስለኝም። ምክንያቱም እኛ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመዋጋት የምናደርገው ትግል ሊሳካ የሚችለው ጐረቤቶቻችን ሰላም ሲሆኑ እንደሆነ ይታወቃል። እርግጥም የጎረቤቶቻችን ሰላም መሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለእኛ ሰላም መጐልበት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው።

በሀገራችን ሰላም ላይ የቅርብ ተጽዕኖ ያላት የሱዳንን ችግር ለመቅረፍ በመንግስታችን የተካሄደው ጥረት ምንጩ ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሰላሟን ዘላቂ ለማድረግ ምንጊዜም ቢሆን ወሳኙ ነገር  በውስጥ የምታካሄደው የፀረ-ድህነትና ኋላ ቀርነት ትግል ሊሳካ የሚችለው ተጋላጭነታችን ሲወገድ ብቻ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በጐረቤቶቻችን ላይ የሚያጋጥም ትርምስንና ቀውስን መፈታት ካልተቻለ ጦሱ ለእኛም መትረፉ የሚቀር አይደለም። ከዚህ አኳያ በፀጥታና በስደተኞች አማካኝነት በጋምቤላ አካባቢ በቅርቡ የተከሰቱ ችግሮችን ማስታወስ ዕውነታውን የሚያሳይ ይመስለኛል።

በደቡብ ሱዳን በኩል ጥቃት ያደረሱት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎችና ሀገራችን በስደተኝነት የተቀበለቻቸው የደቡብ ሱዳን ዜጎች የሚፈጥሯቸው አለመግባባቶች የዕውነታውን ድባብ የሚያሰፉ ናቸው። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በህዝበ-ውሳኔ ከተለያዩ በኋላ ቀጣናውን የተቀላቀለችው አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን፤ ለነፃነቷ የታገለችውን ያህል ሰለሟን ማስጠበቅ አልቻለችም። በዚያች አዲስ ሀገር ውስጥ በተቀናቃኞች መካከል በየወቅቱ እየተከሰተ ያለው ችግር ህዝቦቿ ከነፃነታቸው ማግኘት የሚገባቸውን ትሩፋቶች እንዳያጣጥሙ እንቅፋት ፈጥሯል።

ምንም እንኳን የኢፌዴሪ መንግስት ከመነሻው ጀምሮ ለደቡብ ሱዳን ሰላም መስፈን እስከ ዛሬ ድረስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ቢሆንም፤ ይህን ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ሁኔታ ላይ የሚገኝ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው በቅርቡ በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች አማካኝነት የተፈረመው የተኩስ አቁም ስምምነት ተጥሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት በመቅጠፉ ሳቢያ የአፍሪካ ህብረት ባካሄደው ጉባኤ ላይ የሰላም አስከባሪ ሃይል ድጋፍ ሰጥቷል።

በሶማሊያም ቢሆን አል-ሸባብን ለማጥፋት የሀገራችን መንግስት ከሶማሊያ የፌዴራል መንግስት ጋር አብሮ እየሰራ ነው። እርግጥ በሶማሊያ የተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት ያቺ ሀገር ከብጥብጥ ወጥታ ምርጫ እንድታካሂድ ያደረጋት ነው። ይህም በጥሩ ጎኑ የሚታይ ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ደቡብ ሱዳኖች ሁሉ በስደተኝነት የሚሰቃዩትን ሶማሊያውያኖችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እና እነዚህ ህዝቦች ራሳቸው ከሰላም ተጠቅመው ለቀጣናው ልማትና ሰላም የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ሊያደርግ ይችላል።