Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስደት ብሔራዊ ክብርን ይጎዳል

0 483

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስደት ብሔራዊ ክብርን ይጎዳል

     ዳዊት ምትኩ

የዛሬዋ ኢትዮጵያ በተስፋ የተሞላች ናት። ይህች ባለ ተስፋ ሀገር ከራሷ አልፎ የሌሎች ሀገር ህዝቦችን እየታደገች ነው። በአሁኑ ወቅት በዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተመዘገበ ያለው ለውጥ የዚህ አባባል ሁነኛ ማሳያ ነው። እናም አዲሲቷ ኢትዮጵያ ባለ ተስፋና ዜጎቿን ወደ ተሻለ የህይወት ጎዳና በመምራት ላይ የምትገኝ በመሆኗ ሳይሰደዱ እዚሁ ሀገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ከመንግስት ባሻገር፤ ቤተሰብ፣ ጎረቤትና ዘመድ አዝማድ ዕውነታውን በማስረዳት ረገድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይገባል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደ አውሮፕያኑ አቆጣጠር በ2000 ዓ.ም ያወጣውና “የፓሌርሞ ስምምነት” እየተባለ የሚጠቀሰው ሰነድ ላይ በግልፅ እንደተገለፀው፤ ሰዎችን ለብዝበዛ ዓላማ በኃይል፣ በዛቻ፣ በተንኮል፣ በማታለል፣ በመጥለፍ ወይም በተበዳይ ላይ ኃላፊነት ላለው ሰው ገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅም በመስጠት መመልመል፣ ማጓጓዝ፣ ማስተላለፍ፣ መደበቅ ወይም መቀበል ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መሆኑን ያስረዳል።

የሀገራችን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ህግም ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወርን በወንጀል ተግባር ይፈርጀዋል። ይኸውም ሰዎችን በኃይል ወይም በማታለል መመልመል፣ በሀገር ውስጥ ወይም ወደ ሌላ ሀገር ህገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወር እና አዘዋዋሪዎች ተበዳዮችን የገንዘብ ጥቅም ማግኛ ማድረጋቸው ወይም ለብዝበዛ የተጠቀሙባቸው እንደሆነ በወንጀል ድርጊት እንደሚያስጠይቅ እንደሆነ ትርጓሜ ሰጥቷል።

እርግጥ የዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ያገኘና በተግባር እየተከናወነ ያለ ጉዳይ ነው። እናም እዚህ ላይ ዜጎች ለምን ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ እያልኩ አለመሆኑ ሊታወቅልኝ ይገባል። ይሁንና ሰዎች በሀገር ውስጥ ወይም ወደ ውጭ ሀገር ከቦታ ወደ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወይም ስደት የተሻለ ስራ ፍለጋና ህይወት ወይም ልክ ወንድም እንደሆነው የኤርትራ ህዝብ ከጭቆና ለመሸሽ አሊያም የመኖሪያ ቦታን ለመቀየር ሊሆን ይችላል።

ዳሩ ግን የእንቅስቃሴው ዓላማ በሰዎች ለመነገድ ሲባል የሚከናወን ከሆነ ተግባሩ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚፈረጅ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርበታል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሁለት ዓመታት በፊት ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ባደረገው ጥናት፤ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን መካከል 76 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆኑት የህገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባዎች መሆናቸውን አረጋግጧል። የዚህ ጉዳይ ዋነኛ ተዋናዩቹ ህገ ወጥ ደላሎች መሆናቸውም ታውቋል።

እርግጥ የእነዚህ ህገ-ወጥ ደላሎች ግንኙነት እንደ ሰንሰለት በተያያዘ ሰንሰለት የተቆራኘ ነው። ይሁንና በዚህ አነስተኛ ፅሑፍ ላይ ከህገ-ወጥ ደላሎቹ ማንነት፣ አሰራራቸውና በዝውውሩ ሂደት ከሚኖራቸው ሚና አኳያ አዘዋዋሪዎቹን የአካባቢ፣ ድንበር አሻጋሪ፣ ጉዞ አቀላጣፊ፣ ከስደት ተመላሾችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በመዳረሻ ሀገራት የሚገኙ ደላሎች በማለት ልንከፍላቸው እንችላለን። የአካባቢ ደላሎች በመገኙባቸው ቦታዎች የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና በሌሎች ዘዴዎች ለህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አመቺ ሁኔታ የመፍጠር እንዲሁም ተጋላጭ ግለሰቦችን የመለየት ስራን ከሌሎች ጋር በመሆን ያከናውናሉ። ድንበር አሻጋሪዎቹም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን የሚያዘዋውሩ በኮንትሮባንድ ነጋዴነት የሚፈረጁ ናቸው። እነዚህ አዘዋዋሪዎች ሰዎችን በቡድን ከአካባቢ ደላሎች ተቀብለው ለሌሎች ተመሳሳይ አዘዋዋሪዎች የማስተላለፍ ስራዎችን ይተገብራሉ።

ጉዞ አቀላጣፊዎቹም ቢሆኑ መቀመጫቸውን ትላልቅ ከተማዎች ላይ በማድረግ ወደ መዳረሻ ቦታዎቹ የሚደረገውን ጉዞና የቅጥር ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ ሲሆን፣ ከስደት ተመላሾችና ቤተሰቦቻቸው ደግሞ ዘመድና ጎረቤቶች እናግዛለን በማለት እነርሱ ወደ ነበሩበት ሀገር ሄደው እንዲቀጠሩ በግለሰብ ደረጃ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በመደበኛነት የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

የእነዚህ ከስደት ተመላሽ ዜጎች እንቅስቃሴ በቤተሰባቸውም ይደገፋል። ቤተሰቦቻቸው ልጆቻቸው ውጪ ሀገር ሄደው የሚያመጡት ገንዘብ በምን ሁኔታ የተገኘ መሆኑን ስለማይገነዘቡ ከስደት የተመለሱት ልጆቻቸው ያስገኙላቸውን “ጠቀሜታዎች” በመዘርዘር የህገ-ወጥ ስደቱ ሂደት ተካፋይ ይሆናሉ። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በደላልነት ተሰልፈው የዜጎቻቸውን ህይወት ለአደጋ አሳልፈው ይሰጣሉ። በእነዚህ መንገዶች ከሀገራቸው በህገ ወጥ ሁኔታ በመውጣት ራሳቸውን ያገለጡት ዜጎች በመዳረሻ ሀገሮች ውስጥ የሚገኙ ደላሎች እጅ ላይ ይወድቃሉ። እነዚህ ህገ ወጥ ደላሎችም ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው የተለያዩ ደላሎች አማካኝነት የቀረቡላቸውን ግለሰቦች፤ በማታለል፣ በማስገደድ አሊያም በማስፈራራት በቀጥታ ለብዝበዛ እንዲጋለጡ ያደርጓቸዋል። በዚህ መንገድ ወደ ሌሎች ሀገራት ውስጥ የሚገቡ ዜጎች በመንገድ ላይ ህይወታቸው ካላለለፈና ወደ መዳረሻ ሀገሮች በሰላም ከገቡ ዕጣ ፈንታቸው ብዝበዛ ወይም ለህልፈተ-ህይወት ከሚዳርግ አደገኛ ሁኔታ ጋር መላተም ነው። በህገ ወጥ መንገድ ገንዘቡን የከፈሉት ወጣቶች በገዛ ገንዘባቸው ህይወታቸውን አጥተው ህልፈታቸውም ለቤተሰባቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ሃዘኑን ለሚሰሙት ዜጎች የእግር እሳት ይሆናል።     

በአሁኑ ወቅት በመንግስት በኩል ያለው ቁርጠኝነት በመዋቅሩ ውስጥ የሚገኙ ኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ እየተደረገ ባለው አጠቃላይ ክትትልና ርምጃ ሁኔታው ወደ መሻሻል ያዘነበለ ነው። የግለሰቦቹን ተግባር በተገቢ ሁኔታ ለማረም ህብረተሰቡና መንግስት ተቀናጀተው መስራት እንደሚገባቸው እነዚህ ጥቆማ የሰጡኝ ወገኖች ያስረዳሉ።     በመንግስት በኩል ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ችግሩን ለመፍታት የፖሊሲ፣ የፕሮግራምና የህግ ማዕቀፎች ተበጅተው ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው።

ጉዳዩን የሚከታተል ግብረ ኃይል ከማቋቋም አንስቶ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን እስከመስጠት ድረስ ያሉት ጥረቶች “ይበል” የሚያሰኙ ናቸው። ይሁንና ጥረቶቹ ህዝብን ባማከሉና ወደ መሬት ወርደው ገቢራዊ በሚሆኑ አሰራሮች ይበልጥ ሊደገፉና የችግሩን አስኳል ለይተው ሊያወጡ በሚችሉበት ሁኔታ መቃኘት ይገባቸዋል። ጥረቶቹ የሚያስገኟቸው ውጤቶችም የጉዳዩ ዋነኛ ተዋናይ ከሆኑት ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች አኳያ እየተመዘኑ፣ ተመልሰው ህዝቡን የሚያስተምሩበት መንገድም መመቻቸት አለበት።

ለዚህ ደግሞ በቅርቡ ከሳዑዲ አረቢያ በመመለስ ላይ የሚገኙት ዜጎች አስተማሪዎች ሊሆኑ ይገባሉ። እነዚህ ዜጎች የሳፁዲ መንግስት በሰጠው የሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ናቸው። እነዚህ ወገኖች እንዴት በህገ ወጥ ደላሎች እንደተታለሉ፣ እንዴት ወደ ሀገራቸው እንዳይመለሱና ሆን ተብሎ ለችግር እንዳይጋለጡ ሲደረግ እንደነበር በተገቢው ሁኔታ የሚያስተምሩ ናቸው።

ከሳዑዲ ተመላሾቹ ዜጎች የስደትን አስከፊነት ከእነርሱ በላይ የሚያውቀው የለም። ስደት ራስን፣ ወገንን እና ሀገርን እንደሚጎዳ በማያሻማ ሁኔታ ሊገልፁ የሚችሉ ናቸው። ስደት ምን ያህል አንገትን አስደፍቶና ክብርን አዋርዶ እንደሚያንገላታ ከእነርሱ በላይ እማኝ ማግኘት አይቻልም። ስለሆነም የስደትን መጥፎ ገፅታ ከእነዚህ ወገኖች ተሞክሮ በመነሳት ማስተማር ይቻላል እላለሁ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy