Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለ“ሂዮማን ራይትስ ዎች” የህግ የበላይነት ምኑ ነው?

0 292

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለ“ሂዮማን ራይትስ ዎች” የህግ የበላይነት ምኑ ነው? /ዘአማን በላይ/

            አገራችን ውስጥ ማናቸውም ህጎች የሚወጡት ህዝቡ አምኖና ፈቅዶ እንደራሴ እንዲሆኑለት በሾማቸው ግለሰቦች በሚገኙበት የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ወይም በፓርላማ አማካኝነት ነው። የፓርላማው አባላት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረበላቸውን ህግ በመመርመር ይሁንታቸውን ይቸራሉ አሊያም እንዲሻሻል ወይም እንዳይፀጸድቅ ያደርጋሉ። ይህን በመከወንም ህዝቡ የሰጣቸውን ሙሉ ውክልና ገቢራዊ ያደርጋሉ።

ከዚህ ውጭ የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ኒዩ ሊበራል ሃይሎች በሀገራችን የህግ አወጣጥ ሥርዓት ውስጥ ጣልቃ የመግባት አንዳችም መብት የላቸውም። ህጉን ተከትሎም በሚከናወኑ ጉዳዩች ውስጥ ጣልቃ እየገቡ የመፈትፈት ሞራልም ሊኖራቸው አይችልም። ሆኖም ፅንፈኛ ኒዮ ሊበራል ሃይሎች በተደጋጋሚ በሚያወጧቸው ሪፖርቶች ይህን የህዝብን ሉዓላዊ የስልጣን መብት ጭምር የሚጋፉ ናቸው። ርግጥ መንግሥት የሚያከናወነው ምንም ነገር የማይዋጥላቸው በርካታ አክራሪ ኒዩ ሊበራል ሃይሎች ቢኖሩም፤ በዚህ ፅሑፌ በዋነኛነት ሁሌም ከሀገራችን ራስ ላይ የማይጠፋውና በሰብዓዊ መብት ስም የሚነግደው “ሂዩማን ራይትስ ዎች”ን ብቻ በማሳያነት በማቅረብ የአክራሪ ኒዮ ሊበራሎቹ ትክክለኛ ፍላጎት ምን እንደሆነ ለማጋለጥ እሞክራለሁ።

“ሂዮማን ራይትስ ዎች” የተሰኘው አክራሪ ኒዮ-ሊበራል ተቋም ታሪካዊ ዳራ ቢጤን ፀረ ኢትዮጵያዊነት ምግባሩ የሚበዛ ይመስለኛል። ይህ ርዕዩተ-ዓለማዊ መነሻ ያለው እኩይ ምግባሩ ህልቆ መሳፍርት ነው ቢባል ከእውነታው መራቅ አይሆንም። ተቋሙ በተለያዩ ጊዜያት በሚያወጣቸው ግልብ ዘገባዎች የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብ መልካም ገፅታዎች ለማጠልሸት ያላደረገውን ነገር ፈልጎ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ደግሞ ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ የሚያወጣ ይመስል፤ እዚህ አገር ውስጥ አንድ ድርጊት ሲከናወን የማያልቁ ወረቀቶቹንና ብዕሩን ይዞ ብቅ ማለትን የዘወትር ተግባር አድርጎታል።

ሆኖም ድብቅ አጀንዳውና ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልፅ እየሆነ በመሄዱ የዘወትር ከንቱ ዳዊቱን አድምጦ ከጎኑ የሚቆም ሀገር ወዳድ ዜጋም ይሁን የዓለም አቀፍ ማህብረሰብ አልተገኘም። በለስ አልቀናውም ማለት ይቻላል። ከፖለቲካ መስመሩ ውጭ የሆኑ ታዳጊ አገራትን የሚያወግዝበት ሪፖርቱ እምብዛም ተቀባይነት የለውም። ይህ ደግሞ ያበሳጨዋል። ብስጭቱንም ለመወጣት ቀደም ሲል በየሶስትና በየሁለት ወሩ ያወጣ የነበረውን የሐሰት ሪፖርት ፍጥነቱን በመጨመር በየሳምንቱ ካደረገው ሰነባብቷል። በተለምዶ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው ቦታ ሲደረመስ ሁኔታውን እንኳን ሳያጣራ በማግስት ተሽቀዳድሞ ለቆሻሻው ክምር መደርመስ በምክንያትነት መንገስትን መጥቀሱ የተቋሙ ዓላማ በጥላቻ ላይ ተመስርቶ ማጥላላት መሆኑን ብዙዎችን ያስደመመ ገዳይ ሆኖ አልፏል።

ርግጥ የተቋሙ ሰለባ ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም። ለአጀንዳው ምቹ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መደላድሎችን ለመፍጠር ፈቃደኛ ያልሆኑ የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ ታዳጊ ሀገራት ሁሉ ከሰርክ የጥፋት ዘመቻው አልዳኑም። ሆኖም ይህ አክራሪ ተቋም ፀረ ኢትዮጵያ ሰብካውን የመጥኝ ያለው ያለ ምክንያት አይደለም— እንጀራው በመሆኑ እንጂ። ምንያቱም በሚሊዮን የሚቆጠር ረብጣ ዶላር የሚቆርጥለት በሰራው ልክ ተተምኖ ስለሆነ ነው።

እናም የኒዮ ሊበራሊዝም አስተሳሰብን የማይቀበሉ አሊያም የርዕዮተ ዓለሙ አቀንቃኞች ያስቀደዱላቸውን የፖለቲካዊ- ኢኮኖሚ ጥብቆ ለማጥለቅ ፈቃደኛ ያልሆኑ ታዳጊ ሀገራትን በሰብዓዊ መብት ጥሰት ስም ተጠልሎ ሲያወግዝና ከለጋሽ ሀገራት ጋር ያላቸውን ወዳጅነት የሚያጠለሹ ብዕርና “ሆድ ወለድ” ዘገባዎችን ሲያጧጥፍ ይህን ተግባር እንዲከውን ያሰማሩት የሊበራሊዝም አቀንቃኞች እጃቸውን ኪሳቸው ውስጥ ይከቱለታል። ይህን ለማግኘት ደግሞ ቢሳካለትም ባይሳካለትም የውሸት ዘገባዎችን መወሽከት ስራዬ ብሎ ተያይዞታል—ግምት ላይ የጣለው ተግባር ቢሆንም።

እንደሚታወቀው ታዳጊ ሀገራት ያልተነካ ግዙፍ ሀብት ባለቤቶች ናቸው። ርካሽ የሰው ጉልበትና ያልተበላ ድንግል መሬትም አላቸው። የተፈጥሮ ሃብትና ማዕድኖቻቸውም የሚያስጎመዡ ናቸው። እናም ይህን የተትፈረፈ ሃብት ለመቀራመት ብቸኛውና ምቹው አማራጭ ለዘመኑ እንደማይበጅ በተፈጠረባቸው አገራት ጭምር ሰላማዊ ሰልፍ የተወጣበት የኒዮ ሊበራሊዝም ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ ርዕዮቱ በራሳቸው ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ፍልስፍና በማደግ ላይ የሚገኙትን እንደ ኢትዮጵያ፣ ህንድንና ቻይናን የመሳሰሉ አገራትን በራሳቸው መንገድ የማደግ ክህሎትን ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለም።

ይህም አገራቱ እንደ “ሂዮማን ራይትስ ዎች”ን ከመሳሰሉ የርዕዮተ ዓለሙ አቀንቃኞች ጋር ሆድና ጀርባ እዲሆኑ አድርጓቸዋል። እናም ነገሩ “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” እንዲሉት በመሆኑ፤ ግዙፉን ሃብታቸውን ላለማስመዝበር ‘አሜን’ ብለው ባለማጎብደዳቸው ከፅንሰ ሃሳቡ መስራቾችና ከባለረብጣዎቹ እንዲሁም ከተላላኪዎቻቸው ጋር አይግባቡም፤ ሊግባቡም አይችሉም። በመሆኑም የርዕዩተ ዓለሙ አራማጆች በውኃ ቀጠነ ሰበብ ክስ ታዳጊ ሀገራትን በሪፖርት ያብጠለጥላሉ፤ አንገት ለማስደፋትና ለመማረክ ይደክማሉ። ከመሬት ተነስተው ያለ ምክንያት ይከሷቸዋል። በሐሰት የሪፖርት ውርጅብኝ ትክክለኛ ሚዛናቸውን ሊያስቷቸው ይሞክራሉ።

ምን ይህ ብቻ። ከዓለም አቀፍ ማህብረሰብና ከለጋሽ ድርጅት ጋር ያላቸውን ቅርርብ በማበላሸትም የብድርና የዕርዳታ ድጋፍም እንዲያቋርጠባቸው ጠዋት ማታ ይወተውታሉ። ይህ አሳዛኝ ትዕይንታቸው ድሮም ዘንድሮም ምናልባትም ወደፊት ከትውልድ ጋር አብሮ የሚዝለቅ በሰው ልጆች ላይ የሚደረግ የቼዝ ጨዋታ ሊሆን ይችላል- የሰው – ለሰው- በሰው ‘ጨዋታ’፡፡ ይህ ማለት ግን ጨዋታው ቀጥተኛ ነው እያልኩ አይደለም— ስውር እንጂ። እነ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ነን ባዩቹ ዙሪያ ጥምጥም የሚጫወቱት ድብብቆሽ ነው።

ይህን ጨዋታ ለመከወንም የኒዮ- ሊበራሊዝም አቀንቃኞች በሰብዓዊ መብት ስም ባቋቋሙትና ቀለብ ሰፍረው ወደ ምድረ-አፍሪካና ላቲን አሜሪካ በሚያሰማሯቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተብዬዎች ዓይነት አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓቾች አማካኝነት የተቀለመዱ ጉንጭ አልፋ ክሳቸውን ያዥጎደጉዳሉ። ማን እንደመደባቸው ባይታወቅም፤ ራሳቸውን የአፍሪካ ጉዳዩች፣ የምስራቅ ወይም የምዕራብ አፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ እያሉ በመሰየም በየአቅጣጫው ይሯሯጣሉ።

እነዚህ የርዕዩተ ዓለም ምንደኞች በማደግ ላይ ያሉ አገራት የእኩይ ደቀ መዝሙሮች ናቸው— የማይከተሏቸው የመጨረሻው ዘመን የሐሰት ነቢያን። በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት በአገራት የውስጥ ጉዳይ በድፍረት በመግባት “ይህን ህግ አውጡ፣ ያኛው ደግሞ ሰብዓዊ መብትን ስለሚያፍን ሰርዙት” እስከማለት የሚደርሱ አስገራሚዎች ናቸው። እነርሱ እንደሚያከናውኑት ስራ ሁሉም ነገር ሸፍጥ የሚመስላቸው የርዕዩተ ዓለም አራማጆቹ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አማካኝነት የሚወጡት ህጎች ሁሉ፤ በሰላማዊ መንገድ የሚቃወሙትን አፍ ለማዘጋት ተብለው የሚዘጋጁ ይመስላቸዋል። በተለይም የሀገራችንን ሰላም በማስጠበቅ ልማትን ያለ ስጋት ለማፋጠን እንዲያግዝ የወጣውን የፀረ-ሽብርተኝነት ህግን ሲሰሙ በሪፖርት ቅብብሎሽ ጋጋታ “ሰብዓዊ መብት ተጣሰ” በማለት ከጎሬያቸው ወጥተው ለዚሁ ተግባር የተቋቋሙትን የራሳቸውን ሚዲያንና የፅንፈኛና የአሸባሪዎች ልሳኖችን ያጥለቀልቃሉ።  

ዳሩ ግን ሃቁ ወዲህ ነው። የፀረ ሽብርተኝነት ህግ ማውጣትና ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ የዜጎችን መብት ከማፈን ጋር የሚያስተሳስረው አንዳችም ነገር የለም። የኢፌዴሪ መንግስት እንደ ማንኛውም አገር ከራሱ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ልዩ ልዩ አዋጆችንና ህጎችን የማርቀቅና ወደ ስራ የመተርጎም መብትም ሆነ ግዴታ አለበት።

መንግስት የነባራዊው ዓለም ተጋሪ በመሆኑ አዳዲስ የህግ ማዕቀፎችን ማውጣቱና በስራ ላይ ማዋሉ ማንንም ሊደንቅ አይገባም። ከዚህ ጋር ተያይዞ የወጣው የፀረ ሽብር ህጉ ዜጎችን ከማንኛውም የፕሬስ እንቅስቃሴ የሚገታና ሰብዓዊ መብትን የሚያፍን ነው የሚለው የአክራሪ ኒዩ ሊበራል ሃይሎች ሰበካ በፍጹም ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። አይኖረውምም። ምክንያቱም በህግ ገደብ እስካልተጣለባቸው ድረስ አሁንም እንዳሻቸው የሚፅፉና የሚናገሩ እንዲሁም ህግና ሥርዓትን ተከትለው ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉ አያሌ ዜጎች በመኖራቸው ነው። የዚህ ፅሑፍ አጀንዳ ባለመሆኑ እንጂ ከዚህ አኳያ በርካታ አብነቶችን መጠቃቀስ ይቻል ነበር።

የዚህን ፅሑፍ አቅራቢ ሁሌም ሳስበው ግርም የሚለኝ ጉዳይ፤ በአንድ ወቅት ራሱን “ሂዩማን ራይትስ ዎች” እያለ የሚጠራው አክራሪ ኒዩ ሊበራል ተቋም መንግስትን ከማብጠልጠሉ በዘለለ፤ በህዝብ የስልጣን ሉዓላዊነት ጣልቃ ገብቶ “…የኢትዮጵያ መንግስት የፀረ ሽብር ህጉን እንደገና ሊያሻሽለውና ፖለቲካዊ ተነሳሽነት ያላቸውን ክሶች ከማቅረብ ሊቆጠብ ይገባዋል” በማለት ማስፈራሪያ ይሁን ምክር ቢጤ ያልለየለት ሪፖርት ማውጣቱ ነው። እናም ያኔ ‘አክራሪው ተቋም እያስጠነቀቀ ያለው የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤትን ነው ወይስ የኢትዮጵያ ህዝብን?’ ስል ራሴን ጠይቄያለሁ። በድፍረቱም ተደንቄያለሁ።

ዳሩ ግን አሁን ላይ ሳስበው ይህ ተግባሩ የሁል ጊዜ ዘፈኑ በመሆኑ አይደንቀኝም—ከማውራት ውጪ አንድ ርምጃም ወደፊት ሄዶ አይቼው አላውቅምና። ርግጥ በአገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት የበለጠ ወንጀል የለም— አክራሪው የፖለቲካ ተቋም የራሱ ጥፋት ስለሚጋረድበት እንጂ። የህግ የበላይነትን በጠራራ ፀሐይ መጋፋትም ጭምር ነው። እናም ለ“ሂዮማን ራይትስ ዎች” የህግ የበላይነት ምኑ ነው? በማለት እጠይቃለሁ።

ሆኖም ህግን የማያውቅ ስለ ህግ የበላይነት ሊናገር አይችልም። በሰው አገር ጉዳይ በገሃድ ጣልቃ በመግባት ቀንጀል የመፈፅም አክራሪ ተቋም ስለ ህግ የበላይነት የሚናገርበት አንደበት አይኖረውም። ሲጀመር ተቋሙ ስለተከፈለው ብቻ “በዳቦ” አምላኪነት የህዝቦችን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት ሊጋፋ ባልከጀለ ነበር። የአገር ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ በአግባቡ እንዲካሄዱ እንደ ማንኛውም አገር ኢትዮጵያ ያወጣችውን የፀረ-ሽብርተኝነት ህግን በግድ ከሰብዓዊ መብት ጋር አጣብቆ ሊሰፋው ባልሞከረ ነበር። ያም ሆነ ይህ ግን የህግ የበላይነት ለርዕዩተ ዓለም አራማጁ ተቋም የእንጀራ ጉዳይ እንጂ፤ ትክክለኛ አተገባበሩ ምንም ዓይነት ስሜት አይሰጠውም። እናም ተግባሩ ሁሉ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” የሚሉት ዓይነት መሆኑን እርሱም ቢሆን የሚያጣው አይመስለኝም። የሰው-ለሰው- በሰው እኩይ ‘ጨዋታው’ በእንዲህ ዓይነት አሳፋሪና ህገ ወጥ ተግባሮቹ የተሞላ ነውና።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy