Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በጋራ ሰርቶ አብሮ የማደግ ትልም ይበልጥ እውን ይሁን!

0 249

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በጋራ ሰርቶ አብሮ የማደግ ትልም ይበልጥ እውን ይሁን!

                                                     ዘአማን በላይ

የኢትዮጵያ ህዝቦች ወቅታዊ ሁኔታ ቀደም ሲል ከነበረው ‘ማንነታቸው’ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ተሻሽሏል፡፡ ትናንት አንገታቸውን ደፍተው፣ ተሸማቀውና የድህነት ተምሳሌት በመባል መጠቋቀሚያ በመሆን አሳዛኝ የሃፍረት ካባን ደርበው አጎንብሰው ይሄዱ ነበር። ዛሬ ግን ምስጋና ይህን  ስርዓት ለማምጣት ውድ ህይወታቸውን ቤዛ ላደረጉት የህዝብ ልጆች ይግባቸውና ከአንገታቸው ቀና ብለው መሄድ ጀምረዋል፡፡ በተለይ ባለፉት 15 ዓመታት ይህን የያኔውን ‘ማንነታቸውን’ ለመቀየር በመንግስት መሪነት ጠንክረው በመስራት አዳፋ ካባቸውን በየደረጃው አሽቀንጥረው ጥለዋል፤ እየጣሉም ይገኛሉ፡፡

እናም ዛሬ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን በመዋጋት ህዝባቸውን ከችግር ማላቀቅ በሚገባቸው ወቅት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለት መንገዶችን የመጠቀም አስፈላጊነትን ተገንዝበዋል፡፡ እነርሱም ውስጣዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል በህዝብ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ የልማት ትልምን መከተል እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ ተቋማትን የማስፋፋት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡

ታዲያ እነዚህ አቅጣጫዎች በዋነኛነት የፀረ ድህነት ትግሉን ከዳር የማድረስ ዓላማና ግብ ያላቸው ሲሆኑ፤ በአንድ በኩል በነፃነትና በሉዓላዊነት መርህ ላይ ተመስርተው ዕድገታቸውን የሚያፋጥኑበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተፈጥሯዊ ሃብታቸው የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ተቀናጅተውና ተባብረው ለመስራት ምቹ ዕድል የሚፈጥሩላቸው ናቸው፡፡

ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚያውቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ዕውን ከሆነበት ከዛሬ 22 ዓመት ጀምሮ የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የዜጎቹን እኩል ተጠቃሚነት በየደረጃው ለማረጋገጥ ዋነኛ ጠላት በሆነው ድህነትን የመቅረፍ ስራ ትኩረት ሰጥቶ ተግባሩን በሚገባ ተወጥቷል፡፡ በዚህም በአንድ በኩል ውስጣዊ ችግሮች ላይ በማተኮርና አቅም በፈቀደ መጠን እልባት በመስጠት ተግባር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር በሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ተቋማት የማስፋፋት ስራን አከናውኗል፡፡ እያከናወነም ይገኛል፡፡

የሀገራችን የፀረ- ድህነት ትግል በህዝቦች ሰፊ ተሳትፎ ታጅቦ በመጓዙና ችግሮቹን በመፈተሽ እንደ ክብደታቸው በቅደም ተከተል ለመቅረፍ በተከናወነው ብልህነት የተሞላበት መንግስታዊ አካሄድ ሀገሪቱንና የህዝቦቿን ኑሮ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያስቻለ ነው፡፡ ይህም ሀገራችንን በዓለማችን የፈጣን ዕድገት ባለቤቶች ሀገሮች ጎራ እንድትመደብ ያደረጋት ነው፡፡ ትናንት የድህነት ተምሳሌት የነበረችው ሀገራችን፣ ዛሬ የዕድገት ተምሳሌት መሆን ችላለች፡፡ ታዲያ ለዚህ ውጤት መመዝገብ ዓይነተኛው ምክንያት መንግስት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን በመለየትና እልባት ለመስጠት ያከናወነው ጥረት መሆኑን ለመገንዘብ አዳጋች አይመስለኝም፡፡

ርግጥ ባለፉት 15 የዕድገት ዓመታት የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች በተለይም የዘመናት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ምላሽ መስጠቱ እንዲሁም የትምህርት፣ ጤና፣ የመንገድ፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች መሰረተ ልማት ተቋማት እንዲስፋፉ ማድረጉ፣ የመልካም አስተዳደርና ፍትህን የማግኘት ጉዳዮች አቅም በፈቀደ መጠን በየደረጃው እንዲከናወኑ ባደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ሀገራችንን ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር ተችሏል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳዮቿ ላይ ዋነኛ ትኩረት ሰጥታ ስትሰራ የቆየችና የህዝቦቿን የልማት ተጠቃሚነት በየደረጃው ለማረጋገጥ መንቀሳቀሷን የሚያመላክት ሃቅ ነው፡፡

ያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን የውስጥ ተጋላጭነታችን በሚፈለገው መጠን ተቀርፏል ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ምንም እንኳን ሀገራችን ውስጥ እየተመዘገበ ያለው የልማት ዕድገት ከህዝቡ ቁጥር መጨመር ብሎም ከማስፈፀም አቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ በሚፈለገው መጠን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንዳይሆን ቢያደርግም፣ እዚህ ሀገር ውስጥ ዜጎች በየደረጃው ከተገኘው ዕድገት ተጠቃሚ መሆናቸው የሚካድ አይመስለኝም፡፡ ይህ ሁኔታም የሀገራችንን ዕድገትና ብልፅግና የማይመኙ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ከፀረ-ሰላምና ከሽብር ኃይሎች ብሎም ከፅንፈኛ ዲያስፖራዎች ጋር በመቀናጀት ወጣቶችን ባልተገባ መንገድ በማሰማራት በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጥሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ የውስጥ ተጋላጭነትን አቅም በፈቀደ መጠን በተገቢው መንገድ መቅረፍ የሚገባ ይመስለኛል፡፡

ርግጥ የውስጥ ተጋላጭነታችንን መቅረፍ ባልቻልን ቁጥር፤ ለውስጥና ለውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና አሸባሪዎች ይበልጡኑ የሚጋለጠው ከሀገራችን የህዝብ ብዛት ውሰጥ የማይናቅ ቁጥር ያለው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ይህ ኃይል ትኩስና ያለበት የዕድሜ ደረጃ በበቂ ሁኔታ ለማመዛዘንና ለስሜታዊነት ቅርብ የሚያደርገው በመሆኑ በቀላሉ ለእነዚህ ሃይሎች የውሸት ስብከትና አሉባልታ የመጋለጥ ዕድሉ የሰፋ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ስለሆነም በማንኛውም ወቅት በሚነሱ ውዥንብሮች ውስጥ ባለማወቅ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆኖ የችግር ሰለባ ሊሆን መቻሉ አይቀሬ ነው፡፡

ምንም እንኳን መንግስት በወጣቶች ፓኬጅ ላይ የተጠቀሰውን የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በማቋቋም ወደ ስራ እንዲገባ አስር ቢሊዩን ብር ቢመድብም እንዲሁም ክልሎችም ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት በጀት ቢይዙም አሰራሩ ወጥነት ያለው አይመስልም፡፡ እዚህም ሆነ እዚያ የሚቀር ቅሬታዎች ይደመጣሉ፡፡ ቅሬታዎች ተገቢ ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ ዋናው ጉዳይ ለሚቀርቡ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች የጉዳዩን ባለቤቶች በማወያየት ከመፍታቱ ላይ ነው፡፡

ርግጥ በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እስከ ታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ ዘልቆ መፍታት ይገባል፡፡ ተደጋግሞ እንደሚገለፀው የመልካም አስተዳደር ችግር ከህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ጉዳዩች ጋር የተያያዙ በመሆናቸው በቂ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ፌዴራል መንግስትና ክልሎች ለወጣቶች በቂ በጀት መድበው ሳለ፤ በአፈፃፀም ጉዳይ ሳቢያ ይህ የተቀደሰ ተግባር ሊሰናከል አይገባም፡፡ በጀት ሰጪውም ይሁን በበጀቱ የሚጠቀመው አካል በተገቢው ሁኔታ መናበብ አለባቸው፡፡

መንግስት በጋራ ሰርተን በጋራ እንደግ በሚል ልማታዊ እሳቤ ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በጀት መድቦ ሲያበቃ፤ አስፈፃሚው ክፍል ይህን ታላቅ ተግባር በአሰራር ግድፈቶች የሚሸረሽረው ከሆነ ነገርዬው መልሶ “ታጥቦ ጭቃ” እንደሚባለው ዓይነት ከመሆን አይዘልም፡፡ እናም ለወጣቶች የተመደበው በጀት ለትክክለኛው ስራና ተግባር መዋል እንዳለበት አስፈፃሚው አካል ሊገነዘበው ይገባል እላለሁ፡፡

ርግጥ ይህን ስል ለወጣቶች የተመደበው በጀት ጥቅም ላይ አልዋለም እያልኩ አይደለም። በበርካታ ክልሎች ውስጥ በፌዴራል መንግስት የተመደበውም ይሁን ክልሎች በራሳቸው የመደቡት በጀት ስራ ላይ ውሎ ወጣቶቹም ወደ ስራቸው ገብተዋል፡፡ ይህ የአፈፃፀም ሁኔታ ሊበረታታ ይገባዋል። ያም ሆኖ ግን በአንዳንድ አካባቢዎች በዚህ ረገድ የሚታዮት የአፈፃፀም ችግሮች ሊቀረፉ ይገባል፡፡

በሌላ በኩልም ወጣቶቹም በመንግስት የሚሰጣቸውን ገንዘብ በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ ሊያውሉት ይገባል፡፡ በመሆኑም መንግስት ባለው አቅም በጀቱን ሲሰጥ ወጣቶቹ ሰርተው ይለወጣሉ፤ እነርሱ አድገው ሀገራቸውንም ያሳድጋሉ ከሚል ልማታዊ አስተሳሰብ በመነሳት ነው፡፡ ይህን የመንግስት ፍላጎት ወጣቶቹ በሚገባ ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ እናም ወጣቶቹ የተሰጣቸው ወይም የሚሰጣቸው ገንዘብ እሴት በሚፈጥር መልኩ ሊጠቀሙት ይገባል፡፡

ስለሆነም ወጣቶች እሴት ከማይፈጥርና ወጣቶችን ከማይለውጥ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውንና ሀገራቸውን ከማይቀይር የገንዘብ አጠቃቀም ራሰቸውን ሊያርቁ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ‘የሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ጉዞ ከአንድ ርምጃ ይጀመራል’ እንዲሉ ታታሪዎቹ ቻይናዎች፤ የማንኛውም ስራ መነሻ አነስተኛ ገንዘብ መሆኑን ማወቅ አለባቸው፡፡ ‘የተቀመጠ ያገለግላል’ እንደሚባለውም ወጣቶቹ የቁጠባ ባህላቸውን ሊያሳድጉ ይገባል፡፡ ዛሬ የተቀመጠ ገንዘብ ከመንግስት ብድር የሚያላቅቅና በሁለት እግር ለመቆም የሚያስችል ነው፡፡ ወጣቶቹ ዛሬ ከመንግስት የሚወስዱት ገንዘብ ነገ በቁጠባ አድጎ ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርጋቸው መሆኑ ርግጥ ነው፡፡

ይህን የቁጠባ ባህል እውን ማድረግ ደግሞ በሂደት ኢንቨስትመንትን ያሰፋል፡፡ ኢንቨስትመንት በየትኛውም ደረጃ ሲሰፋ ደግሞ ለዜጎች የስራ ዕድልን ይፈጥራል፤ ምጣኔ ሃብትንም ያደረጃል፡፡ የስራ ዕድል ሲፈጠርና ምጣኔ ሃብት ሲደረጅ ሀገራችን የጀመረችው የልማት ጉዞ ይጠናከራል፡፡ በጋራ ሰርቶ አብሮ የማደግ ትልምም ይበልጥ እውን ይሆናል፡፡  ስለሆነም በአፈፃፀም በኩልም ይሁን በወጣቶቹ ዘንድ የሚታዩት ተግዳሮቶችን በመፍታት ይህን ትልም ማሳካት ይቻላል፡፡ እናም ሁሉም የበኩሉን ሚና መወጣት ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም በየፊናው ‘በጋራ ሰርቶ አብሮ የማደግ ትልም ይበልጥ እውን ይሁን’ የሚለውን መርህ ሁሌም ሊዘምር ይገባል እላለሁ፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy