Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መንግሥት ሒልተን ሆቴልን ለመሸጥ በወራት ጊዜ ውስጥ ጨረታ ለማውጣት እየተዘጋጀ ነው

0 359

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

  • ሻንግሪላን ጨምሮ በርካታ ኩባንያዎች ፍላጎት አሳይተዋል

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለአምስት ኮከብ ሆቴል የነበረውን ሒልተን ሆቴል ለመሸጥ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ከሦስት ወራት በኋላ ጨረታ ያወጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ በዚህ ጨረታ ለመሳተፍ ከአሥር ያላነሱ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እየተጠባበቁ መሆኑ ታውቋል፡፡

ሒልተን አዲስ አበባን የራሳቸው ለማድረግ ፍላጎት ካሳዩ ኩባንያዎች መካከል ሰንሻይን ግሩፕ፣ መቀመጫቸውን ሆንግ ኮንግና ዱባይ ያደረጉት ሻንግሪላና አል ባዋርዲ ኢንቨስትመንትስ ይገኙበታል፡፡

ሰንሻይን ግሩፕ መስቀል አደባባይ አካባቢ ማርዮት ሆቴልን፣ በዚሁ ዓለም አቀፍ የንግድ ስያሜ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ተጨማሪ ሆቴል እየገነባ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሐዋሳ በሒልተን ሆቴል ስያሜ የሚተዳደር የሆቴል ፕሮጀክት ነድፏል፡፡ መቀመጫውን ሆንግ ኮንግ በማድረግ የመጀመሪያውን ሆቴል በሲንጋፖር በመገንባት ወደ ሆቴልና ሪዞርት ቢዝነስ የገባው ሻንግሪላ በበርካታ አገሮች 99 ሆቴሎችንና ሪዞርቶችን ያስተዳድራል፡፡ ይኼ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ሒልተን ሆቴልን ለመግዛትና ተጨማሪ አዲስ ሆቴል በአዲስ አበባ ለመገንባትም ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ሦስተኛው ኩባንያ አል ባዋርዲ ኢንቨስትመንትስ ነው፡፡ ይኼ ኩባንያ ቀደም ሲል አልካሪፊ ሆቴል ኢትዮጵያ ኩባንያ፣ መስቀል አደባባይ የገነባቸውን ሁለት የሆቴል ፕሮጀክቶች በ25 ሚሊዮን ዶላር በመግዛት ኢትዮጵያ ገብቷል፡፡ ሁለቱ ሆቴሎች 10,232 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፉ ናቸው፡፡ ይኼ ኩባንያ ሒልተን ሆቴልን ለመግዛት ለጠቅላይ ሚነስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

መንግሥት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥያቄዎች ቢቀርቡለትም ሆቴሉን በግልጽ ጨረታ ለመሸጥ አቋም በመያዙ፣ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በጨረታው ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሰንሻይን ግሩፕ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳሙኤል ታፈሰ፣ በጥቂት ወራት ውስጥ በሚወጣው ጨረታ ለመሳተፍ እየተዘጋጁ መሆኑን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

መንግሥት የተለያዩ ኩባንያዎች ሒልተን አዲስ አበባን በድርድር ለመግዛት ጥያቄ ቢቀርብለትም ጥያቄዎቹን ባለመቀበል፣ ሒልተን አዲስ አበባ በግልጽ ጨረታ እንዲሸጥ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴርና በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ለሚመራው የሒልተን ሆቴል ሥራ አመራር ቦርድ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ ሊደርስ የቻለው አገር በቀል ኩባንያዎች ለገነቧቸው ሆቴሎች የማኔጅመንት ሥራውን ዓለም አቀፉ ሒልተን እንዲያስተዳድርላቸው በሚፈልጉበት ወቅት፣ ሒልተን በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከመንግሥት ጋር የገባው ውል ሌሎች ሆቴሎች በሒልተን ስም እንዳይተዳደሩ የሚከለክል በመሆኑ፣ መንግሥት ውሳኔ እንዲሰጥ ጥያቄ በመቅረቡ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት በተለይ ሰንሻይን ግሩፕና ፀሜክስ ሆቴልና ቢዝነስ ኩባንያ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ፍላጎታቸውን ማቅረባቸው ታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ላለፉት 50 ዓመታት ሆቴሉን ሲያስተዳደር የቆየው ሒልተን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የገባው ውል ሊጠናቀቅ ከሁለት ዓመት ያነሰ ጊዜ (አንድ ዓመት ከስምንት ወር) ብቻ የቀረው ስለሆነ፣ መንግሥት ሁለት መሠረታዊ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

የመጀመሪያው በሒልተን ወርልድ ዋይድ ኩባንያ የንግድ ስያሜ መተዳደር የሚፈልጉ የሆቴል ፕሮጀክቶች መተዳደር እንደሚችሉ፣ ሁለተኛው ደግሞ መንግሥት በሆቴል ቢዝነስ ውስጥ የሚያቆየው አስገዳጅ ሁኔታ ስለሌለ ሒልተን አዲስ አበባ በግልጽ ጨረታ እንዲሸጥ ወስኗል፡፡

በዚህ መሠረት ሆቴሉን ለገበያ ማቅረብ የሚያስችሉ የጨረታ ሰነዶች ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑ ታውቋል፡፡

ባለ 12 ወለል ከፍታና በላሊበላ ቅርፅ ውብ ተደርጎ የተገነባው ሒልተን አዲስ አበባ በ60 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ነው፡፡

ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ንብረት የሆነው ሒልተን በቂ እድሳት የተደረገለት ባለመሆኑ፣ እንዲሁም የማብሰያና የእንግዳ ክፍሎች አያያዝ ላይ በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ባለሙያዎች በተካሄደ ምዘና አነስተኛ ነጥብ በማግኘቱ፣ ባለሦስት ኮከብ ሆኖ መመደቡ ይታወሳል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy