Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ልማት ለሠላም!

0 440

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ልማት ለሠላም!/ኢብሳ ነመራ/

በያዝነው ዓመት በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ከልሎች አዋሣኝ አካባቢዎች በተለይ በቦረና እና በምሥራቅ ሃረርጌ ዜኖች የተወሰኑ ቀበሌዎች በወሰን አለመግባባት ግጭቶች ተቀስቅስቅሰው መቆየታቸው ይታወቃል። የወሰን አለመግባት ያጋጠመው በተለይ በ1997 ዓ.ም ህዝበ ውሳኔ ተካሂዶባቸው በህዝበ ውሳኔው መሠረት የማካለል ሥራ ባልተከናወነባቸው አካባቢዎች ነው። በዚህ ግጭት ከሁለቱም ክልሎች የንጹሃን ሰዎች ህይወት አልፏል። ሰላማዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተሰተጓጉለዋል።

ለወራት የቆየው ይህ ግጭት አሁን እልባት ተበጅቶለታል። የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት በደረሱበት ስምምነት ነው እልባት የተበጀለት። የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ሚያዚያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም በ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ተስማምተዋል። የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድር በፈረሙት በዚህ ስምምነት መሠረት፣ ህዝበ ውሳኔውን መሠረት በማድረግ የአስተዳደር ወሰን ያልተካለለባቸው አካባቢዎችን እንዲካለሉ ይደረጋል። በስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ካሣ ተክለብርሀን፣ የስምምነት ሰነዱ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ ግጭቶች ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች የቃል ኪዳን ሰነድ ነው ብለዋል። ስምምነቱ በሰባት ዞኖች 33 ወረዳዎች ሥር በሚገኙ 147 ቀበሌዎችና መንደሮች መካከል አስተዳደራዊ ወሰን የማካለል ሥራን የሚመለከት ነው።

ሥምምነቱን ተከትሎ የሁለቱ ክልሎች ርዕሣነ መስተዳድር ግጭት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ዘላቂ ልማት በማረጋገጥ አለመግባባቶችን ከመሠረታቸው ለመፍታት እንደሚሰሩ ቃል ገበተዋል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ባደረጉት ንግግር፣ ሁለቱ ክልሎች በቋንቋና ባህል የተጣመሩ በመሆናቸው የሚያጋጭ ምክንያት የላቸውም። የሁለቱ ክልሎች ግጭት በዋነኝነት በተፈጥሮ ጫና የተነሳ በአካባቢው ልማት ባለመኖሩ የተቀሰቀሰ ከድህነት ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል። በአካባቢው በተለይ የውኃና የመንገድ መሠረተ ልማቶችን በመዘርጋት የሕዝቡን የልማት ጥያቄ በዘላቂነት በመፍታት ግጭቶችን ለማስቀረት እንደሚሰሩም ገልፀዋል። ይህም ለአካባቢዎቹ ብቻ ከሁለቱ የክልል መንግሥታት በጀት በመመደብ እንደሚከናወን አቶ አብዲ አስታውቀዋል። የተደረሰው ሥምምነት ለሕዝቡ ችግር ዘላቂ መፍትሄ የሚያበጅ በተለይም ለአመራሩ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሣ በበኩላቸው በሁለቱም ክልሎች የመሬት ችግር ያለመኖሩንና ከበቂ በላይ መሬት መኖሩን ገልፀው፣ የግጭቱ መንስዔ ቁራሽ መሬት አለመሆኑን አመልክተዋል። ክልሎቹ የሚጋሯቸውን አካባቢዎች ለማልማትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን እንደሚንቀሳቀሱና አለመግባባቶችን ለመፍታት  በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል። አካባቢው ለዘመናት ልማት ተነፍጎት ቆይቷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ለመቀልበስ የልማት ሥራዎችን በስፋት በመሥራት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ኑሮ መቀየር የሚገባ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

እንግዲህ፣ በሁለቱ ክልሎች የተወሰኑ አካባቢዎች የተፈጠሩት ግጭቶች የህዝብ ለህዝብ ግጭቶች አይደሉም። በክልሎቹ አዋሣኝ አካባቢዎች የሚገኙት ነዋሪዎች ቋንቋና ባህል ተጋርተዋል። ግጭት የተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች ቆላማ የአርብቶ አደር መኖሪያ ናቸው። በዚሀ ምክንያት በአካባቢዎቹ ከሥፍራ ሥፍራ በመንቀሳቀስ ከሚከናወነው የአርብቶ አደርነት የኑሮ ሁኔታ የተነሳ አልፎ አልፎ በግጦሽ ሣርና በውኃ ሽሚያ ምክንያት ግጭቶች ሲቀሰቀሱ እንደኖረ ይታወቃል። ይህ ችግር የክልሎቹ ርዕሳነ መስተዳደር እንደገለጹት አካባቢው የህዝቡን ኑሮ ማሻሻል በሚያስችል አኳኋን ባለመልማቱ የተፈጠረ ነው። አካባቢው ሲለማ የግጭት መንስዔ ሆኖ የቆየው የግጦሽ ሣርና የውኃ ሽሚያው ስለሚያበቃ ግጭቱ ታሪክ ሆኖ የሚቀር መሆኑ እውነት ነው።

የሁለቱ ክልሎች አጎራባች ክልሎች ማኅበረሰቦች በዘመናት የአብሮነት ኑሯቸው በተለያየ አጋጣሚ በግጦሽ ሣርና በውኃ ሽሚያ ግጭት ውስጥ ሲገቡ መቆየታቸው እውነት ቢሆንም፣ ወደዘላቂ ግጭትነት ተቀይረው ግን አያውቅም። ማኅበረሰቦቹ ግጭቶች ሲያጋጥሟቸው የሚፈቱበት ባህላዊ ሥርዓት አላቸው። በተለይ በቦረና አካባቢ ያሉት የሁለቱ ክልሎች ብሄሮች ግጭቶችን ለመፍታት በጋራ የሚመሩት “ናጋ ቦረና” ወይም “የቦረና ሸንጎ” የተሰኘ ተቋም አላቸው። በዚህ ሣቢያ የሁለቱ ክልሎች አዋሣኝ ማኅበረሰቦች መካከል ያለው ግንኙነት ሠላማዊ ሆኖ የዘለቀ ነው።

በሁለቱ ክልሎች አዋሣኝ ማኅበረሰቦች መካከል ዘንድሮ የተፈጠረውን ችግር ወትሮ ከነበረው የተለየ ገጽታ እንዲኖረው ያደረገው በሁለቱም ክልሎች በኩል በተለይ በድንበር አቅራቢያ ያሉ አካበቢያዊ የመስተዳዳር አካላት እጃቸውን ማስገባታቸው መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ። በሁለቱ ክልሎች አዋሣኝ አካባቢዎች ተወላጅነታቸው ያስገኘላቸውን የሁለቱንም ብሄሮች ማንነት የመላበስ እድል፣ አንዳንድ ፓለቲከኞች ለግል ፍላጎታቸው ማስጠበቂያነት ለማዋል ያደረጉት ጥረት የግጭት አባባሽ ምክንያት መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ። ለምሣሌ ኦሮሚያ ውስጥ የአካባቢው ተሿሚ የነበሩና በተለያየ ምክንያት ይህን ሹመት ያጡ ግለሰቦች ማንነታቸውን ወደሶማሌነት ለውጠው የሚኖሩበትን የወሰን አካባቢ የኢትዮጵያ ሶማሌ አካል ነው በሚል ይህን ከህግ ውጭ ለማስፈፀም የተንቀሳቀሱ ሰዎች እንደነበሩ ይታወቃል። በኢትዮጵያ ሶማሌም ክልል በኩል ተመሳሳይ ሁኔታዎች ነበሩ።

እነዚህ በሁለቱ ክልሎች አዋሣኝ አካባቢዎች ያሉ የመስተዳደር አባላትና ፖለቲከኞች ሠላም የማስከበር ኃላፊነት የተጣለባቸውን የአካባቢውን ታጣቂ ሚሊሻዎች በግጭቱ ውስጥ እንዲገቡ ያደረጉበት ሁኔታም ነበር። በዚህ ሁኔታ ታጣቂዎች ተኩስ በመክፈት የአካባቢው ነዋሪ እንዲሸሽ በማድረግ፣ ልክ እንደዘመነ መሣፍንት ተሰፋፊ ኃይል ሰዎች ፈርተው የለቀቁትን አካባቢ መቆጣጠራቸውን ለማሳወቅ ክልላዊ ሰንደቅ ዓላማዎች እንዲተከሉ ያደረጉባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ።

በሁለቱም ክልሎች እነዚህ ግጭት እንዲቀሰቀስና እንዲባባስ ያደረጉ ግለሰቦች ተለይተው ታውቀዋል። ሁለቱ ክልሎች ሰሞኑን በፈፀሙት ስምምነት በግጭቱ ውስጥ እጃቸውን ያስገቡ በሙሉ በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ተስማምተዋል። ይህ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር ስለሆነ እንደ ዋዛ ሊታለፍ እንደማይገባው የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከተው የፌዴራል መንግሥት ተቋም ሊያስታውሱ ይገባል። በተመሳሰይ ሁኔታ ዳግም ግጭት እንዳይቀሰቀስ ማስተማሪያም መሆኑ ሊታወስ ይገባል።

ከዚህ በተጨማሪ ለግጭቱ መፍትሄ የማፈላላግ ኃላፊነት ወስደው፣ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ እንዲቀጥል በማድረግ አበል መብያ ያደረጉ የአገር ሽማግሌ ተብዬዎች እንደነበሩም ታውቋል። እነዚህ የአገር ሽማግሌ ተብዬዎች ግጭት ውስጥ የገቡት ማኅበረሰቦች ውስጥ ለዘመናት በኖረው የሽምግልና እርቅ ሥርዓት መሠረት መፍትሄ የማበጀት ኃላፊነት ነበር የወሰዱት። መንግሥት ይህን የተቀደሰ ዓላማ እንዲያሳኩ የሚያስፈልጋቸውን ወጪ ለመሸፈን አበል ቆርጦላቸው ነበር። ሽማግሌ ነን ባዮቹ ግን ከሚወርደው ሠላም ይልቅ አበሉ ስለጣማቸው ግጭቱ እንዲራዘም ማድረግን የመረጡበት ሁኔታ ነበር።

ሁለቱ ክልሎች ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ የክልሎቹ ርዕሣነ መስተዳድር በተገኙበት በድሬዳዋ ከተማ በተካሄደ ህዝባዊ ስብሰባ እርቅ በማውረድ ሰበብ አበል እየበሉ ግጭቱን ማቆሚያ እንዳያገኝ ያደረጉ ግለሰቦች ሁለተኛ በጉዳዩ ውስጥ እንዳይገቡ እንደሚደረግ በይፋ ተነግሯል።

በአጠቃላይ አሁን የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግሥታት በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንደተመለከተው፣ ከአሥራ ሁለት ዓመት በፊት በ1997 ዓ.ም በተካሄደ ህዝበ ውሣኔ የተደረሰበትን ውጤት መሬት ላይ ወሰን በማካለል መጨረሻ እንዲያገኝ ለማድረግ ተስማምተዋል። ይህ ወሰን የማካለል ተግባር በወቅቱ ሳይካሄድ መቅረቱ ያስከፈለው መስዋዕትነት ሳይዘነጋ በሁለቱ ክልሎቸ አጎራባች ማኅበረሰቦች መካከል ዳግም ግጭት እንዳይቀሰቀስ በማድረግ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑ እርግጥ ነው።

የሁለቱ ክልሎች አጎራባች አካባቢ ማኅበረሰቦች፣ ለዘመናት ሲጠቀሙበት የነበረውን ግጭት የመከላከልና እርቅ የማውረድ ሥርዓት ያሸነፈ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ ሁኔታዎችን ያባባሱ ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ማንም ችላ ሊለው የማይቻለው የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ከመሆኑ ባሻገር፣ ለአካባቢው ዘላቂ ሠላም ዋስትና የሚሰጥ የመሆኑ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የህግ የበላይነት ባልተከበረበት ሁኔታ የሠላም ዋስትናን ማረጋግጥ እንደማይቻል መታወቅ አለበት።

ይሁን እንጂ፣ መሠረታዊው ግጭት ቀስቃሽ ምክንያት የልማት እጦት መሆኑ መታወቅ አለበት። የተቀሩት አባባሽ ሁኔታዎች ናቸው። በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሣኝ አካባቢዎችም ሆነ በሌሎች የአርብቶ አደር መኖሪያ በሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች በግጦሽ ሣርና በውኃ ሽሚያ ግጭቶች ሲቀሰቀሱ መቆየታቸው ይታወቃል። ይህ ግጭት በሁለት ክልሎች ብሄሮች መካከል ብቻ ሳይሆን፣ በአንድ ክልል ውስጥ በሚገኙ ተመሳሳይ ብሄራዊ ማንነት ባላቸው ማኅበረሰቦች መካከልም የተለመደ ነው። በግጦሽ ሣርና በውኃ ሽሚያ የሚነሱ ግጭቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው በልማት ብቻ ነው። ውኃንና መስኖን ማዕከል ያደረጉ አርብቶ አደሩን ከቦታ ቦታ ከመዘዋወር የኑሮ ሁኔታ ደረጃ በደረጃ አንድ ቦታ ረግቶ መኖር ወደሚያስችለው የኑሮ ሁኔታ የማሸጋጋር ተግባር ለነገ የሚባል አይደለም። ይህን ማሳካት በተቻለበት ልክ የግጭት መንስዔ ምክንያቶች ይቀንሳሉ። የግጭት መንስዔዎች ሲወገዱ ከግጭት ለማትረፍ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ቀዳዳ ያጣሉ። ልማት ለሠላም! ይሏል ይህ ነው።  

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy