የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ረቂቅ አዋጆችን ሲያፀድቅ አንድ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
በኢትዮጵያና ቻይና መንግስታት መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳይ ግለሰቦችን አሳልፎ የመስጠትና በፍትሃብሄርና በንግድ ጉዳዮች ላይ የተደረጉ የትብብር ስምምነቶችን በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።
የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት እንደገለፁት፥ በወንጀል ጉዳይ ግለሰቦችን አሳልፎ ለመስጠት የተደረገው ስምምነት በሃገራቱ ሠላም፣ ፀጥታና መረጋጋትን ለማረጋጋጥ አስተዋፅኦ አለው።
ሃገሪቷ የጀመረችውን የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አጠናክራ ለማስቀጠል የሕግ የበላይነት መከበር ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑና ወንጀል ፈፅመው ከሃገር የሚሸሹ ሰዎችን ለፍርድ ለማቅረብም ያስችላል ነው ያሉት።
የፍትሃብሄርና የንግድ ጉዳዮች ስምምነቱም በሃገራቱ መካካል እያደገ በመጣው የንግድና የፍትሃብሔር ግንኙነት አለመግባባቶች ቢፈጠሩ በቀላሉ መፍታት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በሃገራቱ መካከል ያሉ ተዋዋይ ወገኖች በውላቸው መሰረት ባይፈፅሙና ክርክር ቢነሳ መረጃዎች እንደ አስፈላጊነቱ ከሁለቱም ሃገራት በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑም ያደርጋል ብለዋል።
የፍርድ ሂደትን ለማፋጠን በተጨማሪም የሚሸሹና የሚደበቁ የሃገርና የግለሰብ ንብረቶችን ለማስጠበቅ ታስቦ የተደረገ ስምምነት መሆኑንም አስረድተዋል።
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወስን የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ መርምሮ፥ ለሕግ፣ ፍትህና አስተዳደርና ለንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።FBC