Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለተጠናከረ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ

0 712

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለተጠናከረ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ…

አባ መላኩ

የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር አቀማመጥ ከምድር ወገብ በስተሰሜን ከሦስት ዲግሪ እስከ 18 ዲግሪ ላቲትዮድ እና በስተምሥራቅ ከ33 ዲግሪ እስከ 48 ዲግሪ ሎንግትዩድ ክልል ውስጥ ስለሚገኝ ዓመቱን ሙሉ የፀሀይ ኃይል ማግኘት ያስችላል፡፡ በመሆኑም በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ይህን ሀብት ለመጠቀም የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ይህም ሁኔታ አገሪቱ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ሥልትን ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላታል።  

የመሠረተ ልማቶች ዳርቻዎችን ሥነ ህይወታዊ እና ፊዚካላዊ የአካባቢ መንከባከቢያ ዘዴዎችን በመጠቀም የአገልግሎት ጊዜያቸውን ማራዘሚያ ቴክኖሎጂዎችን መገልገል ሌላኛው የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ ከሚያስችሉ ዘዴዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው እፀዋቶችን በመትከልና የተለያዩ ፊዚካላዊ የውኃና የአፈር መጠበቂያ ስትራክቸሮችን በመሥራት የኃይል ማመንጫ እና የመስኖ ግድቦችን ከደለል ብሎም መንገዶችን ከመንሸራተት ለመከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ በተለይም በመላው አገሪቱ የሚገኘው አርሶ አደር በየተፋሰሱ የሚገኙ ወንዞችን እየተንከባከበ የተለያዩ እርከኖችን በመሥራት ላይ ይገኛል።  

እርግጥ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሁኔታዎች ተለውጠዋል፡፡ በመንግሥት አስተባባሪነትና በኅብረተሰቡ ሙሉ ተሳትፎ በመላ አገሪቱ ለተከታታይ ዓመታት በተካሄዱ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች ቀደም ሲል የተራቆቱ አካባቢዎች በእፀዋት እየተሸፈኑ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አካባቢዎች መልሰው እያገገሙ ነው፡፡ የደረቁ ምንጮች እንደገና መፍለቅ ጀምረዋል፡፡

የአፈር መሸርሸር በእጅጉ ቀንሷል፡፡ የወንዞች የውኃ መጠን ጨምሯል፡፡ የዛፍና የደን ሽፋን ዕድገት አሳይቷል፡፡ መስኖን የመጠቀም ዕድልም ፈጥሯል፡፡ እየተከናወነ የሚገኘው የእርከን ሥራ አፈር እንዳይሸረሸር በማድረግ በወንዞች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ደለሎችን በመቀነስ እመርታ አሳይቷል፡፡

በመሆኑም በያዝነው ዓመት በመላ አገሪቱ ሊባል በሚችል ደረጃ መጠነ ሰፊ የሆነ የአካባቢ እና የተፈጥሮ ጥበቃ ሥራ በኅብረተሰቡ ተከናውኗል፡፡ በሌላ በኩልም የጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ከሌሎች ቴክኖሎጂዎች ጋር እንደ አማራጭ የሚወሰደው ሌላኛው ከሸንኮራ አገዳ ታዳሽ የኃይል አማራጭን (ኢታኖልን) የማምረት ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ከግብርና መርህ ወደ ኢንዱስትሪው መርህ ለመሸጋገር መሠረት መጣል ነው፡፡ ይህን ትልም ለማሳካትም በስኳር ምርት ከፍተኛ የሆነ ምርታማነትን እንደሚያስገኙ በሚታመኑ የአገሪቱ ስድስት ክልሎች ሰፊ እርሻ መሬቶችን በመጠቀም የስኳር አገዳ ማምረት ነው፡፡ ምንም እንኳን በሚፈለገው ደረጃ መጓተቶች ተፈጥረው ምርቱን ማዘጋት ባይቻልም።

ከዚህ መጠነ ሰፊ የሆነ ምርት የሚወጣውን ተረፈ ምርት ለኃይል ፍጆታ ማዋል በተወሰነ ደረጃ ተጀምሯል፡፡ አካባቢን ሊበክል የሚችለው ተረፈ ምርት ለኃይል ፍጆታ መዋሉ፤ ለኅብረተሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታን አስገኝቷል፡፡ ቴክኖሎጂው ምንም ዓይነት ጪስ አልባ ስለሆነ የጤና መታወክ እና ተዛማጅ አደጋዎችን አያስከትልም። ይህም ተወዳጅነቱን ይበልጥ ከፍ አድርጎታል፡፡

በሌላ በኩልም በአካባቢ ጥበቃ በሁለት በኩል ጥቅም ሊያመጡ የሚችሉ ተክሎችን ወደ አገሪቱ አምጥቶ በማስተዋወቅ ሰፊ ሥራ ተከናውኗል፡፡ ለአብነት ያህልም የጃትፎ ተክል ፍሬን በመጭመቅ በታዳሽ ኃይል አማራጭነት ባዮ ዲዝልን ለኅብረተሰቡ የኢነርጂ ምንጭ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ተረፈ ምርቱንም ለሣሙና፣ ለማዳበሪያና ለመድኃኒት መሥሪያ ለማዋል የሚያስችል ቴክኖሎጂን በመጠቀም አመርቂ ውጤት ለማግኘት ተችሏል፡፡ የጃትፎ ተክልን በአገሪቱ በመጠቀም የእፀዋት ሽፋንን በመጨመር የአፈር መሸርሸር ይቀንሳል፡፡ ከጥቅም ውጪ የሆኑ መሬቶችና ቦረቦሮች መልሰው እንዲያገግሙም ያደርጋል፡፡ ሙቀት አማቂ በካይ ጋዝ ልቀት ቅነሳ ላይ አስተዋጽኦ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከል ሥራን በመደገፍ የላቀ አስተዋጽኦም በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን የማምረት እና ጥቅም ላይ የማዋል ሥራን በማከናወን የአገሪቱ አርሶ አደር ተጠቃሚ እየሆነ ነው፡፡ የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በማምረት እና ወደ ኅብረተሰቡ እንዲደርሱ በማድረግ የማገዶ አጠቃቀምን ከ50 በመቶ በላይ በመቀነስ የደን መጨፍጨፍን ለመከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምም ተችሏል፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ ለዓለማችን የአየር ብክለት ሰፊውን ድርሻ ይወስዳሉ ተብለው በበርካታ ምሁራን የሚነሳው ከኢንዱስትሪ የሚለቀቁ ጋዞች እና የኢንዱስትሪ ፍሳሾች ናቸው፡፡ ይህንን ለመከላከል አገሪቱም የኢንዱስትሪ ፍሳሽን በሥነ ህይወታዊ ዘዴ በማከም ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

በዚህም ፋብሪካዎች በሚገኙበት አካባቢ ፍሳሹ በሚለቀቅበት የታችኛው ክፍል በሚኖሩ ሰዎች እና እንስሳቶች ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጤና ቀውስ ለመፍታት ተችሏል፡፡ ለዚህም ነው በአብዛኛው ፋብሪካዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ከሚኖሩ ህዝቦች ጋር መልካም ግንኙነት ሲፈጥሩ የሚታዩት፡፡ ከዚህ ባሻገርም ይህ ክንዋኔ የወራጅ እና የከርሰ ምድር ውኃ እንዲሁም የአፈር ብክለትን በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

እርግጥ ነው፤ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች እና መልካም ተሞክሮዎች ከተለያዩ የአገሪቱ የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ህጎች እና ደንቦች ጋር ተጣጥሞ ከተቀየሰው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ሥልት ጋር የሚጣጣሙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት ከ2017 ዓ.ም በፊት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት አንዷ ለመሆን በመነሳት መጠነ ሰፊ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች፡፡ ለዚህም ነው መንግሥትም ሆነ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች በቀጣዮቹ ዓመታት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በሙሉ በፍጥነት ከሚያድጉት አገራት አንዱ ሆኖ እንደሚቀጥል በተደጋጋሚ እየገለፁ የሚገኙት፡፡

በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱም ይህን ዕድገት ለማምጣት የግብርና ምርት መጨመር፣ የኢንዱስትሪ መሠረትን ማጠናከር እና የውጭ ገበያን ማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

በመሆኑም አገሪቱ ኃላፊነት የሚሰማት በመሆኗ በመልማት ላይ ያሉ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥን የመመከት ወሣኝ ሚና እንዳላቸው ትገነዘባለች። በዚህም ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ገንቢ ሚና በመጫወት ላይ ናት፡፡ ለዚህም ማሣያ እንዲሆን ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በኮፐን ሀገን ያደረጉትን ድርድር መጥቀስ  ይቻላል፡፡ ይህም በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ አገሪቱ ግንባር ቀደም መሆኗንና በዘላቂ የዕድገት አቅጣጫ ለመጓዝ ያላትን ዕድልና ጠንካራ እምነት የሚያመላክት ነው፡፡

እርግጥ በካርቦንና አላቂ የኃይል ምንጮች ላይ የተመሠረተ ዕድገት በአየር ንብረት ለውጥ መስክ ከሚያስከትለው ችግር ባሻገር መጨረሻው ተንገራግጮ መቆም መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ ይህን ሀቅ ታሳቢ በማድረግ የልማት አቅጣጫዋን በአዲስና በታዳሽ ኃይል ምንጭ ላይ መመሥረት እንዳለበት ወስና ሥራ ላይ አውላዋለች፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል እምቅ አቅም ያላት ስለሆነ የአረንጓዴ ልማትን እንድትከተል ምክንያት ሆኗታል፡፡ ይህም የአገሪቱን ገጽታ በመገንባት ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም በልማት ዕቅዱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2025 ኢትዮጵያ ትርፍ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ የማትለቅበት ደረጃ ላይ የመድረስ ግብ ሰንቃ ሰፊ ለውጥ እያመጣች ነው፡፡ ታዲያ ይህ ግብ በአይቀሬው የአየር ንብረት ለውጥ ሣቢያ ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ የሚያስችል ይዘት ያለው መሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡፡

እንደሚታወቀው የዜሮ ልቀት ግቡ በሦስት ዋና ዋና ስትራቴጂዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ ኃይልን ከታዳሽ ምንጮች በሰፊው በማምረት ለአገሪቱ ከሚያስፈልገው ኃይል ውጭ ያለውን ለጎረቤት አገሮች መሸጥ ነው፡፡ አገሪቱ ሰፊ የኃይድሮ ፓወር እምቅ አቅም ስላላት የኤሌክትሪክ ኃይልን በዋናነት ከውኃ ሀብት ለማመንጨት ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

በዚህም የኃይል አጠቃቀም ሥርዓቱን ኃይል ቆጣቢ ለማድረግ የማስተሳሰሪያና ማከፋፊያ መስመሮች እየተዘረጉ ይገኛሉ፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለትራንስፖርት (ለባቡር) ጭምር የምንጠቀምበት ሥልትም በጅምር ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ሂደት ምንም ካርቦንዳይ አክሳይድ በማይለቅ አኳኋን የኤሌክትሪክ ኃይልን በሰፊው ለማመንጨት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ተግባር ከአረንጓዴነቱ ባሻገር ያለንን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ከውጭ የሚገባውን ውድ ነዳጅ ለማስቀረት ከፍተኛ ዕገዛ ያደርጋል፡፡

ሁለተኛው ስትራቴጂ ደግሞ ነዳጅን ከእፀዋት ማምረት ነው፡፡ በዚህም ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገሪቱ ለማስገባት ጥሩ ውጤት እየታየባቸው ነው፡፡ ሦስተኛው ካርቦንን ከአየር የመምጠጥ አቅምን በከፍተኛ መጠን መጨመር ነው፡፡ ምንም እንኳ የአገሪቱ የኢነርጂ ምንጭ በሂደት ሙሉ በሙሉ ከታዳሽ ምንጮች እንደሚሆን ግልፅ ቢሆንም እስከዚያው ድረስ ግን አላቂ የሆኑ የኃይል ምንጮችን መጠቀም የግድ ይላል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች እንደ ድንጋይ ከሰል ያሉ ኃይሎችን መጠቀም አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜም መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም የተለቀቀውን ካርቦን ዜሮ ለማድረግና ከአየር መልሶ መምጠጥ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ደረጃም የደን ተክልን በማስፋፋትና በመንከባከብ ካርቦንን በሰፊው የሚመጥ አቅም የመፍጠር አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በየአካባቢው የሚኖሩ ሰዎችም ይህን በመረዳት የአካባቢን የጋዝ ልቀት ከመቆጣጠር ባሻገር ደኖችን በመጠቀም የንብ ማነብ ሥራ ላይ ተሰማርተው በግብርና ከሚያገኙት ገቢ ተጨማሪ እያገኙ ነው፡፡ ለእንስሳት መኖ ፍለጋም ሩቅ ቦታ ሳይንከራተቱ በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታም በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በግብርናው ልማት ዘርፍ እየታዩ ላሉ ለውጦች በምክንያት ይጠቀሳል፡፡

እርግጥም አርሶ አደሩ ዛሬ በማሣው አጠገብ እየፈለቁ ያሉትን ወንዞች፣ ሐይቆችንና ኩሬዎችን እየጠለፈ በመስኖ ማልማት ጀምሯል፡፡ እስካሁን ድረስ በአገሪቱ የተካሄዱት የተፈጥሮ እንክብካቤና የደን ልማት ሥራዎችም እያስገኙ ያሉትን ተጨባጭ ውጤቶች እያዩ ያሉት ህዝብና መንግሥት አሁንም የተጠናከሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy