Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተገለለችው ሀገር

0 483

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተገለለችው ሀገር  /ታከለ አለሙ/

       የኤርትራው መንግስት ከአለም የፖለቲካ መድረክ የተገለለ፤ ከአረቡ አለም ጽንፈኞች ጋር እጅና ጓንት ሁኖ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝና አቅሙ በፈቀደ ለእስላማዊ አክራሪ ኃይሎች ጭምር ሽፋን፣ ከለላና ሙሉ እገዛም የሚያደርግ ነው፡፡ ኤርትራ ለራስዋ ዜጎች ወደ ምድር ሲኦልነት ተቀይራ በሰቆቃና በእንባ እየታጀቡ የየእለት ሕይወታቸውን የሚገፉባት፣ ነጻነታቸው ተገፎ ድምጽ አልባ የሆኑባት፣ በፍርሀትና በጭንቀት ተሸማቀው የሚኖሩባት ምድር ከሆነች ብዙ አመታት ተቆጥረዋል፡፡

ብዙ ሺህ ኤርትራውያን ወደጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል፡፡ በመሰደድም ላይ ናቸው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ የመንና ሌላም ወደ አገኙበትና ሕይወታቸውን ማትረፍ ወደሚችሉበት ሀገር በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ፈልሰው መሄዱን ተያይዘውታል፡፡ ሞትንም ጭምር ተጋፍጠውት ያልፋሉ፡፡

ኤርትራ ለራስዋም ዜጎች ታላቅ እስር ቤት የሆነችበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ ቤተሰብ  የታሰሩትን መጠየቅም ሆነ የት እንዳሉ ማወቅ አይችልም፡፡ የኑሮ ውድነቱ ከሚጠበቀውና  ከሕዝቡ አቅም በላይ ሆኖአል፡፡ ዜጎች ተቃውሞ ማሰማት ቀርቶ በምስጢር እንኳን ስለገዢው ፓርቲ መተንፈስ አይችሉም፡፡ ተቃዋሚ ናቸው ወይም ሊቃወሙ ይችላሉ ተብለው የሚጠረጠሩት የሚጠብቃቸው በከፍተኛ ክትትል ስር መዋልና ደብዛቸው መጥፋት ነው፡፡

የኤርትራ ሕዝብ በኃይልና በጠመንጃ አፈሙዝ ስር ተደፍቆ የትም አትደርስም ተብሎ የተያዘ ሕዝብ ነው፡፡ ያለውን መንግስት ምስጢራዊ መንግስት ብለው የሚጠሩት ይበዛሉ፡፡  ሕዝቡ የሚደርስበትን ስቃይ በደልና ግፍ እንግልት የሰብአዊ መብት ጥሰት መገመት ከሚቻለው በላይ መሆኑን በስደት የወጡት ሁሌም የሚናገሩት ነው።

የኤርትራ ሠራዊት አባላትም ሕይወት መራራ ነው፡፡ የደሞዝ ጭማሪም ሆነ የማእረግ እድገት የሚባል ምንም ነገር የለም፡፡ በራሱ የውስጥ ሰላም ማጣትና የሕዝብ አመጽ ስጋት ተወጥሮ የተያዘው የሻእቢያ መንግስት የራስዋ እያረረባት የሰው ታማስላለች እንደሚባለው የራሱን ሀገር መለወጥ፣ ማሳደግ፣ ማልማት ሕዝቡን በሚገባውና በሚመጥነው ደረጃ ማኖር ተስኖት ባለበት ሁኔታም በጎረቤት ሀገሮች ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ማመስና ማተራመሱን መደበኛ ስራው አድርጎ ይዞታል፡፡

ሰላም፣ ጉርብትና፣ ወዳጅነት፣ በሰላም ተከባብሮ አብሮ መኖር የሚባሉት ቋንቋዎች  በሻእቢያ መንግስት ዘንድ አይታወቁም፡፡ ከአቅሙ በላይ መንጠራራት ስለሚወድ ከየመን፣ ከጅቡቲ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ገብቶ ብዙ ቀውስ የገጠመው መንግስት ነው፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ያደረገው ጦርነት የመጨረሻ አከርካሪውን የሰበረው ስለሆነ ከዛን ወዲህ የተከተለው መንገድ የፊት ለፊት ጦርነት መግጠም ሳይሆን ከጀርባ የተለያዩ ኃይሎችን በማሰማራት ለጥፋት በማሰለፍ ማዝመት ነው፡፡

ከግብጽ ጋር ባለው የጸና ጸረ ኢትዮጵያ ቁርኝት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ነን የሚሉ ስመ ብዙ ድርጅቶችን እንዲቀፈቀፉ እያደረገ መጠለያ ወታደራዊ ካምፕ ስልጠናና ትጥቅ እየሰጠ ስምሪቱን በበላይነት እየመራ ለጥፋት ማሰማራቱን ገፍቶበታል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት የግብጽ ዋነኛ ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሶአል፡፡

በየመን ላይ የገልፉ ሀገራት በከፈቱት ጦርነት ለመበቀል ሲል የእነሱው አጋርና ተባባሪ ሁኖ የዘመተው የኤርትራ መንግስት ይህ ድርጊቱ በወደፊቱ የሀገሪቱ እጣ ፈንታና ግንኙነት ላይ  ምን ሊያስከትል እንደሚችል መገመትም ሆነ ማጤን አልቻለም፡፡

አሰብን ለገልፉ ሀገራት ማለትም ለኩዋታር፤ ለሳኡዲ አረቢያና ለኩዌት ሠራዊት የባሕርና የአየር ኃይላቸው የእግረኛ ሠራዊቱ መናሀሪያ አድርጎ የሰጠው የኤርትራው መንግሰት ዋነኛ የጥቃት ኢላማ አድርጎ ያነጣጠረው ይሄንንም ሴራ የወጠነው ኢትዮጵያን የትርምስና የሁከት ማእከል ለማድረግ በማቀድ ነው፡፡

አለም አቀፍ መረጃዎች በተለይም የምእራቡ አለም ታዋቂ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ሳኡዲአረቢያ የዋሀቢዝም አክራሪ እስላማዊ እምነትን በአለም ዙሪያ ለማስፋፋት በየአመቱ በበጀት ደረጃ በብዙ ሚሊዮን ዶላር መድባ ድጋፍ እንደምታደርግ በተለያየ ግዜ ይፋ አድርገዋል (ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ  ከአመታት በፊት ቢቢሲ ዶክመንተሪ ሰርቶበታል)፡፡ ኩዌትም ሆነች ኩዋታር ተመሳሳይ መስመር ያላቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡

ከዚህ አንጻር ሻእቢያ ከእነሱ በሚያገኘው ከፍተኛ የዶላር ድጋፍ በመታገዝ በኢትዮጵያ ውስጥ የዋሀቢ አክራሪ እስላማዊ እምነት እንዲሰርጽ፣ አሸባሪነት እንዲነግስ የስርጭት መነሻቸውን አሰብ አድርገው ምስጢራዊ እንቅስቃሴአቸውን በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ አፋር፤ እንዲሁም በምስራቅ ኢትዮጵያ ጅቡቲን በመንተራስ ለማስፋት እቅድ ነድፈው መስራታቸውን ያመለክታል፡፡

በሌላም በኩል ሻእቢያ ከግብጽ ጋር በፈጠረው ጥብቅ ቁርኝት በደቡብ ሱዳንና በሱዳን በኩል በማድረግ ሰርጎገቦችን በማሰማራት የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማሰናከል ብዙ ጥረት አድርጎአል፡፡ ነቅቶ በሚጠብቀው ሕዝብና በሰራዊታችን ሴራው ይምከን እንጂ አሁንም እንደማይተኛ ይታወቃል፡፡

የኤርትራ መንግስት በአለም አቀፍ አሸባሪነት ከተፈረጀው የሶማሊያው አክራሪ ጽንፈኛ እስላማዊ ኃይል ከሆነው አልሻባብ ጋር አብሮ የሚሰራ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክርቤት አጣሪ ቡድን ባደረገው ምርመራ ማረጋገጡ ይታወቃል፡፡ ጽንፈኛ ቡድን ከጅምሩ ጀምሮ በነዳሂር አዌይስ እስላማዊ ምክር ቤት የሚል ስም ይዞ በሚመራበት ወቅትም በኤርትራ መጠለያ ከመስጠት ጀምሮ ይረዳና ይታገዝ የነበረው በኤርትራው መንግስት ነው፡፡ ዛሬም ግንኙነቱ ቀጥሎአል፡፡

የኤርትራ መንግስት በአፍሪካ ቀንድ ለአካባቢውም ሆነ ለቀጠናው ከፍተኛ አደጋና ስጋትን የጋረጠ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ባደረገው ማጣራት ያረጋገጠው እውነት ሲሆን ዛሬም ከቀድሞው አቋሙ የተለወጠ ሁኔታ የለውም፡፡

በአለፉት አመታት የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክርቤት አጣሪ ኮሚሽን ሰፊ ማጣራቶችን አድርጎ በኤርትራ መንግስት ላይ ማእቀብ መጣሉ ይታወሳል፡፡ በሰው ዘር ላይ በሚፈፅመው ኢሰብአዊ ድርጊት በመከሰሱ በምእራቡ አለም መንግስታት ከፍተኛ መገለልና ውግዘት ደርሶበታል፡፡ ከአለም ዲፕሎማሲና ከፖሊቲካውም መድረክ የተገለለ ለአለማችን ስጋት ናቸው ከተባሉ አሸባሪ ቡድኖች ጋር ትስስርና ቁርኝት ያለው ነው፡፡

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በኤርትራ ላይ በመንግስታቱ ድርጅት የተጣለው የመጀመሪያው እቀባ ባለበት ሁኖ እንደገና ከሰሞኑ የአሜሪካ መንግስት ከሰሜን ኮርያ ጋር ባለው ምስጢራዊ ስምምነትና ግንኙነት ወታደራዊ የጦር መሳሪያዎችን በአውሮፕላን ከሰሜን ኮርያ በመጫን ቻይናን አቋርጦ ወደ አስመራ ሲያመራ የተደረሰበት በመሆኑ አሜሪካ ከኤርትራ ባሕር ኃይል ጋር ያላትን ግንኙነት በማቋረጥ በኤርትራ ላይ አዲስ ማእቀብ ጥላለች፡፡

ከአጠቃላይ አካባቢዊና አህጉራዊ እንዲሁም አለምአቀፋዊ ሁኔታዎች አንጻር ሲፈተሽ በተለይም ከአክራሪ እስላማዊ አሸባሪ ኃይሎች ጋር ባለው ከፍተኛ ትስስር ለቀጠናውም ሰላም አደገኛ በመሆኑ የመንግስታቱ ድርት ቀደም ሲል  በኤርትራ ላይ የጣለው ማእቀብ ተመልሶ እንደሚጸና ሰፊ ግምቶች አሉ፡፡

ግራና ቀኙን ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የኤርትራ መንግስት እንደተለመደው እጄ ንጹሕ ነው በሚል ለማስተባበል ሞክሮአል፡፡ ለምን እቀባ ተጣለብኝ በሚል የአሜሪካን መንግስትንም በሰጠው መግለጫ ወርፎአል፡፡ ከወዳጆቹ አረቦች በስተቀር ሰሚና አድማጭ የለውም፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ ዛሬም ከመስራት አልታቀበም፡፡ ይህ የሻእቢያ መንግስት ጸረ ሰላምና አሸባሪ ድርጊት እስከምን ድረስ ሊዘልቅና ሊራመድ ይችላል? የሚለው ጥያቄ አነጋገሪነቱ ቀጥሎአል፡፡ መልሱን የሚሰጠው ግዜ ብቻ ይሆናል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy