Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሚዲያውና የገዘፈው ተግባሩ!!

0 299

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሚዲያውና የገዘፈው ተግባሩ!! /ይነበብ ይግለጡ/

                        የፕሬስ ነጻነት በሀገራዊ በአህጉራዊና በአለም አቀፍ ደረጃ መብቱ የተከበረለት ነጻነት ነው፡፡ የፕሬስና የመናገር ነጻነት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤በአፍሪካ ሕብረት፤ በአውሮፓ ሕብረት እውቅናና የሕግ ጥበቃ ያለው ነው፡፡ ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ በነጻነት ሊጠቀምበት የሚገባ ከየትኛውም ሶስተኛ ወገን ተጽእኖና ጫና ውጪ የሌሎችንም ሰብአዊና ዲሞክራሲዊ መብት ሳይነካ በተግባር ሊያውለው የሚችለው መብት ነው፡፡

ከዚሁ መሰረታዊ ነጻነት ጎን ለጎን በነጻነት የመስራት የመንቀሳቀስ የፈለጉትን የሀይማኖትም ሆነ የፖለቲካ እምነት የመከተል ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትም በሕግ እውቅናና ድጋፍ ያላቸው መብቶች ናቸው፡፡በሀገራችን የፕሬስ ነጻነት የተጀመረው አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ባጸደቀው ሕገመንግስት አንቀጽ 29 መሰረት ሲሆን በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሰፊ የግል ፕሬሶች እንደ አሸን የፈሉበት ሁኔታ ተከስቶም ነበር፡፡ እያንዳንዳቸው በየራሳቸው ኢዲቶሪል ነጻነት የሚሰሩና የሚንቀሳቀሱ የመሆናቸውን ያህል የይዘት የአሰራር ልዩነትም ነበራቸው፡፡

አክራሪና ጽንፈኛ፤ለዘብተኛና መሀል ሰፋሪ፤ቀኝና ግራ ዘመም  በሚል የሚፈረጁ የግል ፕሬሶችም በብዛት ታይተዋል፡፡በሀገሪቱ የግሉ ፕሬስ ብዙ ዘመን ያላስቆጠረ ጅምርና ገና ለጋ የነበረ የመሆኑን ያህል ብዙ ክስተቶችም አብረውት ተወልደው አልፈዋል፡፡ቀድሞ ከነበረው ሁኔታ አንጻር ሲነጻጸር በአሁኑ ሰዓት የግሉ ፕሬስ በኢትዮጵያ አለ ከማለት ይልቅ የለም ማለቱ ይቀላል፡፡ዛሬ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በሕብረተሰቡ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩ አራት የሚሆኑ በአማርኛ የሚታተሙ ጋዜጦችና መጽሄቶች አሉ፡፡

በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሶስት የሚሆኑ የተወሰኑ ጋዜጦች ያሉ ሲሆኑ እነዚህ ተደራሽነታቸው ለኤምባሲዎችና ለአለም አቀፍ ተቋማት ነው፡፡ የውጭ ሰዎች በሀገሪቱ ያለውን ሁኔታ ለመረዳት የመረጃ ምንጭ አድርገው የሚከታተሉዋቸው ናቸው፡፡በቁጥር ጥቂት የሚባሉ የተማሩ ግለሰቦች ከሚያነቡዋቸው በስተቀር ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ተደራሽ አይደሉም፡፡ ጭርሱንም አያያቸውም፡፡

ሌሎቹ የስፖርት የመዝናኛና በማሕበራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩ የግል ፕሬሶች ናቸው፡፡ የማያወላዳ የገንዘብ አቅም የሌላቸው የራሳቸውንም ወጪ በቅጡ የሚሸፍኑ አይደሉም፡፡ይህ ቁጥር ዛሬ 103 ሚሊዮን ለደረሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፡፡ስርጭታቸውም ከአዲስ አበባ አያልፍም፡፡ የሕትመት ቁጥራቸውም ግፋ ቢል ከአምስት ሺህ የዘለለ አይደለም፡፡ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብዝሐነት የሚመጥን ሰፊ የግል ፕሬስ መኖርና ማደግ ይገባዋል፡፡

የአንዳንዶቹ የግል ጋዜጦች ገጾች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በማስታወቂያ የተሞሉ ለሕብረተሰቡ የሚሰጡት ወይም ስለ ሕብረተሰቡ ጉዳይ አንስተው የሚነጋገሩበት ገጽ እጅግ በጣም የተወሰነና በማስታወቂያ ንግድ ላይ ተሰማርተው ትርፍ የሚሰበስቡ ናቸው፡፡በዚህ ደረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ የግል ፕሬስ አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡ በ103 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 10 የማይሞሉ ጋዜጦችና መጽሄቶች መኖር የግል ፕሬስ አለ ለማለት የሚያስደፍር ከሆነ አለ ብሎ ማለት ይቻላል፡፡ በትክክለኛው መንገድ እንየው ከተባለ ግን የለም ማለቱ ሚዛን ይደፋል፡፡

ያለውም የግሉ ሚዲያ በጥቂት ግለሰቦች እጅ በሞኖፖል የተያዘና የወደቀ መሆኑ  በእጅጉ አሳሳቢ ነው፡፡የአብዛኛውን ሕዝብ ስሜትና ፍላጎት ለማንጸባረቅ የሚችሉ የተለያዩ  ድምጾች የሚሰሙበት የግል ሚዲያ መኖር ጠቃሚነቱ ለሀገር ለሕዝብም ነው፡፡ ከሰፊውና ውቅያኖስ ከሆነው የሀሳብ  ገበያ ውስጥ ብዙ መገብየት መሸመት ይቻላል፡፡ሰፊ ብዝሀነት ባለበት ሀገር የተለያየ ሀይማኖት ባሕል ቋንቋ ስነልቡና ጎልቶ በሰፈነበት ሀገር የግሉ ፕሬስ በብዛት መኖር ነበረበት፡፡ የግሉ ፕሬስ ለምን ተዳከመ፤ ለምን አቅም አጣ፤ለምን ሕልውናው ተዳከመ ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ ተጨባጫ መልሶች አሉት፡፡

የመጀመሪያው ጠንካራ የሆነ የኢኮኖሚ አቅም የሌለው በመሆኑ ገበያው ውስጥ ጸንቶ ሊቆይ የሚችልበት ሁኔታ  አልነበረም፡፡ውድድሩን ለመመከትና ለማለፍ የሚያስችለው አቅም አልነበረውም፡፡ ስለዚህም ከተወሰነ ተከታታይ ሕትመት በኃላ ለማቆም ይገደዳሉ፡፡ሌላ ምንም የገቢ ምንጭና ድጋፍ የሚያደርግላቸው ስለሌለ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ተደራራቢ ክሶች በግሉ ፕሬስ ላይ ስለሚሚመጡ በሚጣልባቸው ቅጣት ጭምር ለመስራት ያለመቻላቸው እውነት ነው፡ በዚህ መሰረታዊ ምክንያት  በዘርፉ ለመሰማራትና ለመስራት የሚፈልግ ዜጋ አለመኖርም ጭምር ነው የግሉን ፕሬስ ከመኖር ወደ አለመኖር ያሸጋገረው፡፡ ኤሌክትሮኖክስ ሚዲያውንም በተመለከተ ጥቂት ማለት ይቻላል፡፡

በአሁኑ ሰአት የሕዝቡን ችግር ብሶት በመልካም አስተዳደር በሙስናና በፍትሕ እጦት በሕብረተሰቡ ላይ ደርሶ የነበረውንና የደረሰውን ችግር በአደባባይ አውጥተው ከሕዝቡ ጋር በግልጽ በመነጋገር መንግስት ችግሩን በቅርበት እንዲያውቅ እንዲረዳ እንዲፈታው  በማድረግ ረገድ ጠንክረው እየሰሩ ያሉ የግል ኤፍኤሞች ዛሚና ሸገርን የመሰሉ አሉ፡፡ ሊበረታቱም ይገባቸዋል፡፡

በድሀ ሀገር የአየር ሞገድ ሰአት የቆጡን የባጡን ሲያወሩ በዋዛና በፈዛዛ ሲያውካኩ መሽቶ የሚነጋባቸውም ኤፍኤሞች አሉን፡፡ስንትና ስንት የሚያስጨንቅ የሚያሳስብ በሰላም ልንፈታው የሚገባን ብዙና የተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ሞልተው በፈሰሱበት ሀገር  የደላንና ምንም ችግር የሌለ ይመስል በቧልት በፌዝ በቀልድ አንዳንዶችም ከአቀራረብ ከስነምግባር ጀምሮ በብዙ ችግር የተጠመዱ አሉ፡፡ እንደነዚህ አይነት ሚዲያዎች የአድማጭን አእምሮ ከማደንዘዝ ውጭ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ፋይዳ የላቸውም፡፡

የመንግስትን ሚዲያ ስንመለከት የሕዝብን ችግር በማንሳት በማወያየት ችግሩን አንጥሮ በማውጣት መፍትሄ እንዲገኝ የማስቻል አቅማቸው በእጅግ የተመናመነ ነው፡፡እንግድያማ  በሀገሪቱ ውስጥ እንደ መንግስት ሚዲያ ያለ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ጋዜጠኞችን የያዘ የረቀቁ  ዘመናዊ የመገናኛ ብዙሀን መሳሪያዎችን የታጠቀ በቂ ትራንስፖርት ያለው የትም ቦታ ተንቀሳቅሶ ለመስራትና ለመድረስ የሚያስችል አቅም ያለው ሌላ ኃይል በኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ግን እንዳይሰራ በቢሮክራሲው ማነቆ ተሰንጎ የተያዘ ይመስላል፡፡ጩህ ሲባል የሚጮህ ዝም በል ሲባል ዝምታን የሚመርጥ በራሱ ግዜ በነጻነት ሰርቶ ፋይዳ የሚያስገኝ አይነት አይደለም፡፡ስርነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡

ይህን ከፍተኛ ድርጅታዊ አቅም ለበለጠ ውጤት ለስኬት ለግልጽነት ተደማጭነትን  ለመፍጠር ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት ችግሮችን ለመፍታት መቀራረብ እንዲፈጠር ለማድረግ መጠቀም ይገባዋል፡፡ ሕዝብን ከሚያስከፉ ከሚያስቆጡ ዘገባዎች የአንድ ወገን ዘገባዎች መጠንቀቅ ሚዛናዊ በአግባቡ የሚተች ችግሮችንና መፍትሔዎችን የሚያመላክት መሆን ይገባዋል፡፡በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሚዲያ የግሉም የሆነ የመንግስት ትልቅ የፖሊሲ ለውጥና ሪፎርም ሊያደርግ የሚገባው ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ የቀድሞዎቹ አሰራሮችና መንገዶች አዋጪ አልሆኑም፡፡ አሰራሩን መቀየርና ስርነቀል ለውጥ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ይህን ማድረግ ካልተቻለ በምንም አይነት ተአምር በሚዲያው ደረጃ  ሀገራዊ ለውጥና እድገት ማምጣት አይቻልም፡፡

በሰፊው ለሕዝቡ ተደራሽ ለመሆን የሚያስችላቸውን ታክቲክና ስትራቴጂ መቀየስ ለዚህም ስኬት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ማንኛውም ሚዲያ ሕግንና ስርአቱን ተከትሎ በሕጉ የተከለከሉትን ትቶ በተጨባጩ ማስረጃ ተመርኩዞ መውቀስ መተቸት መንቀፍ እንዲሁም ችግሩን ብቻ ሳይሆን መፍትሄውንም የማመላከት የመፍትሄውም አካል የመሆን ሙያዊ  ግዴታ አለበት፡፡

በመንግስትም ሆነ በግሉ ፕሬስ ባለፉት በርካታ አመታት የታየው ትንቅንቅ አንድን ወገን አጉልቶ ሌላውን የማኮሰስ የማጥላላት በስሜትና በጥላቻ ወጀብ ታጅቦ አንዱ በሌላው ላይ የመዝመቱ ሁኔታ ለሀገር ለሕዝብ ሰላምና መረጋጋት ልማትና እድገት ጭርሱን የሚጠቅም እንዳልሆነ በአለፉት በርካታ አመታት ተሞክሮ በተጨባጭ ታይቶአል፡፡

እኔ ጋ ብቻ ነው እውነቱ ያለው፤እኔ ብቻ ነኝ ትክክል፤እኔ ብቻ ነኝ ለሀገር አሳቢና ተቆርቋሪ ሌላው ጸረ ሀገር ጸረ ሕዝብ ነው የሚለው ፍረጃ ደካማና ኃላቀር አስተሳሰብ በሁለቱም ጎራ እያደገና እየሰፋ ሄዶ ልዩነትን ማጥበብ በሰለጠነ መንገድ ችግሮችን መፍታት ለጋራ ሀገር ከልዩነት ባሻገር በጋራ ጸንቶ መቆም መስራት ያልተቻለበት ጎራ ለይቶ መወነጃጀሉ መነታረኩ አልፎም በእልህና በስሜታዊነት በጥላቻ ተዘፍቆ ከውጭ ጠላቶች ጋር የመሰለፍና ሀገርን ከጀርባ የመውጋት ሁኔታዎችን ለመፍጠር በቅቶአል፡፡ ለሀገርም ለሕዝብም አይበጅም፡፡

ሀገርን ሕዝብን መንግስትን መለየት ይገባል፡፡ በእንዲህ አይነቱ የከፋ ትንቅንቅ ሀገርንም ለውጭ ኃይሎች መጫወቻነት አሳልፎ መስጠት ሊከተል እንደሚችልም መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ የግሉ ፕሬስ ማደግ መጠንከር መጎልበት የሕዝብንም ሆነ በመንግስትም ውስጥ  ያለውን ችግር ነቅሰው የሚያወጡ ባለስልጣናትን በማስረጃ የሚተቹ የሚወቅሱ ሙስናን የመልካም አስተደዳደርና የፍትሕን ችግር አንጥረው የሚያሳዩ ከስሕተቱ እንዲታረም በማስረጃ በሚዛናዊነት የሚሰሩ ችግሩንም መፍትሄውንም አጥርተው የሚያሳዩ የግል ፕሬሶች መኖር ዛሬ ለኢትዮጵያ ከምንግዜውም በላይ ወሳኝ የሆነበት ወቅት ላይ ተደርሶአል፡፡

ጠንካራ የግል ፕሬሶችን ለመፍጠር መንግስትም ሕዝብም ሊረባረብ ይገባል፡፡ምክንያቱም የጤነኛ ዴሞክራሲ መለኪያ መስፈርቱ የመንግስት ሚዲያ ብቻ መኖር ወይንም ጥቂት ግለሰቦች ሚዲውን በሞኖፖል መያዛቸው አይደለም፡፡ብዝሀነትን የዋጠ የተለያዩ ድምጾች ሳይሰሙ ታፍነው እንዲቀሩ የተደረገ መስሎ ነው በውጭው አለም የሚወሰደው፡፡ በቅርቡ በነበረው የፈረንሳይ ምርጫ እጩ ተወዳዳሪዎች ካነሱዋቸው የመወዳደሪያ ነጥቦች መካከል የሚዲያ ሞኖፖሊን መዋጋት የሚለው አንዱ ነበር፡፡

አለም አቀፉ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን አይኤፍጄ የሚዲያ ሞኖፖሊ ለሕዝብ አሳሳቢ አደጋ እየሆነ መምጣቱን ቀደም ባሉ አመታት ገልጾአል፡፡ በአውሮፓ ለጋዜጠኞች መብት ለብዝሐን ድምጽ መሰማት እንዲሁም ለዲሞክራሲ አደጋና ከባድ ችግር መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቶአል፡፡

የሚዲያ ሞኖፖሊ ዲሞክራሲያዊነትን በማቀጨጭ አምባገነንነት እንዲወለድ ትልቅ በር ይከፍታል፡፡ በሂደትም ጸረ ዲሞክራሲ ይሆናል፡፡ በስተመጨረሻም ሕብረተሰቡ የእኔነት ስሜት ስለሚያጣ ድምጹ ስለማይሰማና ስለሚረገጥ እውነቶች ታፍነው ስለሚቀርቡ ሀሰት ገኖ ስለሚወጣ ለሰላምና መረጋጋት እጦት ትልቅ በር ይከፍታል፡፡

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እድገት በመሰረት ልማት በሜጋ ፕሮጀክቶች መስፋፋትና ማደግ፤የውጭ ኢንቨስትመንትን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባትና ተመራጭ ሀገር በመሆን ረገድ አለምአቀፍ አድናቆቶችን ያተረፉ ምስክርነት የተሰጠባቸው ታላላቅ ስራዎች ሰርታለች፡፡የፕሬስ ነጻነትን አክብሮና አስከብሮ በመስራት ዲሞክራሲውን በማስፋትና አሳታፊ በመሆን ረገድ እጅግ በጣም ብዙ ይቀራታል፡፡

ለዚህም አብይ ምክንያቱ አሁን ግዜው እየገለጸው የመጣው እውነት በራሱ በመንግስት ውስጥ ተሸሽጎና አድፍጦ ሲሰራ የነበረው ኪራይ ሰብሳቢና ሙሰኛው እንዲሁም መልካም አስተዳደርንና ፍትህን ሲረግጥ የነበረው ስብስብ የመንግስቱም ሆነ የግሉ ፕሬስ ተጠናክሮ የሕዝብ ድምጽ እንዲሆን ችግሮችን አፍረጥርጦ እንዲያወጣ እንዲያጋልጥ አይፈቅድም አይፈለግምም ነበር፡፡

ዋናው ምክንያቱ እጋለጣለሁ ብሎ ስለሚፈራ ስለሚባንን ጋዜጠኛውን አንገት ማስደፋት በእስር ማዋከብ ጫና ማሳደር ከስራው እንዲርቅ ማድረግ አልፎም ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት ስራው እንዲቋረጥ በማድረግ ረገድ ሰፊ ሚናዎችን ተጫውቶአል፡፡

ጠንካራና ሚዛናዊ ሆነው የሚሰሩ የግሉም ሆነ የመንግስት ሚዲያ ተቋማት በሁሉም አካባቢዎች ቢኖሩ ኖሮ ሙስና ኪራይ ሰብሳቢነት የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ችግር እንዲህ ገኖ ልቅና መረን ወጥቶ አይፈነጭም ነበር፡፡ለሀገር አደጋ ሁኖ የሚከሰትበት እድል ይቀንስ ነበር፡፡የመንግስት ሚዲያውም ሆነ የግሉ ሚዲያ መጠንከርና መጎልበት ለራሱ ለመንግስትም ሆነ ለሕዝብ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፡፡

ሕዝብ የሚሰማውን ስሜት ይተነፍሳል፡፡ሀሳቡን በነጻነት ይገልጻል፡፡ቸግሩን ይፋ ያደርጋል፡፡መንግስት ደግሞ በራሱ አቅም ሊደርስበት ከሚችለው በላይ ያለውን ከግሉ ፕሬስ ሰፊ መረጃዎችን ያገኛል፡፡ የሕዝቡንም ችግር በሰፊው በመረዳት ለመፍትሄ ፍለጋም ቀላል መንገድ ይሆንለታል፡፡ መንግስት የተነገሩትን የተባሉትን የተሰጡትን አስተያየቶችና ጥቆማዎች በራሱ መንገድ ያጣራል፡፡ያረጋግጣል፡፡ችግሩንም ለመፍታት ለማስተካከል የእርምጃ መነሻ ይሆነዋል ማለት ነው፡፡በሌላውም ሀገር የሚደረገው እንዲዚሁ ነው፡፡

ለዚህ ነው የግሉ ፕሬስ መጠንከርና መጎልበት ለራሱ ለመንግስት መስተዋት ሁኖ እውነተኛ በሕዝቡ ውስጥ ያለውን ስሜትና መልክ ሊያይበት የሚችል መለኪያ ነው የሚሆነው፡፡ የመንግስቱም ሆነ የግሉ ሚዲያ ሕዝብን ማእከል አድርገው እስከሰሩ ድረስ በሀገር ደረጃ ያሉ ብዙና ውስብስብ ችግሮችን መቅረፍ ይችላሉ፡፡

ባለስልጣናት በመገናኛ ብዙሀን ሕጉ መሰረት ተገቢ መረጃ በመስጠት ለሕዝብ የማሳወቅ ግዴታ ያለባቸው ቢሆንም ጉዳዩን ወደ ሕዝብ ግንኙነት ይመሩታል፡፡ ሕዝብ ግንኙነቱ የአለቆቹን ፊት አይቶ መረጃ ከመስጠት ይቆጠባል፡፡ምክንያት ያበዛል፡፡ያመላልሳል፡፡ደጅ ያስጠናል፡፡

ሕዝብ ሊያውቀው የሚገባውን መረጃ እንደ ግል ንብረቱ ጠረጴዛው ውስጥ ይቆልፈዋል፡፡ የራሱም የግል ንብረት ሳይመስለው አይቀርም፡፡ ጋዜጠኛውን አስቸገርከኝ የሚል ፍጥጫ ውስጥም ይገባል፡፡መረጃም ይከለክላል፡፡ይህን የመሰለ ስራውና ሰዎቹ ያልተገናኙበት ያልተዋወቁበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ችግሩ የራስ በመሆኑ መፈታት ያለበትም በራስ ነው፡፡ በአጠቃላይ ያለን ሚዲያ ስርነቅል ሪፎርም ለውጥና ተሀድሶ ያስፈልገዋል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy