Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰው በአገሩ

0 394

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰው በአገሩ

በአቦዘነች ነጋሽ

‹‹ሰው በአገሩ- ቢበላ ሳር፣ቢበላ መቅመቆ

ይከበር የለም ወይ-ማንነቱ ታውቆ››

ይህ ውብ ስነ-ቃል ሀገራችን፣ እትብታችን የተቀበረባት አፈር፣ ማንነታችን የሚጠራባት ምድር የመሆኗ ጥልቅ ትርጉም ጥበባዊ በሆነ መንገድ ይገልጻል፡፡ ሀገር የትውልድ ማንነት የሚገለጽባት እውቅና  መገለጫ ናት፡፡ በሀገር መኖር ከስብዕና ክብር ጋር አብዝቶ እንደሚጎዳኝ ይናገራል፡፡

ከዚህ ስነ ቃል ተቃራኒ ያለው እውነት በስደት ሀገር ክብር አይታሰብም፡፡ ጥረታችን ምስጋናን   ላባችን ፍቅርን ይገዛል ተብሎም አይጠበቅም፡፡ ጭው፣እልም ባለ በረሃ በውሃ ጥማት ማለቅ፣ በእቃ መጫኛ በኮንቴነር ታሽጎ በአየር እጦት ተሰቃይቶ መሞት፣ በባህር ሰጥሞ ለአሳነባሪ ሲሳይ መሆን… እኒህ ሁሉ የመከራ ጥጎች በስደት ወቅት የሚያጋጥሙ ናቸው፡፡ ከስደት ወዲህ ማዶ በጉዞ ላይ የሚጋጥሙ  አማራጮች ሁሉ በዘግናኝነታቸው ተወዳዳሪ የላቸውም፡፡ ‹‹አሟሟቴን አሳምርልኝ›› እያለ የሚፀልየው የሀገሬ ሰው እኮ እንኳንስ ኑሮ ሞትና ቀብርም ወግ ስላለው ነው፡፡

ለዚህ ፅሁፌ መነሻ የሆነኝ የሰሞኑ ወሬ እውነትም ስደት ምን ያህል ክብርን ዝቅ እንደሚያደርግ በግልፅ ያሳያል፡፡ የአለም መገናኛ ብዙሃን  በስፋት እንደዘግቡት በነዳጅ ሀብቷ ቁጥር አንድ ተብላ የምትጠራው የመካከለኛ ምስርቅ ቱጃር ሀገር ሳዑዲ አረቢያ የመኖሪያ እና የስራ ፍቃድ የሌላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች በ90 ቀናት ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቧን ነው፡፡ በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ያለ መኖሪያና የስራ ፍቃድ በሳዑዲ የሚኖሩ ዜጎች መካከል ኢትዮጵያውያን 400 ሺህ እንደሚገመቱ  መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ዜጎች እንግልት ሳይደርስባቸው በተሰጠው የምህረት ቀናት ተጠቅመው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ጥሪ በማስተላለፉ  ዜጎች  መመለስ ጀምረዋል፡፡ ተመላሽ ዜጎች በደስታ ቀን አስጠግታ በክፉ ቀን ወደማትገፋቸው፣ በደስታም በሃዘንም መጠለያ ወደምትሆናቸው ወደ እናት ምድራቸው፣ ሲያዝኑ አፅናንቶ ሲቸገሩ ያለውን ወደሚያካፍለው ወገናቸው መመለስ መጀመራቸውን እንደመልካም አጋጣሚ በመሆኑ አለንላቸው  ልንላቸው ይገባል፡፡

ይህን ጅምር ለማደናቀፍም ከመነሻው በወገናቸው ስቃይ ጥቅም የሚያጋብሱ ህገ-ወጥ ደላሎች ‹‹በሀገር ሰርቶ የመለወጥ ምንም አማራጭ የለም›› የሚለው ስብከታቸውን አሁንም አጠናክረው ገፍተውበታል፡፡ እኒህ ሰው በላ አረመኔዎች የሚረጩት መርዘኛ ስብከት የሚያሳድረው ስነ-ልቦናዊ ጫና ዜጎችን ከጎጇቸው አውጥቶ ለስቃይ በመዳረግ ብቻ አይገታም፡፡ ከሀገር ወጪ ኑሮ በስተቀር የህይወት አማራጭ እንደሌለ  አድርጎ በማሳየት እንደሰው ሳይሆን ከክብራቸው ዝቅ ብለው እንደ እንስሳ በሚታዩበትና ህይወታቸውን እስከማስከፈል ለሚደርሰው ስደት ይዳረጋሉ፡፡

እውነት ግን ከዚህ ፍፁም የራቀ ነው፡፡ ስደት፣ መከራና እንግልት ያስተማራቸውና ከእንግዲህ ስደት ጠላቴ ያሉ ሁሉ በተከፈተላቸው በር አልፈውና የተመቻቸላቸውን ዕድል ተጠቅመው ሌት ተቀን ለለውጥ እየተጉ ይገኛሉ፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ ከስደት ተመልስው ሠርተው መለወጥ የቻሉ ወጣቶች አፍ አውጥቶ በሚናገረው ጉልህ ስኬታቸው የብዙዎችን ቀልብ ገዝተዋል፡፡ እነዚህ ወጣቶች በርግጥም በአገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል በተጨባጭ አስመስክረዋል፡፡ በስደት ሀገር ተንከራተው ምንም  ሳያተርፉ እንዲያውም ያላቸውን አጥተው የተመለሱ ወገኖች በእልህና በቁጭት ተነሳስተው በአገራቸው ላይ በመስራታቸው ያለ ስደት አማራጭ የሌለ ለሚመስላቸው ሁሉ የለውጥ ፋና ወጊነቱን ድርሻ  ወስደዋል፡፡

ይህንን እውነት በማስገንዘብ የችግሩን ሰንኮፍ ከስሩ ለመንቀል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በአግባቡ መፈተሸ ደግሞ የመከራ ሾተል የመዘዘችባቸውን የስደት ሀገር የሙጥኝ ያሉ ወገኖቻችንን ህይወት ለመታደግ የሚያስችል ቀዳሚ እርምጃ ይሆናል፡፡ በስደት ምድር ከአሁን አሁን ምን ይመጣብን ይሆን? ብለው ነፍስና ስጋቸው እየተላቀቀ የሚገኘው ወገኖቻችን ሳር የሚበቅልበት የቤታቸው ጓሮ፣ ረግጠው የሚሻገሩት ድንጋይ፣ አሻግረው የሚመለከቱት ኮረብታና ተራራ ሁሉ የሀብት ምንጭ የሆነባት ሀገር እንዳለቻቸው የሚያስረዳ ፣ ሰርተው የሚለወጡበትን መንገድ የሚመላክትና በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ የሚያደርግላቸውን ወገን አጥብቀው ይሻሉ፡፡

ባለፉት ጊዜያት በተመሳሳይ ሁኔታ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የሳዑዲ አረቢያ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው በተመለሱበት ወቅት መንግስት ተመላሾቹን ለማቋቋም የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን ሲያከናወን ቆይቷል፡፡ በዚህ እድል ተጠቅመው ለሌሎችም የተረፉ ጥቂቶችንም አይተናል፡፡ ሆኖም ግን ሁሉም ተመላሾች ውጤታማ ነበሩ ለማለት አያስደፍርም፡፡ በዚህም ተስፋ ቆርጠው ወደ ቀደመው የስደት ህይወታቸው የተመለሱም ይኖራሉ፡፡ ይህ መሰሉ ሁኔታ  በስደት ላይ የሚገኙ ሰዎች ወደ ሀገራቸው የመመለስ ፍላጎታቸውን የሚነጥቅ ሊሆን ይችላልና በይበልጥ ሊታሰብብት ይገባል፡፡ ለዚህም የነበሩትን ክፍተቶች ለይቶና መርምሮ የተሻለ ዕድል በማመቻቸት ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡

በስደት የተንገሸገሹ ዜጎችን አጠቃላይ ሁኔታ ከግምት ያስገባ፣ እንዲያው ለታይታና ለይምሰል ሳይሆን ተጨባጭ ለውጥን ማምጣት የሚችል፣ በአሰልቺና ተስፋ አስቆርጭ ቢሮክራሲ የተቆላለፈ ሳይሆን ቀላልና ግልፅ በሆነ አሰራር የሚተገበር፣ የአንድ ሰሞን ትኩረትና ርብርብ ብቻ ሳይሆን የስደት ተመላሾችን ህይወት በዘላቂነት የሚቀይር ስራ ለመስራት ምን ያህል ተዘጋጅተን ይሆን? ‹‹ሂዱ ውጡልኝ!›› የሚለውን የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ትዕዛዝ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ለመሸጉ ወገኖቻችን በሀገራቸው የሚጠብቃቸውን ተስፋ በምን ያህል መጠን አጉልተን እያሳየናቸው ይሆን? ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ ያሳየውን አይነት ቁርጠኝነት  በተመሳሳይ ስደተኞችም በየደረጃው ሊስተናገዱ የሚችሉበት ዕድሉም እንዳለ በማመን ይህንኑ ዕድል መጠቀም እንዲችሉ የሁሉንም አካል ርብርብ ይጠይቃል፡፡

ለእነዚህና መሰል ጥቄዎች በቂ ምላሽ ለመስጠት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ከረፈደ ግን መከራው ይበረታል፡፡ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ወደ መጠናቀቂያው እየገሰገሰ ነው፡፡ ድብደባ፣ እንግልትና ከየቤቱ እየታሰሱ እስር ቤት መታጎር የጊዜ ገደቡ ሲጠናቀቅ ወገኖቻችንን የሚጠብቃቸው እጣ ፋንታ ነው፡፡ እያንዳንዷ  ሰከንድ መፃዒ እድላቸውን ለመወሰን ዋጋ ይኖራታል፡፡ ሀገርና ወገን እያላቸው እንደሌላቸው የተቆጠሩ ዜጎቻችንን አለንላችሁ! ለማለት ለነገ ቀጠሮ የምንይዝበት ጊዜም አይኖርም፤ ከምናደርግላቸው ሞቅ ያለ ኢትዮጵያዊ አቀባበል ቀጥሎ በዘላቂነት ሊቋቋሙ የሚችሉበትን ዕድል ተረባርበን በሀገር ውስጥ ሠርቶ መለወጥ እንደሚችሉ ልናሳያቸው ይገባል፤ በእናት ምድራቸው ህይወታቸውን ለማሳካት ሊጓዙበት የሚችሉበት የብርሃን ጎዳና እንዳለ በተግባር ጠቁመን እባካችሁኑልን! ልንላቸው ግድ ይላል፡፡

ተባብሮ የድህነት ተራራን እየናደ የሚገኘው ክንዳችን ይህን እውን ማድረግ ከቶውንም ያቅተዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በእርግጥም ለዘመናት አንገታችንን ያስደፋንን ድህነት ለመሻገር መጪው ጊዜ ብሩህ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ተግባራዊ እየተደረጉ በሚገኙ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጦች ኢትዮጵያ ፈጣን እድገትን እያስመዘገቡ ከሚገኙ የአለም ሀገራት ተርታ እየተሰለፈች እንደምትገኝም አለም እየመሰከረላት ነው፡፡ ከዚህ ፈጣን ልማት ዜጎችን በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰሩት ስራዎች ከሀገር ወጥተው በስደት እሳት እየተጠበሱ የሚገኙ ወገኖቻችንን ህይወት መታደግ የሚቻልበትን ሁኔታም ጭምር ከግምት ካስገቡ የድህነታችን ጠባሳ የሚገለፅባቸውን አሻራዎች ሁሉ ፈፅሞ መደምሰስ የሚቻልበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም፡፡

በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ስር ሰዶ የተንሰራፋውን ስደትን ብቸኛ የህይወት አማራጭ አድርጎ የመወሰድ አመለካከት ላይ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ስራዎችም ከዚሁ ጎን ለጎን ተጠናክረው ሊሰሩ ይገባል፡፡ ጉዳዩ በመንግስት ላይ በሚወድቅ ጫና ብቻ መፍትሔ ይመጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ መላው ህብረተሰብ ስደትና ስደትን የሚያስከትለውን አስተሳሰብ ለመግታት የየራሱ ድርሻ እንዳለው ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የህገወጥ ደላላ  አታላይነት እስካልቆመ ድረስ የስደት አሰቃቂ ጣጣ ይከስማል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ወላጆች የየራሳቸውን አመለካከት ፈትሸው ለለውጥ ካልተጉ፣ በጥቅል ማህበረሰቡ የስደትን አስከፊነት ተገንዝቦ እኮ ስደት ለምን! ብሎ ካልመከረና ካልገሰፀ ከስደት መራር ፅዋ ቀማሾች የመሆናችንም እውነታ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ የሰለጠኑ ሀገራትን ቅንጦት በማወድስ የሚዘግቡ ሚዲያዎቻችንና ከሀገር መውጣትን የስኬት ጫፍ አድርገው የሚሳዩ የኪነ ጥበብ ውጤቶቻችን ለድርጊቱ መስፋፋት እያሳደሩ ያሉትን አሉታዊ ጫናም ቆም ብለው ካላጤኑ የማያውቀውን ሀገር ዘወትር የሚናፍቅ ትውልድ የመፍጠራቸው እውነት ነገም ይቀጥላል!

ስለሆነም ሁላችንን የድርሻችንን በመውጣት አንገታችንን ያስደፋንን ድህነት አሽቀንጥረን ለመጣል መስራት ይጠበቅበናል፡፡ ለዘመናት በድህነት አዙሪት ውስጥ እንድንኖር ያስገደደንን ያረጀ አስተሳሰብ በተስፋ በተሞላ አዲስ ስብዕና ፣ ለውጥን በሚያቀነቅን ማንነት ሲተካ ስማችን ይታደሳል፤ የደጃችንን ሲሳይ ተራምደን ከሰው ደጃፍ ለቁራሽ ያሳደረን የሩቅ ሀገር ናፈቂነታችን ሲሽር የእኛነታችን ገፅታ ይለወጣል፤ ጉልበታችን በርትቶ ህብረታችን ጠንክሮ ታሪካችን ይቀየራል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy