Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአንድ እጅ ማጨብጨብ እንዳይሆን…

0 405

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአንድ እጅ ማጨብጨብ እንዳይሆን…/አባ መላኩ/

እንደ ኅብረተሰብ የጋራ ስምምነት የተገለፀበትና የጋራ መግባባት የተያዘበት  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አገሪቱን ወደ ጥንቱ የታላቅነት ከፍታዋ መልሶ የዕድገትና ብልጽግና ጐዳናን መርገጧን የሚያመላክት ጠቋሚ ምዕራፍ ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ የቀደምት ትውልዶች አገራዊ ህልም እውን የማድረጉ ታሪካዊ ጉዞ ተጀምሯል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በራስ ምጣኔ ሀብታዊ አቅም የመገንባቱ ጥረትም ተጠናክሮ  ቀጥሏል፡፡

 

በእርግጥም ይህ ታላቅ ፕሮጀክት ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ለዘላቂ ልማት ቆርጠው መነሳታቸውን በጉልህ የሚያንፀባርቅ ሀቅ ነው፡፡  አንዳንድ አገራዊ ህልውናን የመገንባት ታሪካዊ ጉዞን የሚያጠኑ ተንታኞች እንደሚሉት “ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን የማይገሰስ የውኃ መብትን ተጠቅማ ትርጉም ያለው የልማት ተግባር እያከናወች ያለች አገር” ይሏታል።

 

ዛሬ የመሠረተ ድንጋይ ከተቀመጠለት ስድስተኛ ዓመቱን ያሳለፈው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ግንባታው ግለቱን ጠብቆ መጓዙም እርግጥ ሆኗል።

 

ኢትዮጵያ የመላ ህዝቧቿን የጋራ ህልውና በእጅጉ ሲፈታተን በቆየው ሥር የሰደደ ድህነትና ኋላ ቀርነት ላይ የሞት ሽረት የዘመቻ ትግል ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህን ደግሞ  እንኳን የቅርብ ጐረቤት ከሩቅ የሚታዘበው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር ምስክርነቱን የሚሰጥበት እውነታ ነው፡፡

 

ይሁንና የአዲሲቷን ኢትዮጵያ መፃኢ ተስፋን በሚሰብክው በዚህ ታላቅ ፕሮጀክት መሳለጥ እንቅልፍ ያጡ አልጠፉም፡፡ በተለይ ደግሞ የሻዕቢያ አገዛዝ ባለሥልጣናት የህዳሴው ግድብ ሥጋት ሆኖባቸዋል፡፡

 

እነዚህ ባለሥልጣናት በሚሰፍሩላቸው ቀለብ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ሽብር ፈጣሪ ቡድኖችም በአጋዥነት ሲሰለፉ ይታያል፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ሰርገው በመግባት ጥቃት ሊፈጽሙ የሞከሩና በሕዝብና በሚሊሺያ ኃይሎች ድባቅ ተመትተው ዒላማቸው የከሸፈባቸውን የዚያን ሰሞኑን የፀረ ህዝብ ኃይሎች ጥረትን ማስታወስ በቂ ነው።

 

የኤርትራ ባለሥልናት የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ለምን እንቅልፍ ነሳቸው? ወደ ኋላ እስቲ መለስ ብለን እናስታውስ። የአሥመራው አገዛዝ ቁንጮ ኢሣያስ አፈወርቂ እ.አ.አ 2016 አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ለኤርትራ ህዝብ በአገሬው ቴሌቪዥን ሁለት ሰዓት በፈጀ ቃለ ምልልሳቸው ላይ የደሰኮሩት ጉዳይ ትዝብት ላይ ነው የጣላቸው። በማያገባቸውና በማይመለከታቸው የሌላ አገር ጉዳይ ውስጥ ገብተው ለምን መዘባረቅ ሞከሩ?፤ ይህ ዲስኩራቸው ያኔ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን ፈርጀ ብዙ የህዳሴ ጉዞ እንቅልፍ እንደነሳቸው አሳብቆባቸዋል።

 

የአገሬው ዜጋ እጣ ፈንታ አፈና፣ ሰቆቃና ሥደት ሆኗል። በሠላም ገብቶ መውጣት ቅንጦት ሆኗል። በኃይል ታፍነው በውትድርና ማሰልጠኛ ጣቢያዎች መታጎር የእለት ተእለት ግዴታቸው ሆኗል። በድህረ ነፃነት ኤርትራ የአምባገነኑን ኢሣያስ አፈወርቂ የፈላጭ ቆራጭነት ሥልጣን ለመጠበቅ ሲባል ብዙ አስነዋሪ ድርጊቶች ተፈፅመዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሚወዷት አገራቸው የሚሰደዱት ዜጎች እማኝ ምስክር ናቸው፡፡

 

በመሠረቱ በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ወጣቶች ባገኟት ቀዳዳ ሾልከው አገራቸውን ጥለው እንደሚሰደዱ ይታወቃል፡፡ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ከ180 ሺህ ያላነሱ ወጣት ኤርትራዊያን በስደር እንደሚኖሩ ልብ ይሏል።  

በእብሪተኝነት ተነሳስተው ባድመ ላይ የጫሩት እሣት እርሳቸውንና ጦረኛ ሥርዓታቸውን አጋይቶ ለአሳፋሪ ሽንፈት እንደዳረጋቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነት ሽንፈትን ተከትሎ የሻዕቢያ ባለሥልጣናት የወያኔ አገዛዝ እያሉ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ጥላሸት ለመቀባት ሲጠሩ ተስተውሏል፡፡ የሀሴት ሴራ ማውጠንጠንንም የሥራቸው አካል በማድረግ ብዙ ደክመዋል፡፡

 

ቀደም ሲል ወዲአፎም ወይም ደግሞ ኢስጢፎ በሚል ቁልምጫ ይጠሯቸው የነበሩ አፍቃሪ ሻዕቢያ ኤርትራውያን ጭምር አሁን…አሁን ኢሣያስ በቴሌቪዥን መግለጫ ሊሰጥ እንደሆነ ሲሰሙ ግድም አይሰጣቸውም፡፡ የጐረቤት ኢትዮጵያን መንግሥት ለማጥላላት ካለመ ባዶ ፕሮፖጋንዳ ያለፈ የሚናገረው የለም ሲሉም ይደመጣል፡፡ ለኤርትራና ህዝቧ ተጨባጭ ፋይዳ የሚያስገኝ ምን አዲስ ነገር ይዞልን ቀርቧል? ሲሉም መጠየቅ ጀምረዋል።

 

የኤርትራው መሪ ወደ ምድራዊ ሲኦልነት እንደትቀየር ስላደረጓት አገራቸውና ስለሚቀልዱበት አሳረኛ ህዝብ ምንም መናገር አይፈልጉም፡፡ ከዚህ ይልቅ እርሳቸውን በማይመለከታቸው በሌሎች ሉዓላዊ አገራት የውስጥ ጉዳይ በመግባት  ሲዘበራርቁ መስማት የተለመደ ሆኗል።

 

አምባገነኖቹ የሻዕቢያ ባለሥልጣናት የኢትዮጵያን መንግሥት ለማጥላላት ቢሞክሩም ኤርትራውያን ግን ስለ ኢትዮጵያ ነባራዊ እውነታ በደንብ ያውቃሉ፡፡ የችግራቸው ጊዜ መጠለያቸው መሆኗንም አስረግጠው ይረዳሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ምንም እንኳ ፕሬዚዳንቱና አጃቢዎቻቸው ይህ እውነታ ባይዋጥላቸውም፡፡

ለማንኛውም እብሪተኛው የኢሣያስ መንግሥት ባድመን ወርሮ ተቀጥቅጦ አካባቢው ለቅቆ ከወጣ ድፍን ሃያ ዓመት ሊሞላው ተቃርቧል። የሁለቱ አገሮች ድንበር አካባቢ አሁን ያለበት ሁኔታ ፈረንጆቹ ኖ ፒስ ኖ ዋር የሚሉት “ሠላም የለሽ፣ ጦርነት የለሽ” ቀጣና ውስጥ ይገኛል።

ይህ ሁኔታ እስከ መቼ በዚህ መልኩ ይቀጥል ይሆን? በኢትዮጵያ በኩል ባለፉት ዓመታት ችግሩን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት በርካታ ሙከራዎች ሲደረጉ ቆይተዋል – ምንም እንኳን መሬት ላይ የወረደ ለውጥ ባይገኝም። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያለውን ውዝግብና ግጭት “በውይይትና በድርድር መፍታት”፣ ይህ ካልሆነ ግን ለሚቃጡባት ትንኮሳዎች “ተመጣጣኝ ርምጃ በመውሰድ” ጉዳዩን አስታግሳለሁ ዓይነት ፖሊሲን ስትከተል ቆይታለች።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያ ኤርትራን በተመለከተ አዲስ ፖሊሲ ልትከተል እንደምትችል በቅርቡ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቋቁማሉ፡፡ ይህን ችግር ከሥር መሠረቱ ለመቅረፍ ይረዳል በሚል አዲስ ፖሊሲ ልታወጣ ስለመሆኗ እየተነገረ ይገኛል። ኢትዮጵያ ኤርትራን በተመለከተ ከዚህ በፊት ታራምደው ከነበረው ሕግ ለየት ያለ ይዘት ያለው ፖሊሲ ማርቀቋን በመግለጽ ጭምር። ምንም ይሁን ምን በሉዓላዊነቷ ላይ የማትደራደረው ኢትዮጵያ ስለሠላም ያላት አቋም መቼም ተዛንፎ አያውቅም። ስለ ሠላም ሲባል ሁሉም በጋራ ሊያስብበት ይገባል። በአንድ እጅ ብቻ ማጨብጨብ እንዳይሆን።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy