Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እናድጋለን ገና፤ ምኑ ተነካና

0 861

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እናድጋለን ገና፤ ምኑ ተነካና /ይነበብ ይግለጡ/

  ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገቷ ያስመዘገበቻቸው ድሎች በተጨባጭ መሬት ላይ ወርደው ይታያሉ፡፡ ወርልድ ፋይናንስ ድረገጽ የአለም ባንክን ወቅታዊ ሪፖርት ጠቅሶ “The world’s five fastest-growing economies” በሚል ርእስ ባወጣው ዘገባ እንዳመለከተው በአለማችን በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ካሉ ሀገራት ኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ተቋሙ የ200 ሃገራትን ኢኮኖሚያዊ እድገት በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን ኢትዮጵያን ቡታን ከተባለች አገር ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧል።

ኢትዮጵያ ከድኃ ሀገራት ውስጥ ስትሆን በርካታ የልማት ሜጋ ፕሮጀክቶች በመተግበር በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ ነው እድገት ልታስመዘግብ የቻለችው፡፡ የዓለም ፋይናስ ኢትዮጵያ በ8 ነጥብ 7 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገቧን በሪፖርቱ  ጠቅሶአል፡፡ ኢትዮጵያ እንደአውሮፓ አቆጣጠር ከ2004 እስከ 2014 በነበሩት ዓመታትም በሕዝብ መሰረተ ልማትና በኢንቨስትመንት ዘርፎች ፈጣን እምርታዊ ለውጥ ማሳየቷን አስታውቆአል፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሀገሪቱን ወደ ከፍተኛ እድገት ሊያስገቧት የሚችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ መሆኗንም ነው አስምሮበታል፡፡

በመሰረተ ልማት ግንባታ፤ በመንገዶች፤ በኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች፤ በተለያዩ ግድቦች ግንባታ፤ በትራንስፖርቱ ዘርፍ፤ በሆቴልና ቱሪዝም፤ በባንክና ኢንሹራንስ፤ በአየር መንገድ፤ በጤናው አገልግሎት ዘርፍ፤ በከተሞች ማደግና መስፋፋት፤ በከተማ ቀላል ባቡርና በረዥም ርቀቱ የባቡር መስመር ግንባታ ወዘተ እድገትን ያስጨበጡ ስራዎች በገዘፈ ሁኔታ ተሰርተዋል፤ በመሰራትም ላይ ናቸው፡፡

ሜጋ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት፤ የውጭ ኢንቨስትመንትን በብዛት በመሳብ ሀገር ውስጥ እንዲሰሩ በማድረግ፤ ይህም ከሚገኘው የእውቀትና የልምድ ሽግግር በተጨማሪ ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል መክፈት ችሎአል፡፡ ዘመናዊ ግብርናን በማስፋፋት፤ ድርቅን በዘላቂነት ለመመከትና ለማስወገድ ዘላቂ የሆነ የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ በመላው ሀገሪቱ፣ ብዙ ሚሊዮኖች አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን በማሳተፍ በስፋት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ለበርካታ አመታት የተሰራ ስራ በመሆኑ በየክልሎቹ ተጨባጭ ለውጥ አስመዝግቦአል፡፡

በተለይ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በግዙፍ ግድብነቱ በአፍሪካ አንደኛ በአለም ደረጃ 7ተኛ ላይ መቀመጡ፣ ያለምንም የውጭ እርዳታ በራስ አቅም መሰራቱና ለፍጻሜም መቅረቡ ሀገራችን በታላቅና ስርነቀል ኢኮኖሚያዊ ለውጥና እድገት ላይ የምትገኝ መሆንዋን ያረጋግጣል፡፡ በሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትና ለውጥ መስፈርት ሲታይ ዛሬ እጅግ የገዘፉ ለውጦች ታይተዋል፡፡ እናድጋለን ገና መቼ ተነካና እንዲሉ፡፡

የትላንትዋ ኢትዮጵያና የዛሬዋ ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማትና በኢኮኖሚ እድገት ስሌት ሲታዩ የሰማይና ምድር ያህል ርቀትና ለውጥ አላቸው፡፡ ይህ ለውጥና እድገት የተገኘው ለሀገራችን መሰረታዊ የኢኮኖሚ ችግሮች በትክክል መፍትሄ የሚሆን አዋጪ የኢኮኖሚ ቀመርና ፖሊሲ ተንድፎ ስራ ላይ በመዋሉ ነው፡፡ በመጀመሪያው አካባቢ ኢትዮጵያ የምትከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትክክለኛ አቅጣጫን የተከተለ አይደለም የሚለው የምእራባውያን ኢኮኖሚስቶች ተቃዋውሞ አይሎና ጎልቶ  ይሰማ ነበር፡፡

አይ.ኤም.ኤፍ ሆነ ወርልድ ባንክ ከሚሰጡት ብድር አንጻር ወይንም ጎን ለጎን አስገዳጅ ሁኔታዎችን ለመፍጠር፤  እኛ በምንለው የኢኮኖሚ ስሌትና ቀመር ብቻ ነው መሄድ ያለባቸሁ በማለት የማያባራ ጥረት አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ የለም እናንተ ድሕነትን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል በአጋዥነት ቆማችሁ መርዳት ማበደር ነው ያለባችሁ፤ ለኢትዮጵያ አዋጪ የሆነውን የኢኮኖሚ ልማትና እድገት እንዴት እንደሚገኝ የምናውቀው እኛ ነን የሚለው በመንግስት በኩል የተያዘው ጠንካራና ያልተፍረከረከ መስመር ነው ለተገኙት በርካታ ሀገራዊ የኢኮኖሚና የልማት ስኬቶች ዋና መሰረት የሆነው፡፡

የምእራባውያን ኒዮ ሊበራል ኃይሎች የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ የተፈጥሮ ሀብት ማእድን የፖለቲካ ሕይወት ጭምር በእነሱና በእነሱ በጎ ፈቃድና አቅጣጫ ብቻ እንዲዘወር ይሻሉ፡፡

በነጻ ኢኮኖሚ ስም ሀገርን ሀገር ያሰኙ፤ አሰኝተውም የኖሩ፣ ትውልድ በፈረቃ የገነባቸውን መንግስታዊ ተቋማትና ድርጅቶች ተሟጠው ወደ ግል ይዞታ እንዲዞር ይፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ እንደዚህ አይነቱን አግበስብስ የሆነ፡ ለሀገርና ለሕዝብ የማይጠቅም እሳቤ መመከት እንጂ መቀበል አልፈለገችም፡፡ ይህም በነሱ በኩል የጎሪጥ እንድትታይ አድርጓት ቆይቷል።

በዋነኛነት እራሳቸው ምእራባውያን ዋናውን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ክፍል ገዝተው የግላቸው አድርገው እንዲመሩት፣ እንዲያስተዳድሩትና እንዲቆጣጠሩት ይፈልጋሉ። ብሔራዊ ክልልን ተሻጋሪ የሆኑ አለምአቀፍ የንግድ ካምፓኒዎቻቸውና ኮርፖሬሽኖቻቸው በየሀገራቱ ዘልቀው በመግባት ኢኮኖሚውን እንዲቆጣጠሩት በዚህም ተረፈ ምርትን ወደየሀገራቸው ለማጋዝ ተግተው የሚሰሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ምናልባት ለዚህች ሀገር የሚተርፋት ከውጭ የሚመጣውና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የእውቀትና የልምድ ሽግግር በቀጣይ ራስዋን ችላ እንድትሰራ የሚያደርጋት ከመሆኑ ውጪ በዋነኛነት ተጠቃሚዎቹ እነሱው ናቸው፡፡

ኒዮሊበራል ኃይሎች የየሀገራቱን ጥሬ ሀብትና ዝቅተኛ ዋጋ ያለው የሰው ጉልበት በመጠቀም በሚያመርቱት ምርት እጥፍ ድርብ ተረፈ ምርት አግኝተው ምርቶቻቸውን በአለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ የተትረፈረፈ ሀብት የሚያገኙበት ገንዘባቸውን ወደ ሀገራቸው ልከው ሌሎች ስራዎችን የሚሰሩበትም ጭምር ነው፡፡ እኛ ዘንድ ያሰቡት ብዙም አልቀናቸውም እንጂ፤ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል እንዲሉ የሀገራትን ሀብት በዚህ መልኩ ነው የሚያግዙት፡፡

እኛን ብቻ ስሙ፤ በምናበድራችሁ ገንዘብ እኛ የምንላችሁን ብቻ ስሩ የሚለውን በስውር ፍላጎቶችና ጥቅሞች የታጀበ ስውር ሴራቸውን መከላከልና ለግዜውም ቢሆን በመገደብ ኢትዮጵያ በራስዋ ሀገራዊ ልማትና እድገት ያስገኝልኛል ባለችው የኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመጓዝዋ ነው ግዙፍ የኢኮኖሚ ስኬቶችና ለውጦች የተገኙት፡፡

ሀገራዊ የሆነውን የራስን የኢኮኖሚ እድገት መስመር መከተል ባይቻል ኖሮ ለዚህ ውጤት መብቃት አይታሰብም አይገመትምም ነበር፡፡ ኒዮ ሊበራሉ ኃይሉ ከራሱ ጥቅምና ትርፍ ውጪ የሚያሰላው ሌላ ነገር የለውም፡፡ በማንኪያ ሰጥቶ በአካፋ የሚወስድ ትንሽ አሳይቶ ብዙ የሚነጥቅ፤ ይህ መንገድ አልሳካለት ሲል ደግሞ ያቺ ሀገር በተፈጥሮ ሀብትዋ ተፈላጊ ከሆነች የፖለቲካ ሴራ ውስጥ በመግባት ከጀርባ ተቃዋሚዎችን በማደራጀትና በመምራት በማስታጠቅም ጭምር ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ እስከማድረግ መፈንቅለ መንግስትም እስከ ማስላትና የእኔ የሚላቸውንና የመለመላቸውን ቅጥረኞች ለስልጣን እስከ ማብቃት ድረስ ይራመዳል፡፡ ይሄ በበርካታ የአለማችን ክፍሎች በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡

በየሀገራት ውስጥ ከሚፈጠረው ቀውስና ብጥብጥ፣ ሁከትና ጦርነት ጀርባም ይሀው አደገኛ አለም አቀፋዊ የሞኖፖሊስቶች እጅና ሴራ አለበት፡፡ ለእነሱ የማይበጅ መስሎ ከታያቸው ከማጥፋት ወደኃላ አይሉም፡፡ በሀገራችን መሬት፤ ባንኮች፤ ቴሌኮሚዩኒኬሽን፤ አየር መንገድ፤ ወዘተ ወደ ግል ይዞታ መዞር አለባቸው ብለው ሰፊ ክርክር አድርገዋል፡፡ ይህ ማለት እነዚህና ሌሎችም ሀገራዊ ተቋማት በሙሉ የአንድ ሕዝብና መንግስት መገለጫ መሆናቸው ቀርቶ ወደ ግል ይዞታ ሲዞሩ በቀጥታ የውጭ ኢንቨስተሮች (የውጭ ዜጎች) ይገዙዋቸዋል፡፡ የማስተዳደሩም ስራ የነሱው ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ በውጭ ኃይሎች እጅ ከተገባ የመንግስትም ሆነ የሀገር ህልውና አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ነው።

የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት፣ ከከርሰ ምድር የሚገኘውን ጭምር እንዳሻቸው እየቆፈሩ፣ ዘመናዊ ቴክኒዮሎጂን እየተጠቀሙ ወርቁን፣ አልማዙን፣ ኮባልቱን፣ ኡራኒየሙን፣ ማግኒዥሙን ወዘተ ከልካይ በሌለበት ሁኔታ ወደ ሀገራቸው ያግዙታል፡፡ በነጻ ገበያ ስም ዘመናዊና የሰለጠነ ዘመኑን የተከተለ  የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ምዝበራ የሀገርና የሕዝብ ሀብት ዘረፋ ማለት ደሞ ይህ እንጂ ሌላ አይደለም ነው፡፡

በምእራባውኑ የነጻ ኢኮኖሚ ቀመር የሀገርና የሕዝብ ሀብት ሀገርም ሙሉ በሙሉ በውጭ ዜጎችና መልታይ ሚሊዮነርና ቢሊዮነር በሆኑ የአለማችን ጥቂት ሀብታሞች ስር ትወድቃለች ማለት ነው፡፡ይህ እንዳይሆን የኢትዮጵያ መንግስት ሰፊ መከላከል አድርጎአል፡፡

አለም አቀፍ ኢንቨስተሮች በተለያየ መስክ ቢሰማሩም ሀገራዊ ጥቅምና ሉአላዊነትን ደህንነትን በሚያስከብርና በሚያስጠብቅ መልኩ ውልና ግዴታ ውስጥ ገብተው ነው የሚሰሩት፡፡ የዛኑም ያህል ኢትዮጵያውያን ኢንቨስተሮች የበለጠ እንዲሰሩ ይበረታታሉ፡፡ ድጋፍና እገዛም ይደረግላቸዋል፡፡

በሀገራችን ውስጥ የተገኙትና የተመዘገቡት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ለውጦችና እድገቶች በቀላሉ የተገኙ ሳይሆኑ ከውጭ ኃይሎች በየግዜው ከተለያየ መልኩ የሚመጡ ጫናዎችንና ግፊቶችን ለመከላከልና ለመመከት በመኚደረግ ትግል ውስጥ በማለፍ ጭምር የተገኙ ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ የቀጠለው ሀገራዊ የኢኮኖሚ ፈጣን ለውጥና እድገት በራሳቸው በምእራቡ አለም ተቋማት ተደጋጋሚ ምስክርነት ተሰጥቶታል፡፡

አይኤምኤፍ፤ አለም ባንክ፡ የተለያዩ አለም አቀፍ በልማትና በእድገት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የታየውን ልማትና ስር ነቀል ኢኮኖሚያዊ እድገት አድንቀዋል፡፡ ለማረጋገጥም የየራሳቸውን አጣሪና መርማሪ ቡድን በየግዜው በመላክ በከተማና በገጠር የተሰሩትን መሰረተ ልማቶች፤ መንገዶች፤ የንጹህ ውሀ ተጠቃሚነትን፤ ትምህርት ቤቶችን፤ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎችን፤ የጤና አገልግሎቶችን፤ የግሉን ሴክተር የኢኮኖሚ እድገት፤ የሀገሪቱን የቱሪዝም አቅም ወዘተ በብዙ መልኩ ሲያጠኑ፣ ሲፈትሹና የራሳቸውን አስተያየት ሲሰጡ ኖረዋል፡፡

እስከ ዛሬ የተሰራውና መሬት ላይ ያለው ሀገራዊ የኢኮኖሚ ልማትና እድገት ስራ የሚታይ የሚጨበጥ በመሆኑ ሊክዱት፣ ሊያስተባብሉት አልተቻላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአለም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ቀደም ባሉ አመታትም መስክረዋል፡፡ ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት አንደኛ ከአጠቃላይ አፍሪካ አራተኛ፤ በአለም ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ካላቸው ሀገራት ውስጥ በአስረኛ ደረጃ እንደምትገኝ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

ዛሬ ደግሞ በቅርብ ቀደም ሲል የጠቀስነው ወርልድ ፋይናንስ ድረገጽ ባወጣው ደረጃ መሰረት ኢትዮጵያ በአለማችን በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት፣ በሕንድና በቻይና መካከል ከምትገኝና ቡታን ከምትባል ሀገር ቀጥላ በአለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች ሲል ገልጾአል፡፡ ይህ አለም አቀፋዊ ምስክርነት የት ላይ እንደሆንን፤ ወደየትስ እየሄድን እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡

የመጀመሪያው ታላቁ ስኬት ሀገራችን ያስቀመጠችው የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነው፡፡ ቀጥሎ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ የተዘረጋው ስልትና ተግባራዊ አፈጻጸሙ ነው፡፡ ሌላው ልማቱና እድገቱ በሕዝብ ንቅናቄና ባለቤትነት የታገዘና የተደገፈ መሆን መቻሉ ነው ለውጤት ያበቃው፡፡

እዚህ ደረጃ ለመድረስ ታላቅ ሀገራዊ ልፋትና ድካም እንደሁም መስዋእትነት ተከፍሎአል፡፡ ጽንፈኛው ተቃዋሚና አክራሪው ፖለቲከኛ ሀገራዊ ልማትና እድገት እንደማይገኝ አድርጎ ሲሰብክና ፕሮፓጋንዳ ሲነዛ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እውን አይሆንም ሲል ለግብጽ ጌቶቹ አድሮ ተሳልቆም ነበር፡፡ ግን ሁሉም በስኬት ምእራፍ ዘልቆ  አለም አቀፍ ምስክርነት እየተሰጠባቸው የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እነሆ በአለም ሁለተኛ ደረጃ የሚገኝ መሆኑን የአለም ባንክ መሰከረ፡፡

መንግስትን መቃወምና ሀገርን መቃወም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ መንግስትን መደገፍም መንቀፍም መብት ነው፡፡ ሀገር ግን ሁሌም ቋሚና ዘላቂ፤ በትውልድ ፈረቃ የምትቀጥል በመሆኑ የሀገር ልማትና እድገት ሁሉንም ዜጋ በጋራ ሊያሰልፍ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ የተገኘው ውጤት እንደሀገርና እንደ ሕዝብ የኢትዮጵያ ውጤት ነው፡፡ ሊያኮራም ይገባል፡፡ ገና ብዙ ያልተሰሩ፣ መሰራት የሚቀራቸው፣ መለወጥና ማደግ የሚገባቸው፣ መታረምና መሻሻልም የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህም ሁኖ ሀገራዊ እድገታችን እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ በትልቅ ስኬትነት ሊታይ የሚገባው ነው፡፡

ችግሮች አሉ፤ አዎን አሉ፡፡ መንግስት በይፋ አምኖ የተቀበላቸው እንዲታረሙና እንዲስተካከሉ ለመስራት ወስኖ እንቅስቃሴ እያደረገባቸው ያሉ ሰፊ ጉዳዮች አሉ፡፡ ያልተመለሱ ሊመለሱ የሚገባቸው የሕዝብ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ጠባብነት፣ ትምክሕት ዛሬም ያልተፈቱ ለመፈታት ግዜን የሚጠይቁ እየተሰራባቸው ያሉ ሀገራዊ ችግሮች፣ ፈተናዎችና አደጋዎች ናቸው፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጀውም እነዚህን ችግሮች ለመክላት በጋራ ተረባርቦ መስራቱ ብቻ ነው፡፡ ሌላ መንገድ የለም፡

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy